ኢትዮጵያ አሃዳዊነትን ላትመልስ ሸኝታዋለች፣ ይህ ዓይነቱ ስርዓት ሊታሰብ አይችልም። – አቶ ንጉሱ ጥላሁን


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

ኢዜአ ፤ ብልጽግና ፓርቲ “የቆመባቸው ምሰሶዎች ፌዴራሊዝሙን የሚጠብቁና የሚንከባከቡ ናቸው” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬቴሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።

አቶ ንጉስ ሰሞኑን እንደገለጹት የብልጽግና ፓርቲ ግብ የኢትዮጵያዊያን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ባህላዊ፣ ስነ አእምሮአዊና ስነ ልቦናዊ ሁኔታን ባካተተ መልኩ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ነው።

የብልጽግና እሴቶች ተብለው የሚጠቀሱት ህብረ አገራዊ አንድነት፣ የዜጎች ክብርና ነጻነት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ንጉስ ገለጻ፣ “ኢትዮጵያ አሃዳዊነትን ላትመልስ ሸኝታዋለች። ይህ ዓይነቱ ስርዓት ሊታሰብ አይችልም።”

አገሪቷ ባለፉት ዓመታት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቅኝት ስትመራ እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህ ወቅት ያጣቻቸውን እሴቶች በመመለስ ያገኘቻቸውን መልካም ጎኖች ለማስቀጠል መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ፌዴራላዊ ስርዓቱን በማፍረስ አሃዳዊነትን መገንባት የማይታሰብ መሆኑን ጠቁመው፤ አሀዳዊነት ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚንድ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥና እውነተኛውን ፌዴራላዊ ስርዓት ለመገንባት ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ህብረ ብሄራዊ አንድነት ከሰው ልጆች ባህርይ ተነስቶ ወደ አገራዊ ባህርይ ጎልብቶ የሚያድግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ብልፅግና በኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ቋንቋ ባህልና ማንነትን ተከትለው ለተነሱ ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ ባለመሰጠቱ ጥያቄ ሆኖ የተነሳና ያታገለ አጀንዳ መሆኑን አብራርተዋል።

ብልጽግና የዜጎችን ክብር የሚያረጋገጥ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን የግለሰብና የቡድን መብታቸው የሚከበርበት ግለሰባዊና ተቋማዊ ጭቆናዎች የሚወገዱበት ስርዓት እንደሚያሰፍንም ጠቁመዋል።