" /> በቃ!!! ዐቢይም ሆነ ተስፋ ያደረግንባቸው የለውጥ አመራሮች አልቻሉም።-ጋዜጠኛ ደረጀ ሀ/ወልድ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

በቃ!!! ዐቢይም ሆነ ተስፋ ያደረግንባቸው የለውጥ አመራሮች አልቻሉም።-ጋዜጠኛ ደረጀ ሀ/ወልድ

በቃ!!! – ጋዜጠኛ ደረጀ ሀ/ወልድ

በለውጡ አመራሮች ሙሉ እምነት አሳድሬ በሙሉ ልቤ ስደግፋቸው ቆይቻለሁ። የዐቢይ አሕመድን የመጀመሪያ የፓርላማ ቀናት ንግግር ሥሰማ አልቅሻለሁ። በለማ መገርሳ “ኢትዮጵያዊነት ሡስ ነው” ንግግር እንባዬን ረጭቻለሁ። “እግዚአብሔር ኢትዮጵያ መከራዋን በቃሽ ሊላት ነው” በሚል ተስፋና ደስታ ለተደጋጋሚ ሌሊቶች አምላኬን አመስግኛለሁ።
ዐቢይ ወደ አውሮፓ ባቀናበት ወቅትም በደስታ ተሞልቼ ከአምስተርዳም-በርሊን ድረስ ተጉዤ ተቀብዬዋለሁ።

ከቡራዮ እና ለገጣፎ ጀምሮ የለውጡ ተስፋ በጽንፈኞች እየደበዘዘ ፣ነገሮች ባልተጠበቀ ፍጥነት እየደፈረሱ እና እየተበላሹ መምጣት በጀመሩበት ጊዜ እንኳ፤ ዘመን ተሻጋሪ የሚመስሉ አንዳንድ ጥረቶቹን በማዬት ጊዜ ልንሰጠው ይገባል ብዬ ሽንጤን ገትሬ ተሟግቼለታለሁ።

“ለኢትዮጵያ ስንል ከነ ችግሩም ቢሆን ልንደግፈው የሚገባ መሪ ነው” በማለት በያዝኩት የጸና አቋም ምክንያትም፤ ከሩቅም፣ከቅርብም፣ከወዳጆቼም፣ከደጋፊዎቼም፣ ክፉኛ ተነቅፌያለሁ። ተዘልፌያለሁ። መስቃ ተሸክሜ ቆይቻለሁ። ይህን ሁሉ ያደረኩት ግን ለሀገሬ ስል እንጂ ለማንም ስል ስላልሆነ -ባደረኩት ነገር አልቆጭም። ምናልባት እቆጭ የነበረው፤ ምንም በጎ ድጋፍ አድርጌ ሳልሞክረው እንዲሁ ብቃወመው ነበር።

ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጬው እንዲሉ ሎሬት። አሁን ግን “ለውጥ”በሚባለው ቀልድ ላይ ያለኝን ሃሳብና አቋም ቀይሬያለሁ። የገባነው ወደ ለውጥ ሳይሆን ወደ መራራ ትግል መሆኑን ተረድቻለሁ።
ይህም ሆኖ “ዐቢይ አልቻለም” እንጂ “ዐቢይ አታሉኛል” ብዬ ማሰብ አልፈልግም። ለነገሩ እንደፈለግኩ ባስብም፤ አሁን በያዝኩት አቋም ላይ ለውጥ አይኖረውም። የያዝኩት አቋሜም፤ ተባብሮ እና አስተባብሮ ጠንካራ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ነው።

አዎ፣ ዐቢይም ሆነ ተስፋ ያደረግንባቸው የለውጥ አመራሮች አልቻሉም። አሁን የሀገሪቱ መሪ፣አድራጊና ፈጣሪ እነ ማን እንደሆነ በሚገባ ግልጽ ሆኗል። በጋራ የተገኘውን ድል በመስረቅ “ሕወሓትን ብቻዬን ነው” የሸኘሁት” እያለ የሚቦተረፈው ኦህዴድ – ከሕወሓት የቀሰመውን አገዛዝ ለማስቀጠል ቋምጦ ተነስቷል። አብዷል። “ለውጡ የኔ ብቻ ነው” የሚለው ትርክትም የተፈለገው ለዝርፊያ አገዛዝ እንዲያመቼው መሆኑ ግልጽ ነው።

መዥገሮች ሙሉ ሰውነቱ ላይ አርፈው ደሙን ሲመጡት የነበረ በሬ ከሰውነቱ ላይ መዥገሮቹን ሲያነሱለት፦” ተዋቸው፤ አታንሷቸው። እነዚህ መጠውኝ፣መጠውኝ ጠግበዋል። ከዚህ በላይ ምንም አያረጉኝም። አሁን እነሱ ሢነሱ ግን ሌሎች የተራቡ ስግብግቦች መጥተው ይሰፍሩብኝና ከነ ህይወቴ ያጠፉኛል” አላቸው ይባላል።

አዎ፣ ሕወሓት ተሸኜ ቢባልም ፤ለመዝረፍና ለመርገጥ የቋመጡ ስግብግቦችና በቀለኞች ፣ በጥላቻ የተሞሉና በዘረኝነት ስካር አቅላቸውን የሳቱ የሥልጣን ራብተኞች አሁንም ወንበሩን ተቆጣጥረውታል። ያለኝ ብቸኛ አማራጭ ፤ እነዚህን ኃይሎች ከሕዝቤ ጋር ሆኜ መታገል ብቻ ነው።
መጽሐፍ “እርፍ ይዞ ማንም ወደ ኋላ የሚያይ የለም” እንዲል፤ ከእንግዲህ በምንም እና በማንም ወደ ኋላ የምናይበት ጊዜ አክትሟል።

በቃ!!!

ጋዜጠኛ ደረጀ ሀ/ወልድ


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV