በመጪው የ2012 ዘመን መለወጫ በዓል የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዥቅን ለመቀነስ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዥቅን ለመቀነስ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

በመጪው የ2012 ዘመን መለወጫ በዓል የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዥቅን ለመቀነስ፤ ከተከሰተም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በአገር አቀፍ ደረጃ ