የሕግ የበላይነትን በማስከበር በኩል ኢትዮጵያ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የዓለም አቀፍ ጥናት ጠቆመ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የሕግ የበላይነትን በማስከበር በኩል ኢትዮጵያ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የዓለም አቀፍ ጥናትን ጠቅሰው አንድ የሕግ ምሁር ተናገሩ፡፡

የሕግ የበላይነትን ማስከበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት በባሕር ዳር ተካሂዷል፡፡

Image may contain: 2 people, people sitting and indoor

(አብመድ) “የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ከእኛ ምን ይጠበቃል?” በሚል ርዕሰ በተካሄደው የምክክር መድረክ የሕግ የበላይነት በአማራ ክልል ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ በማንሳት ውይይት ተደርጓል፡፡ ቀጣይ መደረግ ስለሚገባቸው ተግባራትም የመፍትሔ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ወርቁ ያዜ በአማራ ክልል እየተስተዋለ ያለውን የሕግ ጥሰት አስመልክቶ መነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል። በክልሉ የሕግ የበላይነት አለመከበር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም አስታውቀዋል። በክልሉም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚስተዋለው የሕግ የበላይነት ጥሰት ከሀገሪቱ የማኅበራዊ፣ የኢኮሚ፣ የፖለቲካ እና የሕግ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ የሕግ የበላይነት አከባበርን አስመልክቶ በተሠራ ዓለም አቀፍ ጥናት መሠረትም ኢትዮጵያ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በጽሑፉ ተመላክቷል፡፡

በ2014 (እ.አ.አ) በተሠራ በዓለም አቀፍ ጥናት ከተካተቱት 99 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ 88ኛ ደረጃ ላይ ነበረች፡፡ በ2017/18 (እ.አ.አ) በተደረገ ጥናት ደግሞ ከ113 ሀገራት መካከል 107ኛ ደረጃ ላይ እንደነበረች በጥናቱ ተመላክቷል፡፡ የሕግ የበላይነት ጥሰት ፈጣን መፍትሔ የማይሰጠው ከሆነ የጎላ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም ገልጸዋል፡፡ሕግን ማስከበር የሁሉም ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ሚዛናዊ እና ምክንያታዊ ትውልድ ለመፍጠር ወላጆች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ብዙኃን መገናኛ እና የመንግሥት አካላት በታዳጊዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲስሩም አስገንዝበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የሕግ የበላይነት ጥሰት ከምንጊዜውም በላይ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም መነሻው ተውልዱ የተቃኘበት የፖለቲካ ሥርዓት ውጤት መሆኑን አስታውቀዋል። የሱስ ተጋላጭነት እየጨመረ መምጣት፣ችግሮችን እንደ ገቢ ምንጭ የሚጠቀሙ አካላት መኖር፣ የፖለቲካው ብልሽት እና ሌሎችም ለሕግ ጥሰቱ በምክንያትነት ተነስተዋል። የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ምሁራን እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ትውልዱን የማስተማር ማኅበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ተናግረዋል። መንግሥትም የሕግ የበላይነትን የማስከበር ድክመት እንዳለበት ገልጸው ቀጣይ ሀገር ወዳድና እውነተኛ ዜጋ ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ቀዳሚ ተግባሩ እንዲሆን ጠይቀዋል። የሕግ አስፈጻሚ አካላት ለሕግ የበላይነት ጥሰት የሚያደረጉ ነገሮችን ከምንጫቸው በማድረቅ ሕግ እና ሥርዓትን ማሰከበር እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል። ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር ውይይቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው አስተያዬት ሰጪዎች የተናገሩት።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ ኅብረተሰቡ ነገሮችን በጥሞና መመልከት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች ከቤተሰቦቻቸው ጀምሮ በቅርባቸው የሚገኙ ሰዎችን እንዲያስተምሩም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በወጣቶች የተጀማመሩ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስፋት ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ውይይቶቹ ቀጣይነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