ጥምቀት – የመንፈስ ቅዱስ ልጅነት ማግኛ ረቂቅ ልጅነት ነው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


“ጥምቀት” የሚለው ቃል ሲተረጎም መጠመቅ፣ ከውሃ ውስጥ መግባት፣ በውኃ መነከር ማለት ነው፡፡ መንፈሳዊ ትርጓሜው ደግሞ “የመንፈስ ቅዱስ ልጅነት ማግኛ ረቂቅ ልጅነት ነው” ይባላል፡፡

Image may contain: night and outdoor

የጎንደር መንበረ መንግስት መድኃኒዓለም ዋና አስተዳዳሪና የአራቱ ጉባኤያት መምሕር ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ በዮርዳኖስ ወንዝ የነበረውን ታሪክ ሲናገሩ አብርሃም ከከላውዲዮን ወደ ከራን፣ ከከራን ወደ ከነዓን በኢየሩሳሌም ሲኖር ይስሐቅን ወለደ፡፡ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፡፡ በያዕቆብ ዘመንም ረሀብ ሆነና እስራኤላውያን ወደ ግብጽ ተሰደዱ፡፡ 215 ዓመታትንም በሀገረ ግብጽ ተቀመጡ፡፡ ይህን ሁሉ ዘመን አልፈውም ታላቁ ሰው ሙሴ ተነሳና እስራኤላውያንን ከግብጽ አውጥቶ ወደ ምድረ ርስት ጉዞ ጀመሩ፡፡

በታላቁ ሙሴ መሪነት ‹ናበው› በሚባል ተራራ እንደደረሱ ሙሴ ቀረ፡፡ የእርሱን ስልጣንም እያሱ ተቀበለ፡፡ የሙሴን ኃላፊነትም ተቀብሎ ወደ ምድረ ርስት መሄዳቸውን ቀጠሉ፡፡ እስራኤላውያን ወደ ምድረ ርስት ሲሄዱ ሙሴ በሲና ተራራ ላይ የተቀበለውን የቃል ኪዳኑን ጽላት ይዘው ይሄዱ ነበር፡፡ በጉዟቸው ላይም በባሕረ ዮርዳኖስ አቅራቢያ ሲዳረሱ እግዚአብሔር ለእያሱ መልዕክት ነገረው፡፡ መልዕክቱም ‹‹ዮርዳኖስን ስትሻገሩ የተለየ ስርዓት አሳያችኋለሁ በዚያ ስርዓትን፣ ባሕረ ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ›› አለው፡፡ ‹‹ሕዝቡ ታቦቱን ከተሸከሙ ካህናት ሁለት ሺህ ክንድ ይራቅ፤ ርቀውም ይከተሉ፡፡ ካህናቱም በወንዙ ሲደርሱ ተአምር ይታያል፤›› ተባለ፡፡ የተባለውንም አደረገ፡፡ ታቦቱን የተሸከሙት ካህናቱም በባሕረ ዮርዳኖስ ሲደርሱ ያ ቅዱስ ወንዝ ለሁለት ተከፈለ፡፡ ግማሹ ወደ ታች ግማሹ ደግሞ ወደ ላይ ሆኖ በመካከሉም መሬት እየታዬ ቆመ፡፡ ባሕረ ዮርዳኖስም ከተፈጠረ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የብስን አሳዬ፡፡ ካህናቱም በተከፈለው ውሃ በታየው የብስ ተሻገሩ፤ ሕዝቡም ተሻግሮ ወደ ርስት ምድሩ ሄደ፡፡

ታቦቱንም ወንዝ እንደ ሚፈራው አመላከተ፡፡ ዘመን ዘመንን ተሻግሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጣ፡፡ በዘመነ እያሱ ያሳየውን ተአምርም እራሱ መጥቶ አሳዬው፡፡ ‹‹በባሕረ ዮርዳኖስ ሲገባው ውሃው በፍርኃት ሸሸ›› እንዳለ መጽሐፍ፡፡ ዮርዳኖስ ከገሊላ ተነስቶ ከሰሜን ወደ ምስራቅ ይፈሳል፡፡ በባሕረ ሎጥም ይገባል፡፡ አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ከመልከፀዴቅ ‹‹ህብስተ አኮቴት ጽዋ በረከት›› ተቀብሏል፡፡ ይህንንም ሊቁ ሲያመሰጥሩት ‹‹አብርሃም የሰው ልጅ ምሳሌ፣ መልከፀዴቅ የካህናት ምሳሌ፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ፣ ህብስተ አኮቴቱ ጽዋ በረከቱ የስጋ ወደሙ (የቁርባን) ምሳሌ ነው›› ብለዋል፡፡

የትዕግስት ምሳሌው እዮብ በባሕረ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ድኗል፤ እያሱም ባሕረ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ብሔረ ሔዋን ገብቷልና ይህ ወንዝ ታላቅ እና ቅዱስ ወንዝ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ክርስቲያኖችም ከከተራው ጀምሮ ታቦቱ በካህናት ከመንበሩ ወጥቶ ወደ ጥምቀተ ባሕር ሲወርድ ከጥምቀተ ባሕር አድሮም ወደ መንበሩ ሲመለስ ካህናቱ ታቦቱን በመንፈሳዊ ስርዓት ሲያጅቡ ክህነት የሌለው ሕዝብ ደግሞ ከታቦቱ ሳይቀርብ ከፊት ከኋላ፣ በቀኝ በግራ አጅቦ ሲሄድ ይታያል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለእያሱ የሰጠውን ቃል ኪዳን ለመዘከርና ለታቦቱ ያላቸውን ክብር ለማሳዬት ነው፡፡ ታቦታትን ከመንበራቸው አውጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር በማውረድ ጥምቀትን በሚያከብሩት ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችም ታቦቱ ከመንሩና ከደብሩ ሲወጣ ጀምሮ በታቦቱ ዙሪያ ታላቅ መንፈሳዊ ክብር እየተደረገ በዓሉ ይከበራል፡፡

በከተማ ታቦቱን የሚሸከሙት ካህናት የሚረግጡት መሬት የክብር መንጣፍ ይነጠፍበታል፡፡ ለምን? ቢሉ ለታቦታቱ ታላቅ ክብር ይሰጣልና ነው፡፡ በገጠር ደግሞ ታቦቱ ከመንበሩ ወጥቶ እስከሚያርፍበት ድረስ የሚገኘው መንገድ እሾህና አሜኬላ እንዳይኖረው ቀደም ብሎ ይጸዳል፡፡ አስቸጋሪ መንገድ ሲኖርም ጥንቃቄ እንዲደረግ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ በዚህ ልዩ ክብር ጥምቀት ይከበራል፡፡ ከተራ የሚባለውም ይሄንኑ ነው መከለል፣ መሸፈን መንከባበከብ ክብር መስጠት ነውና፡፡

መልካም በዓል!

source AMMA