ወጣቱ በዘርና በፖለቲካ ቢከፋፈልም ስራ አጥነትን ይጋራል።


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


DW : ግጭት ጠብ በቀጠለባት ኢትዮጵያ ወጣቱ በዘር እና በፖለቲካ ቢከፋፈልም አንድ ነገር ይጋራል። ስራ አጥነትን! ይህንን የወጣቱን ችግር ለመቅረፍ መንግስት ወጣቶችን እያደራጀ ብድር ቢሰጥም በርካታ ወጣቶች አሁን ድረስ የብድሩ ተጠቃሚ ሊሆኑ እና ከስራ አጥነት ሊላቀቁ አልቻሉም።

ኢትዮጵያ ውስጥ ወጣቶች በአንዳንድ ስፍራ በዘር እየተደራጁ፣ ሌላጋ ደግሞ በተናጣል ሆነዉ ዝርፍያ እና ስርቆት እያካሄዱ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል።እነዚሕ ወጣቶች ያሳደሩት ስጋትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ነዉ። በዘር እና በፖለቲካ የመከፋፈል ፈተና የገጠመው ወጣት በአሁኑ ሰዓትም እኩል የሚጋራው ስራ አጥነትን ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ  ከአራት ወር በፊት ለኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር ኢትዮጵያ ውስጥ የስራ አጡ ቁጥር ከ 11 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ገልጸው ነበር። ከነዚህም ስራ አጦች መካከል ሶስት ሚሊዮን ያህሉ ወጣቶች የስራ እድል እንዲያገኙ መንግስት አቅዶ ለመስራት መዘጋጀቱንም የ2012 ዓም በጀት ሲፀድቅ ይፋ ሆኗል።

ከዚህም በተጨማሪ  በርካታ ወጣቶችን  በልዩ ልዩ የስራ ዘርፎች አሰልጥኖ በ 2012 በጀት አመት 50,000 ስራ ፈላጊዎችን ወደ ዱባይ ለመካል እቅድ እንዳለም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። መንግሥት ወጣቱን የስራ እድል ለማሲያዝ ከሚጠቀመው ዘዴ አንዱ ወጣቶችን በጥቃቅን እና አነስተኛ አደራጅቶ ብድር የሚሰጥበት መንገድ ነው። በዚህ ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች ባይጠፉም አሰራሩ ብዙ ፈተናዎች እንደገጠሙት ነው ከዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዶቻችን የምንረዳው። ዶይቸ ቬለ DW ከወረባቦ ወረዳ ያነጋገራቸው ሁለት ወጣቶች እንደሚሉት ከሆነ ብድር ለማግኘት ከየቀበሌያቸው ተመልምለው ብድራቸውን ሲጠባበቁ 10ኛ ወራቸው ነው። « ያለንበት መጥተው መዘገቡን  ግን አንዱ ቆይ ዛሬ ሌላው ቆይ እከሌ የለም ሲመጣ ይላል። እስካሁን ድረስ የቁጠባም ደብተር አውጥተን አልተሰጠንም» ይላል 50 000 ብር ለመበደር የጠየቀው ወጣት ከበደ። ሌላው ወጣትም እንደሱ 50 000 ብር ለማግኘት እና ሱቅ ከፍቶ ለመደራጀት ሲጠባበቅ የቆየው አባተ ነው። « ካዝና ብር የለም ስለሌለ ነው ይሉናል።  የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሲሰጥ ነው ይህንን የጀመርነው። እስካሁን ድረስ አልተሰጠንም። ተስፋ ቆርጠን ትተንዋል።»

ስራ አጥነት በሌሎች የአፍሪቃ ሀገራትም ከፍተኛ ነው ስራ አጥነት በሌሎች የአፍሪቃ ሀገራትም ከፍተኛ ነው

አባተ እንደገለጸልን እሱ ከሚኖርበት ቀበሌ የተመለመሉት ዘጠኝ ወጣቶች ሲሆኑ ከነሱ መካከል ሶስቱ ገንዘቡን ባለማግኘታቸው ተማረው የስደቱን አለም ተቀላቅለዋል። እሱ በሚኖርበት ቀበሌ ያሉ ወጣቶች ከብት ለማደለብ ወይም ሱቅ ለመክፈት ብድሩን የጠየቁ ሲሆን እንደ ወጣቱ ከሆነ በነሱ በኩል የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልተዋል። « የቤተሰብ የይዞታ መሬት ደብተር አምጡ አሉን። አስያዝን ቤተሰብም ፈረመ። የእኛምንም መታወቂያ ፎቶ ኮፒ አስያዝን» ይላል አባተ። አባተ እና ከበደ የጠየቁት ገንዘብ መጨመሪያ ይሆነን እንደው ብለን ነው እንጂ ብዙ ሆኖ አይደለም ይላሉ። ምንም እንኳን 100 000 ብር ለመበደር ቢጠይቁም የተፈቀደላቸው ግማሹ ብቻ ነው። ይህንንም ገንዘብ የሚያገኙት ገና ሌሎች ብድራቸውን ሲመልሱ ነው። ከበደ ግን መስጠት ስላልፈለጉ ነው ሲል ነው የሚወቅሰው።

በክልል ደረጃ በአማራ ክልል ለወጣቶች ከተሰጠው የተዘዋዋሪ ብድር ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንዳልተመለሰ እና ከግማሽ ቢሊዮን የሚበልጠው ደግሞ አይመለስም የሚል ስጋት እንዳለበት አበዳሪ ተቋሙ ባለፈው ወር አስታውቆ ነበር። ይህም ስጋት በወረባቦ ወረዳ አለ። የወረባቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ካሊድ መሀመድ እንደገለፁልን ወረዳቸው በዘንድሮውም ይሁን ባለፈው ዓመት ከመንግስት የተለቀቀለት ገንዘብ የለም። እየተጠቀመ ያለው በ 2009 የተለቀቀለትን 13 ሚሊዮን ብር « የተዘዋዋሪ ፈንድ» ነው። በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች እንደ አባተ እና ከበደ ያሉት የወረዳው ወጣቶች የብድሩ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቀርተዋል። « 2009 የተለቀቀው ብር እየዞረ ነው የሚሄደው። ከዚህም ገንዘብ የተሰበሰበ አራት ሚሊዮን ብር አለ። ይህንን ገንዘብ ነው በስራ ላይ ያላዋልነው። ሌላው እንከን የገጠመን ቴክኒክ እና ሙያ እና አብቅቶ ተነጋግረው ነበር ምልመላውን ማድረግ የነበረባቸው። ይህም ክፍተት ፈጥሯል። ቴክኒክ እና ሙያ ሙያ ይመለምላል። አብቅቶ ደግሞ እነዚህ ብድሩን መመለስ አይችሉም የሚለው ነገር አለ»

የመንገድ ላይ ነጋዴ በደቡን አፍሪቃ የመንገድ ላይ ነጋዴ በደቡን አፍሪቃ

አቶ ሁሴን ሰይድ በወረባቦ ወረዳ ወጣቶችን የሚመለምለው የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ፅህፈት ቤት የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ቴክኖሎጂ ሽግግር የአቅም ግንባታ አደረጃጀት ባለሙያ ናቸው። ለወጣቶቹ ገንዘብ ያልተሰጠበት ምክንያት « ከአሁን በፊት የተሰጡት ብድሮች ሳይመለሱ በመቅረታቸው ነው።» ቀጣዩን ብድር ለመስጠት ደግሞ የተለያዩ አካላት መፈረም ስላለባቸው ነው ይላሉ። ወጣቶቹ ሌላም ወቀሳ አላቸው። አባተ ለእነሱ እንዲሰጥ የነበረው ብድር በዘመድ ለሌሎች ተበዳሪዎች ሊሰጥ ነበር የሚል እምነት አለው።  ይህንን አወቅሁ የሚለው ባለሙያዎች እና የብድር ተቀባዮች ዘንድ ብጥንጥ በተፈጠረበት ወቅት ነው። አቶ ሁሴን ግን እንደዚህ አይነት አሰራር የለም ሲሉ ያስተባብላሉ። አቶ ሁሴን እንደገለፁልን በድሕፈት ቤቱ መደራጀት ይገባቸዋል ተብለው ከገጠር እና ከከተማ የተለዩ ከ 6082 በላይ ስራ አጥ ወጣቶች በወረባቦ ሁሉም ቀበሌዎች ይገኛሉ። እድሜያቸው ከ 18 እስከ 34 ዓመት ነው።