ዓባይ በእምቦጭ እየተወረረ ነው ተባለ

እምቦጭ ከጣና አልፎ ዓባይን እየወረረ ነው

(አብመድ) ኢትዮጵያ ትንሣኤዋን እውን እንድታደርግ የሚያግዛትን ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት በመገንባት ላይ ትገኛለች:: “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ” እያልን ለምንጠራው ለዚሁ ፕሮጀክት ከአንድ መቶ ቢሊዮን ብር ላይ ውጪ እንደሚደረግም ይታወቃል::

ይሁንና ይህን ያህል መዋእለ ንዋይ እያፈሰሰ ያለው የፌዴራል መንግስት የግድቡ ዋነኛ የውሀ ምንጭ በሆነው ጣና ሀይቅ ላይ አደጋ መደቀኑን እያወቀ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል::

Image may contain: one or more people, outdoor and nature

ችግሩ ከአማራ ክልል አልፎ ለመላ ሀገሪቱ እና ለአጐራባች የአባይ ተፋሰስ ሀገሮችም የሚተርፍ እንደመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማውጣት የዘለቀ ብሄራዊ የአደጋ መከላከል ዘመቻ ማካሄድና ካልተቻለም የጥቅሙ ተጋሪ ሀገራትን ርዳታ መጠየቅና አስተባብሮ መከላከል ይገባው ነበር::
የአማራ ክልል ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ከዓመታት በፊት የጣና ሀይቅ በእምቦጭ አረም ስለመወረሩ፣ በደለል ስለመሞላቱና በመሰል ችግሮች ሳቢያ የመድረቅ አደጋ የተደቀነበት መሆኑን ይፋ በማድረግ መንግስት እና የአባይ ተፋሰስ ሀገራት አፋጣኝ መፍትሄ ማቅረብ እንደሚገባቸው የሚያመላክቱ ተደጋጋሚ ዘገባዎችን ቢያቀርብም መፍትሄ ማምጣት ቀርቶ ሙከራ እንኳን አልታየም::
ይልቁንም “ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ” እንዲሉ ሰሞኑን ኢትዮጵያና ግብጽ በግድቡ ውሀ አሞላል ላይ ውይይት ስለማድረጋቸው ሲነገረን ሀይቁን ከአደጋ የመከላከሉ ተግባር ግን ዛሬም ለአማራ ክልል መንግሰትና ህዝብ እንደተተወ ነው::
ከጥንት ጀምሮ በመማሪያ መጽሀፎቻችን ላይ ጭምር “የግብጽ ህይወት የተመሠረተው በአባይ ወንዝ ላይ ነው” የሚል ጽሁፍ ሲያስነብቡንና ሲያጠምቁን የኖሩት ግብፃዊያንና የሀገራችን መንግስት የሀይቁ የመድረቅ አደጋ ሳያሳስባቸው ውሀ በሌለበት ስለ ግድቡ አሞላል የመደራደራቸውን አስገራሚ ዜና በሰማንበት በዚህ ዓመት እምቦጭ ከጣና አልፎ አባይ ወንዝ ዳርቻዎች በሚገኝ 200 ሄክታር መሬት ላይ ተንሠራፍቷል::
ባለፈው ዓመት በ34 ሄክታር መሬት ላይ የተከሰተው የአባይ እምቦጭ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 166 ሄክታር ጨምሮ ወደ 200 ሄክታር መስፋፋቱ የአደጋውን አሳሳቢነት ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ነው:: ይሁንና ሀገሪቱን በበላይነት የሚያስተዳድረው የፌዴራል መንግስት፣ ጣና በለስን ጨምሮ በጢስ አባይ ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫዎች ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰበስበው የኢትዮጵያ ውሀ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር እና “ህይወታችን የተመሠረተው በአባይ ወንዝ ላይ ነው” የሚሉት ግብጽ እና ሱዳን ሀይቁን ለመታደግ ምንም አይነት ጥረት አለማድረጋቸው እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው የባህር ዳርና አካባቢዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ::

