በአዲስ አበባ በጥቅም በተሳሰረ አሻጥር ህገ ወጥ የመሬት ወረራ ተባብሷል ተባለ

በመዲናዋ በጥቅም በተሳሰረ አሻጥር ህገ ወጥ የመሬት ወረራ ተባብሷል- አስተያየት ሰጪዎች

 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በጥቅም በተሳሰረ አሻጥር ህገ ወጥ የመሬት ወረራ ተባብሷል አሉ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች።

በመዲናዋ ክፍት ቦታዎች ለአረንገዴ ስፍራነት የቀሩትን ጭምሮ በህገ ወጦች እየታጠሩ መሆኑን እና አንዳንድ ስፍራዎች ደግሞ ግንባታ እየተካሄደባቸው መሆኑን ጭምር ታዝበናል ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ።

ነዋሪዎች ታዘብን እንደሚሉት ከማጠር እስከ ህጋዊ ካርታ መስራት በጥቅም የተሰናሰሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ያሉበት ነው፤ ችግሩን ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላትም ጥረታቸው ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ 1 ምክትል ዋና ስራ አስፍጻሚ አቶ አማን ገብረሚካኤል ፥የመሬት ወረራው መኖሩን ያምናሉ፤ ወረዳው ሰፊ አካባቢን የያዘ በመሆኑ ለቁጥጥር ቢያዳግትም ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ከወረዳው ደምብ ማስከበር አገልገሎት ዘርፍ የተቃርኖ ሀሳብ ይደመጣል፤ የስራ ሂደቱ ተወካይ ሰላም ስለሺ፥ በወረዳው ያሉ ክፍት ቦታዎች መሬት ባንክ የገቡትን ጨምሮ የተደራጁ ወጣቶች
በእንጨትም በቆርቆሮም እያጠሩ ለማስቆም ቢሞከርም ከባድ ሆኖብናል ይላሉ።

ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ቀድሞ የመንግስት የነበሩ ይዞታዎችን አጥረው ለማፍረስ ሲኬድ ህጋዊ ፈቃድ ወይም ካርታ ይዘው መጠበቃቸው ነው፤ ሌላው ደግም ድርጊቱን ለማስቆም በሚሞከርበት ጊዜ ስለታም ነገሮችን ይዘው ያስፈራራሉ ብለዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ የይዞታ አስተዳደደር ጽህፈት ቤት ሃላፊው አቶ ሰምበቶ ገለቶ በበኩላቸው፥ ሰነድ አልባ ይዞታዎች በመፈተሽ ህጋዊ የማድረግ፤ ስም ዝውውርና ሌሎች አገልግሎቶችን እንሰጣለን እንጅ በህገ ወጥነት ቢታጠሩም ህጋዊ አላደረግንም ይላሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽህፈት ቤት በመዲናዋ ህገወጥ የመሬት ወረራ መኖሩን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከወትሮ የተለየ አይደለም የሚሉት የጽህፈት ቤቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ቢቂላ፥ እርምጃ ወሰድን ቢሉም ሲገነቡና ሲያጥሩ ከማፍረስ የዘለለ አይደለም።

የአዲስ አበባ ከተማ አስትዳደር ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እንደሚለው አሁን ያለው መሬትን የመውረር ድርጊቱ እየተባባሰ ነው።

ኮልፌ ቀራኒዮ ፣ ቦሌ፣ ነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማና ሌሎችም የአዲስ አበባ ማስፋፊያ አካባቢዎች ችግሩ ተስፋፍቶባቸዋል።

ቡድኖችና ግለሰቦች በጦር መሳሪያ ታግዘው ሌሊትም ጭምር መሬት እያጠሩ በመሆኑ ከባድ ሆኖብናል ሲሉ በቢሮው የደምብ መተላለፍ ክትትል ቁጥጥርና እርምጃ አወሳሰድ ዳይሬክተሩ አቶ እዮብ ከበደ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ቤት የተቸገሩትና መሬት ያስፈለጋቸው ሳይሆኑ መሬትን እየወረሩ ያሉት ባለሀብቶች፣ በተቋማቱ ያሉ የመንግስ የስራ ሃለፊዎችና ደላሎች ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፥ መመሪያዎች እየተሻሻሉ ቀድሞ ህገ ወጥ የነበሩት ህጋዊ
መሆናቸውም ለመባባሱ ምክንያት ናቸው ብለዋል።

በመዲናቸን ያለው ህግን የጣሰ የመሬት ወረራ ከደምብ ማስከበር አቅም በላይ ነው የሚሉት አቶ እዮብ ከበደ
ጠንካራ ውሳኔና እርምጃ እንደሚያስፈልግ አስምረዋል።