ትራምፕ እና አል ሲሲ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን ግድብ ዙሪያ መከሩ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


DW : የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የግብፁ አቻቸው አብደል ፈታህ አል ሲሲ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን ግድብ አስመልክቶ መነጋገራቸው ተዘገበ።

ትናንት ሁለቱ መሪዎች ዋሽንግተን ላይ ካካሄዱት ንግግር በኋላ ትራምፕ ግብፅ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ የሚያደርጉትን ድርድር እንደሚደግፉ መግለፃቸውን ኋይትሀውስ አመልክቷል።

የኋይትሃውስ ቃል አቀባይ ጄድ ዲሪ የሰጡትን መግለጫ የጠቀሰው የሮይተርስ ዘገባ እንዳመለከተው ፕሬዝደንት ትራምፕ በሦስቱ ሃገራት መካከል የሚካሄደው ውይይት የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርስ ድጋፋቸውን ከመግለፃቸው ውጭ ዋሽንግተን ላይ ይካሄዳል ስለተባለው የጋራ ውይይት የጠቀሱት ነገር የለም።

ባለፈው ሳምንት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የትራምፕ አስተዳደር ሦስቱን ሃገራት በጉዳዩ ላይ እንዲወያዩ ለነገ ወደዋሽንግተን መጋበዙን ገልፀው ነበር። ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው የኃይል ማመንጫ ግድብ የውኃ ፍሰቱን ይቀንስብኛል የሚል ስጋት የምታሰማው ግብፅ በተደጋጋሚ በጉዳዩ ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንዲገባ ስትጠይቅ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ የሦስተኛ ወገን አደራዳሪነትን እንደማትቀበል ብታስታውቅም ባለፈው ሳምንት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነገ ይካሄዳል በተባለው ውይይት ኢትዮጵያም እንደምትሳተፍ አስታውቀዋል።