Image may contain: one or more people, outdoor, nature and water
እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ እምቦጭ ከተከሰተበት ዓመት ጀምሮ በመከላከል ተግባር ደፋ ቀና የሚሉት የሰሜንና ደቡብ ጐንደር አርሶ አደሮች፣ የክልሉ መንግስት፣ የአካባቢው ተቆርቋሪ ግለሰቦችና ሀገር ወዳድ የበጐ አድራጐት ማህበራት ብቻ ናቸው::
እነዚሁ አካላት በየአመቱ በማሽን ጭምር እየታገዙ በዘመቻ ከማጽዳት ያልቦዘኑ ቢሆንም የእምቦጭ ጉዳይ ዛሬም “ውሀ ቢወቅጡት ቦጭ” ከመሆን አልዘለለም:: የእስካሁኑ ልፋት ሁሉ ውጤት አለማስገኘቱንም በመከላከሉ ተግባር ላይ የተሠማሩት ባለሙያዎች ይናገራሉ::
ይህን ያስተዋለው የክልሉ መንግስት ደግሞ ጉዳዩን በባለቤትነት የሚመራ ራሱን የቻለ ተቋም እንደሚያስፈልግ በማመን በቅርቡ “የጣና እና ሌሎች የውሀ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጄንሲን” አቋቁሟል::
ለመሆኑ አዲሱ ተቋም የተሰጠውን ተልእኮ ለማሳካት ምን ያህል ዝግጁ ነው? እስካሁን የነበረው አፈፃፀም እንዴት ተገመገመ? ምን ጐደለ? ምንስ ታሰበ? በሚሉት ዙሪያ አማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ሰሞኑን የጉዳዩን ባለቤቶችና አጋር አካላት በአንድ መድረክ አገናኝቶ አወያይቷል::
ተወያዮቹ “የችግሮችን መፍትሄ ለማግኘት መንስኤውን መረዳት ወሳኝ ነው” ካሉ በኋላ እምቦጭ ወደጣና ሀይቅ እንዴት መጣ?” የሚለውን ጥያቄ የመጀመሪያው መወያያ ርዕስ አድርገዋል::

እምቦጭ ወደጣና እንዴት መጣ?
የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ፣ መሬት አስተዳደርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር በላይነህ አየለ ከ2003 ጀምሮ በጣና ሀይቅ ሰሜናዊ ምስራቅ ስለተከሰተው እምቦጭ አመጣጥ መስሪያ ቤታቸው ሦስት መላ ምቶችን እንዳስቀመጠ ጠቁመዋል:: መላምቶቹም አንደኛው ከመካከለኛው ምስራቅ ኤዥያ በቀይ ባህር በኩል ወደ ጣና የሚሰደዱ ወፎች አመጡት የሚል ሲሆን ሁለተኛው በአሣ ማጥመጃ መረብ መጥቶ ሊሆን ይችላል፤ ሦስተኛው ደግሞ እምቦጭ በአሜሪካ ግዛቶች ለጌጣጌጥነት የሚጠቀሙበት የቤት ውስጥ አበባ በመሆኑ ይህን ያዩ ሰዎች ዘሩን ከውጭ አምጥተው ለቤታቸው ሲጠቀሙ አምልጦ ወደ ጣና ሊገባ ይችላል የሚሉ መሆናቸውን ገልጸዋል:: ጣናን ከጥቅም ውጪ በማድረግ አማራ ክልልን መጉዳት የሚፈልግ አካል ዘሩን አምጥቶ ሊበትንበት ይችላል የሚል አራተኛ መላምት እንደሚኖርም ተናግረዋል::
ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር በላይነህ ካቀረቧቸው አራት መላምቶች በተጨማሪም ለኢንዱስትሪዎች ፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያነት የመጣ ነው፤ ከእርሻ መሣሪያዎች ጋር የመጣ ሊሆን ይችላል፤ የቁጥጥርና ክትትል ስርአት ባልተዘረጋለት የቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴአችን ሳቢያ የገባ ነው… የሚሉ መላምቶች ከውይይቱ ተሳታፊዎች ቀርበዋል::
በዘመናዊ አሣ እርባታ የተሠማሩት እና እምቦጭን በሀገር በቀል ዘዴ ለመከላከል ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት አቶ ብርሃኑ ውብነህ ደግሞ “ከቀረቡት መላምቶች መካከል ብዙዎቹ አያሳምኑኝም” ብለዋል::

Image may contain: outdoor and nature

ለምሳሌ መረብ የተባለው ጣና ላይ አገልግሎት የሚሰጠው መረብ ሁሉ አንድም ከሱዳን ታሽጐ የሚመጣ አልያም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራ አዲስ መረብ በመሆኑ እምቦጭን ሊያመጣ አይችልም ብለዋል:: አረሙ በስደተኛ አእዋፍ የመጣ ቢሆን ኖሮ ደግሞ ወፎቹ በሚያርፉበት የጣና ስነምህዳር ሁሉ ይከሰት ነበር በማለት ከሁሉም መላምቶች የሚያመዝነው ሀይቁ እንዲጐዳ የፈለገ የሆነ አካል አምጥቶ እንዲላመድ አድርጐታል የሚለው ነው:: በተለይ ደግሞ አረሙ ቀድሞ የተከሰተበት መገጭ ከአርሶ አደሩ መኖሪያ ራቅ ስለሚልና በቅርብ የሚያይ ሰው የሌለ በመሆኑ ሆን ተብሎ ለመተከሉ ማሳያ ነው ብለዋል::
ከገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ የተገኙት ምክልት ቢሮ ኃላፊው አቶ መለሰ ዳምጤ በበኩላቸው የመገጭ ሰራቫ ግድብ “የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፖለቲክስ” ያለበትና ባለፉት ዓመታት የተጀመሩት የመስኖ ግድቦቻችን በሙሉ እየተጓተቱ ሥራ ሳይጀምሩ ከመቆየታቸው በዚያ አካባቢ እምቦጭ ቀድሞ ከመከሰቱ ጋር ተደምሮ ሲታይ አረሙ ሆን ተብሎ የመተከሉን መላምት ያጠናክረዋል ነው ያሉት::
አቶ መዝገቡ ዳኘው የተባሉ የውይይቱ ተሳታፊም ጣና የአማራ መታወቂያ እንደመሆኑ የአማራ ጠል ሀይሎች ሆን ብለው አምጥተውታል የሚለው መላምት እንደሚያምዝንባቸው ተናግረዋል::

የእምቦጭ ሽፋን ምን ያህል ነው?
የቢሮ ኃላፊው ዶ/ር በላይነህ “በ2009 ወደ መሬት አስተዳደር ተቋም ስገባ 40 ሺህ፣ 50 ሺህ እና 24 ሺህ ሄክታር መሬት በአምቦጭ መወረሩን የሚገልፁ ሪፖርቶች አግኝቻለሁ” ካሉ በኋላ “እርግጠኛ ሆነን የምንናገረው በምስራቅና ምዕራብ ደንቢያ፣ በጐንደር ዙሪያ፣ በሊቦ፣ ፎገራ እና ደራ ወረዳዎች የተከሰተ መሆኑን ነው” ሲሉ አስረድተዋል::
“መጠኑን በመደበቅ መፍትሄ ስለማይገኝ ተክክለኛው በገለልተኛ ወገን እንዲለካ እንፈልጋለን:: ይሁን እንጂ እምቦጩ በሀይቁ ነፋስ ምክንያት ስለሚንቀሳቀስና ቋሚ ስላልሆነ ያወዛግባል:: ስለዚህ ለእቅድ መነሻ የምንጠቀምበት ሀይቁ በተረጋጋበት ሰአት መስከረም ወር ላይ በ22ቱም ቀበሌዎች የሚለካውን ነው:: የጂፒኤሱ ውጤትም አለማቀፍ እውቅና ካለው ሳተላይት ጋር ይመሳከራል” ሲሉም አክለዋል::
አዲስ የተቋቋመውን ኤጄንሲ የሚመሩት ዶ/ር አያሌው ወንዴ በበኩላቸው የአለካኩ ዘዴ ችግር ስላለበት በየዓመቱ ተመሳሳይ ቁጥር እንደሚታይ ገልፀው አረሙ ተንቀሳቃሽ በመሆኑ በየሄደበት የሚጥለው ቅርንጫፍ ሁሉ ግምት ውስጥ ስለማይገባ አሁን ድረስ በአለካኩ ላይ ስምምነት እንደሌለ ነው የተናገሩት::
ባለፉት ስምንት ዓመታት በየወረዳው የሚላከው መረጃ የተሳሳተ እንደነበር የገለጹት ዶ/ር አያሌው “የሚገለፀው ሪፖርትም ቀልድ ነው” ነው ያሉት::
ዶ/ር በላይነህ ግን ቢሯቸው የተቋቋመው እምቦጭን ለመከላከል እንዳልሆነና በተደራቢነት የሚሰራው ተግባር መሆኑን ጠቅሰው ሪፖርታቸው ትክክል አይደለም የሚል ካለ በማሳያ ውድቅ ማድረግ ይገባዋል በሚል ሞግተዋል::
የዶ/ር አያሌውን ትችት ደግፈው ማሳያ በማቅረብ የሞገቱት አቶ ብርሃኑ ውብነህ ደግሞ ትረስት ፈንዱ ከተቋቋመ ከ2010 ጀምሮ አካባቢ ጥበቃ አስወገድኩ እያለ የሚገልፀው ቁጥር ትክክል እንዳልነበር ጠቁመው እንደአብነት ቢሮው በናበጋ የነበረን እንቦጭ ሙሉ ለሙሉ አስወግዶ ሽፋኑን ዜሮ እንዳደረሰ ገልጾ ነበር:: በዚያን እለት የናባጋ አርሶ አደሮች ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በእምቦጭ እንደተወረረ ነበር፤ ጉዳዩንም ለአማራ ቴሌቪዥን በአካል አሳይተናል:: አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ግን ሽፋኑን ቀንሶ እየገለፀ እምቦጭን ፖለቲካዊ አድርጐት ነበር ብለዋል::
የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጥላዬ ተክለወልድ በበኩላቸው በአምቦጩ አለካክ ላይ ብቸኛ ዘዴ ላይኖር እንደሚችል ጠቁመው ጂፒኤስን፣ ሳተላይትን፣ ድሮንን እና መሰል ቴክኒዮሎጂዎችን የሚጠቀም ወጥ አሠራር አስቀምጦ በተቀናጀ መንገድ መሥራት ችግሩን እንደሚፈታው ያላቸውን ሀሳብ ሰጥተዋል::

እምቦጭን ማጥፋት ይቻላልን?
የአዲሱ ኤጀንሲ ኃላፊ ዶ/ር አያሌው “አዎ! ልናጠፋው እንችላለን” ሲሉ ስራውን በኃላፊነት ሲመሩት የቆዩት ዶ/ር በላይነህ ግን “እስካሁን እምቦጭ በተከሰተበት ሁሉ ሲጠፋ አላየሁም፤ አላነበብኩምም:: ስለዚህ መካላከል እንጂ ማጥፋት አይቻልም” ብለዋል::
አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው እስካሁን አረሙን እንዳይጠፋ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ “አረሙን ማጥፋት አይቻልም” የሚለው እሳቤ ነው:: ወደፊትም “አይቻልም” ከሚል አስተሳሰብ ወጥቶ “ይቻላል” ወደሚል መሸጋገሩ ጥሩ ነው፤ አረሙ በሳይንሳዊ መንገድ ማጥፋት ባይቻል እንኳ አገር በቀል የመከላከል ዘዴዎች በመጠቀም እምቦጭን ማጥፋት በሚችሉ ተፈጥሯዊ የሣር ዝርያዎች እንዲወገድ ማድረግ እንደሚቻል አብራርተዋል::
በመጨረሻም “በጋራ አቅደን በጋራ እየገመገምን እንሠራለን:: አይጠፋም ብሎ ከመነሳት ህዝባችንን ይዞ ለማጥፋት መስራት ይሻላል” ያሉት ዶ/ር አያሌው እምቦጭን 99 በመቶ ለማጽዳት አቅዶ መስራት በራሱ አርሶ አደሩን ማድከም በመሆኑ መቶ በመቶ ለማጽዳት አልሞ መነሳት አማራጭ የለውም” ብለዋል::

