" /> ኢህአዴግ፤ ወደ ዉህደት ወይስ ክስመት? – ዉይይት | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

ኢህአዴግ፤ ወደ ዉህደት ወይስ ክስመት? – ዉይይት

ዉይይት፤ ኢህአዴግ፤ ወደ ዉህደት ወይስ ክስመት? DW

ተወያዮች ካነስዋቸዉ ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል!

«ህወሃት ዉህደቱን እንደማይቀበለዉ ገልጾአል። ጭራሽም ዉህደቱን አላዉቅም ብሎአል። ወደድንም ጠላንም ህወሃት በትግራይ እስካሁን በነበረዉ የዴሞክራሲ ችግር ምክንያት ሌሎች ተቀናቃኝ ፓርቲዎች በሌሉበት በክልሉ ሕዝቡን ወክሎ ይገኛል። ሕዝቡም ቢሆን በሃገር ፖለቲካ ደረጃ ይወክለኛል ብሎ የሚያስበዉ ህወሃትን ነዉ። ስለዚህ ዉህደቱን አልቀበልም ያለዉን ህወሃትን አቅልሎ ማየት የትግራይን ሕዝብ ድምፅ ከቁጥር ዉጭ አድርጎ ማሰብ ነዉ። ይህ ደግሞ ሃገሪቱ ካለችበት ችግር በላይ ሌላ ችግር መፍጠር ነዉ። 27 ዓመት ስልጣን ላይ የነበረዉ ኃይል ብለን ስናነሳ፤ ያንን ኃይል አሳንሰን ማየት የለብንም እወክለዋለሁ የሚል ሕዝብም አለ። »

«ኢህአዴግ ይዋሃድ የሚለዉ ጉዳይ እስከ ብሔራዊ ምርጫ ካለዉ ጊዜ አንጻር አግባብ ነዉ ማለት አይቻልም፤ ጊዜዉን የጠበቀ አይደለም። » ምርጫዉ ሊካሄድ የቀረዉ 7 ወር ገደማ ነዉ» አዲስ ይመሰረታል የተባለዉ ዉህድ ፓርቲ አራቱ እህትማማች ፓርቲዎች ያላቸዉን ጥያቄ በምን አይነት መልኩ ነዉ የሚመልሰዉ? ፓርቲዎቹ ይዘዉት የሚቀርቡት ጥያቄ በምንም አይነት መልኩ በመካከላቸዉ አስታራቂ አግባቢ ነጥብ ያለ ይመስልም። ይህ ጥያቄ በትክክል መልስ ሳያገኝ እና መግባባት ላይ ሳይደረስ ተዋህዶ ለምርጫ መቅረብ አስቸጋሪ ነዉ የሚሆነዉ »

«ዉህደቱ የኢትዮጵያን ችግር አይፈተም ማለት አይቻልም። ዋናዉ ጥያቄ ዉህደቱ ጊዜዉን የጠበቀ ነዉ ወይ? የሚለዉ ነጥብ ነዉ። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ምርጫን አስታኮ አደረጃጀቱን ቢቀይር ሊገርመን አይገባም ። ይህ ርምጃ ለዉጥ ለማምጣት ታሪክ ለመስራት ነዉ።»

«በኢህአዴግ አደረጃጀት ሃገሪቱ ወደ ቀዉስ ገብታ ፤ የኤኮነሚዋ በከፍተኛ ሁኔታ ተንኮታኩቶ ፤ የኑሮ ዉድነት ጣርያ የደረሰበት ደረጃ ላይ እንገኛለን። ስለዚህ ለሕዝቡ ጥያቄ መልስ መስጠት የግድ ነዉ። የለዉጡ ኃይላት የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፤ በምርጫ ቦርድ ላይ ለዉጥ በማድረግ ፤ መልስ እየሰጡ መሆኑ ማሳያ ነዉ። አሁን ደግሞ የፖርቲ ለዉጥ ማድረግ አስፈላጊ ነዉ።»

«ኢህአዴግ የሚባለዉ በህወሃት ይዘወር የነበረዉ ፓርቲ፤ ይህንን ሃገር ከፋፍሎ ዉድቀት አፋፍ ላይ አድርሶታል። እሱን ይዞ መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ስለተደረሰ፤ የግድ እነኝህ ለዉጡን የሚመሩ ኃይሎች አዲስ የፓርቲ አደረጃጀት ለዉጥ ማምጣት አለባቸዉ» «ለትጥቅ ትግል ተብሎ የተመሰረተዉ ግንባር ፓርቲ ለ 28 ዓመታት ወደ ፖለቲካ ስራ ሳይዛወር በዝያዉ የትግል አስተሳሰብ ላይ ነዉ የቆየዉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እሱን ይዘዉ ሃገሪቱ ወደ ዲሞክራሲ በምታደርገዉ ሽግግር ላይ መጓዝ አይችሉም። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ለፓርቲዉ መከፋፈል ዋናዉ ምክንያት የዴሞክራሲ መዋቅር ስለሌለዉ ነዉ።»


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV