የጤና መድህን ረቂቅ አዋጁ የፌዴራል ሥርአቱን ታሳቢ አላደረገም የሚል ወቀሳ ቀረበበት

መረጃ ቲቪን ሰብስክራይብ በማድረግ ወቅታዊ ዜናዎችን፣ ትንተናዎችን፣ የኪነጥበብ ፕሮግራሞችን እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ማግኘት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

DW : ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣው የጤና አገልግሎት ወጪ በተለይ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ አላደረገም በሚል በስፋት ይነገርለታል። የጤና  አገልግሎቱን ችግር ለመቅረፍ በሚል መንግስት በቅርቡ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አዋጅ ለማውጣት በጤና መድህን ኤጄንሲና ሌሎች ባለድርሻ ከተባሉ አካላት ጋር በመሆን ውይይት ሲያደርግበት ቆይቷል። በተለየ ሁኔታ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን ፣ የአነስተኛ ንግድ አገልግሎት አንቀሳቃሾችን ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ወገኖችና ሌሎች የራሳቸው ገቢ የሌላቸውን ወገኖች ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለለት ረቂቅ አዋጁ በተለይ ከኦሮሚያ ክልል በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል።

አዋጁ ለጤና መድህኑ ሲባል የሚሰበሰበው ሃብት በሚተዳደርበት ሁኔታ ላይ የክልሎችን ሚና ለፌደራል ኤጀንሲው ሰጥቷል በማለት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የአንድ ዞን የጤና መድህን አስተባባሪ ለዶቸ ቨሌ ተናግረዋል።

«አዋጁ የሚለው ፤ የክልል ስልጣን እንዳለ ይጥሳል፣ብር ሰብስቡና  እንዳለ ወደ ላይ ወስደን እኛ እናስተዳድራለን ፣ ለጤና ተቋማት እና ነን የምንከፍለው ፣ ክልል ግን አባል ማፍራት ብቻ ነው የሚለው።»

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ አምስት ላይ የተጠቀሰው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ቋት ምስረታ በመደበኛው አሰራራችን ላይ ብቻ ሳይሆን በፌዴራል ስረአቱ ያልተማከለ አስተዳደር ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር ነው የሚሉት ደግሞ በኦሮሚያ ጤና ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አስተባባሪ አቶ ዲንቃ ኢረና ናቸው።

Symbolbild Herzschlag Herz EKG Stethoskop (Fotolia/M&S Fotodesign) « ይህ የወጣው ረቂቅ አዋጅ በፌዴራል ስረአቱ ውስጥ ለክልሎች የተሰጠውን ስልጣን ይጋፋል ፤ ያሳንሳል ፤ እንዲሁም የህዝቦችን መብት ይገፋል።»

«ገንዘቡን ሰብስባችሁ ማእከል ወዳለ ቋት ታስገባላችሁ ፤ ከዚያም የፌዴራል ኤጄንሲው ነው የሚያስተዳስድረው ብለው አንስተውልን ነበር ፤ አዋጅ መውጣቱ በራሱ ችግር የለውም ። ነገር ግን ከአርሶ አደር እጅ ሳንቲም በመሰብሰብ ከክልል አልፎ ወደ ፌዴራል መስጠት  እርስ በርሱ የሚጣረሱ ነገሮችን ይዟል፤ ህዝቡም እየተቃወመው ነው።»

በኢትዮጵያ በሶስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ጥቂት ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ከተጀመረ አስር አመታት ገደማ ያስቆጠረው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተገልጋዩ ህብረተሰብ በርቀት ላይ መገኘቱ ታሳቢ መሆን አለበት ይላሉ አቶ ዲንቃ። አገልግሎቱንም የሚያቀርቡት የጤና ተቋማት በተመሳሳይ ከፌዴራል መስሪያ ቤቱ ርቀው መገኘታቸው ወደ ተማከለ የጤና መድህን ሃብት አስተዳደር ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ውጤት አይኖረውም ይላሉ።

«የሚሰጠው አገልግሎት ከሰማኒያ አራት ከመቶ በላይ በአካባቢው ባሉ የጤና ጣቢያዎች ነው። እኛ ባሳለፍናቸው አስር አመታት ውስጥ አገልግሎት ያቀረብነውና ህዝቡም በአግባቡ የተጠቀመው በእነዚሁ ጤና ጣቢያዎች በመሆኑና ጤና ጣቢያዎቹ በርቀት ላይ እንደመገኘታቸው አዋጁ የመልካም አስተዳደር ችግር ይዞባቸው ሊመጣ ይችላል።»

Karte von Äthiopien (AP GraphicsBank/DW)

በረቂቅ ደረጃ ላይ የሚገኘው የጤና መድህን አዋጁ በውይይት የተገኙ ግብአቶችን በመጠቀም መሻሻል የሚገባቸውን ማሻሻል የሚከለክለን ነገር የለም ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ይመር ናቸው። ነገር ግን እንደ አቶ መሃመድ ገለጻ በሀገሪቱ የሚገኙትን ሁሉንም ክልሎችና ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች በውይይት አሳትፏል የተባለለት የረቂቅ አዋጁ ተቃውሞ የገጠመው ከኦሮሚያ ክልል ብቻ እንደሆነ ነው።

«ያዘጋጀነውን ረቂቅ ለማጸደቅ የህብረተሰቡን ይሁንታ ማግኘት ስላለበት ፤ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዘጠኙም ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች አወያይተና። ዋናው አላማውም ግብአት ማሰባሰብ ነው። ይህ አዋጅ ይጠቅመናል አይጠቅመንም ፣ ያሰራናል አያሰራንም ያላቸውን አስታያየቶች መቀበልና ማስተካከል ስለሆነ በሰጡን አስተያየት መሰረት ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን ከህጉ ጋር የሚሄዱ ጉዳዮችን እና እኛም ያላየናቸው ጉዳዮች ካሉ ለማካተት ነው።»

«ከሌሎች ክልሎች ምንም የገጠመን ችግር የለም። ከኦሮሚያ ክልልም የተነሳውም ቢሆን የሚመስላቸውን ሊያነሱ ይችላሉ። ያንን ሃሳብ የሚጠቅም ከሆነ የሚካተት ነው የሚሆነው።

ዳይሬክተሩ አቶ መሃመድ ለዶቼ ቬሌ እንዳስረዱት ከሆነ ሲመከርበት የነበረው የጤና መድህን አዋጁ ተጨማሪ ግብአት በማሰባሰብ ከሁለት ወራት በኋላ ጸድቆ ወደ ትግበራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።