እስካሁን ምን ተዘየደ? ምንስ ፈየደ?
በጣና ላይ የተከሰተውን እምቦጭ ለመከላከል እንደየአካባቢው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ የሰው ኃይልን፣ ማሽኖችን፣ ስነ ህይወታዊ ዘዴዎችን፣ የተፈጥሮ ጠላቶችን፣ ኬሚካል እና ባህላዊ ዘዴዎችን መጠቀም እንደሚቻል ፍንጮች አሉ:: ይሁንና እስካሁን የተሞከሩት በሰው ጉልበት እና በማሽን ማጽዳት ብቻ ሲሆኑ ሌሎቹ ገና ከቤተ ሙከራ ያልወጡ መሆናቸውን ዶ/ር በላይነህ ተናግረዋል::
በማሽን የማጽዳቱ ተግባርም ገና በሙከራ ላይ ያለ ከመሆኑም በላይ ማሽኖቹም የሚያጭዱትን አረም የሚያጎጉዙበት እና ከሀይቁ የሚያስወጡበት ዘዴ ገና ያልተሠራላቸውና ወደብም ያልተገነባላቸው መሆኑ ተነግሯል::
ለማሽኖቹ የሚያስፈልገው ወጪ እና የሚሰጡት አገልግሎት ከኢኮኖሚ አንፃር አዋጭ ካለመሆኑ በላይ መለዋወጫ እስኪገኝላቸው የሚወስደው ጊዜ ርዝመትም በአርሶ አደሩ ጉልበት የሚካሄደውን የማጽዳት ሥራ ያዘናጋ ከመሆን ውጪ ውጤታማ እንዳልሆነም ዶ/ር አያሌው ጠቁመዋል::
በውይይቱ በቀጥታ ስልክ ገብተው አስተያየት የሰጡት ከወሎ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶ/ር አስማረ ደጀን በኬሚካል እምቦጭን ማጥፋት ይቻላል ቢሉም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ጌታቸው ኬሚካል እምቦጭን ቢያጠፋም ኬሚካሉን የሚያመርተው ካምፓኒ ኬሚካሉ ወደሀይቅ ፈጽሞ መለቀቅ እንደሌለበት ማስጠንቀቁን እንዳነበቡ ጠቅሰው ለሀይቁ ብዝሀ ህይወት ሲባል ሊለቀቅ አይገባም ሲሉ ሞግተዋል::
የእምቦጭ መከላከያ ናቸው የሚባሉ ዘዴዎችን ሁሉ በሙከራ ጣቢያዎች ላይ በመመርመር ላይ የሚገኙ ምሁራንም አቼቶ በ30 ደቂቃ ውስጥ አረሙን መቶ በመቶ እንደገደለ በኩሬ ላይ ሙከራ ማረጋገጣቸውንና የሣት እራት፣ ፈንገስ/ሻጋታ/ እና በአይን የማይታዩ ትላትሎች የእምቦጭ ተፈጥሯዊ ጠላቶች ስለመሆናቸው ፍንጭ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል:: ይሁንና ማንኛውም ዘዴ በቤተ ሙከራ ተረጋግጦ በቴክኒክ ኮሚቴ እስካልፀደቀ ድረስ ወደ ሐይቁ ስለማይለቀቅ ስጋት ሊገባን አይገባም ብለዋል::
ከዚሁ ከስነ ህይወታዊ መከላከል ዘዴ ጋር በተያያዘ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከውጪ ያስመጣቸውን ጢንዚዛዎች እስካሁን ወደ ስራ ያላስገባበት ምክንያት ተጠይቆ ዩኒቨርሲቲው ጢንዚዛዎችን አራብቶ እና በ10 የተለያዩ አካባቢዎች የጐንዮሽ ጉዳት የማያደርሱ መሆኑን አረጋግጦ ለሥራ ዝግጁ ያደረጋቸው ከስምንት ወራት በፊት መሆኑን አስታውቋል:: ለመዘግየቱ ምክንያት የሆነው የጢንዚዛዎቹ ማረፊያ ካምፕ ግንባታ በአራት ጣቢያዎች እየተዘጋጀ በመሆኑ እንደተጠናቀቀ ወደ ስራ ይገባሉ ተብሏል::
እምቦጭን በባህላዊ መንገድ ለማጥፋት የሚያስችል ዘዴ አለኝ ብለው የቀረቡት መሪጌታ በላይ “ከተለያዩ እጽዋት ያዘጋጁት ‘ኦርጋኒክ’ ቅመም እምቦጩን በ24 ሰአት የሚያደርቅና በብዝሀ ህይወቱ ላይ ጉዳት የማያደርስ፣ እንደ ቄጤማ፣ እንግጫና የመሳሰሉትን ለይቶ እየተወ እምቦጩን ብቻ የሚያጠፋ ‘ኬሚካል’ ያልሆነ መከላከያ ነው” ብለዋል:: መሪጌታ አያይዘውም እንዲህ አይነት አገር በቀል መፍትሔ ሲመጣ ፕሮፕዛል ቀርፀህ አምጣ፤ ጨርሰህ ስትመጣ እንገዛሀለን” የሚል ቢሮክራሲ የበዛበት ምላሽ መስጠት ተገቢ እንዳልሆነና ለአገር በቀል እውቀቶች መንግስት ቴክኒካዊ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል::
“እምቦጭን በሰው ኃይል እና በአነስተኛ አገር በቀል ቴክኖሎጂዎች እየታገዙ ማጥፋት ይቻላል” የሚሉት አቶ ብርሃኑ ለምሳሌ በውሀማ መሬቶች ዳርቻ ላይ የሚኖረው ህዝብ እምቦጭን የማጥፋት ተፈጥሯዊ አቅም ያላቸውን ሣሮች እንዲተክል እና እምቦጩን ሲያፀዳ የሚቀሩ ቁርጥራጮችን በመረብ ጠርጐ እንዲያስወግድ በማድረግ አረሙን ማጥፋት ይቻላል ብለዋል::

ምን ይበጃል?
እምቦጭን በመከላከሉ ተግባር አስካሁን በነበሩ ጥረቶችና ድክመቶች ላይ ጥልቅ ውይይት ያደረጉት ተሣታፊዎች ጣና ሀይቅ እምቦጭ ብቻ ሣይሆን በደለልም መሞላት፣ በፍሳሽ የመበከል እና ሥርአት ያልተዘረጋለት የአጠቃቀም ችግርም የተጋረጠበት በመሆኑ ለአንድ ተቋም ብቻ የማይተውና ከፌዴራል መንግስት ጀምሮ የሚመለከተው አካል ሁሉ ጊዜ ሳይሰጥ ተቀናጅቶ ሊታደገው የሚገባ መሆኑን ጠቁመዋል::
አረሙ ጣናን አልፎ አባይን እስከመውረር እየሄደበት ያለው ፈጥነት ከመከላከሉ ተግባር ጋር የተመጣጠነ ባለመሆኑ ሁሉንም የመከላከያ ዘዴዎችን አቀናጅቶ በመጠቀም መረባረብ አማራጭ የለውም ተብሏል::
ስለሆነም አራቱም ማሽኖች የሚያስፈልጓቸው መለዋወጫዎች፣ ወርክሾፓች፣ ወደቦችና ተጨማሪ መሣሪያዎች ተሟልተውላቸው የፈረስ ጉልበታቸው በሚፈቅደው ስነምህዳር ተሰማርተው እንዲያፀዱ ማድረግ ያስፈልጋል:: መፍትሔ ናቸው የተባሉ ግኝቶችን በሙከራ ጣቢያዎች የሚሞክሩ ተማራማሪዎችም በተለይ ኬሚካሎች ሾልከው እንዳይወጡና በሀይቁና ብዝህ ህይወቱ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ በፍጥነት ውጤታማነታቸው የተረጋገጠላቸውን ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቁሟል:: ለዚህም የሚመለከታቸው ሁሉ የጋራ እቅድና የክትትል ስልት ዘርግተው መሥራት እንዳለባቸው አምነዋል::
የጣና ሀይቅ ችግርን ለመፍታት ከተጀመረው ገና ያልተነካው ስለሚልቅ አካባቢውን በፓርክነት ከልሎ ስትራቴጂክ ዶክመንት እንዲዘጋጅለትና በሥርአት እንዲመራ፣ ለኤሌክትሪክ የሚለቀቀው ውሀም በዘፈቀደ መሆኑ እንዲቀርና በሀይቁ የሚገለገል ሁሉ ሀይቁን ከመታደግ አልፎ ለተገለገለበት የሚገባውን ክፍያ የሚፈጽምበት ሥርአት ሊዘረጋ እንደሚገባው ነው ተወያዮቹ ያሠመሩበት::

በኩር (ጌታቸው ፈንቴ) ህዳር 22 ቀን 2012 ዓ.ም ዕትም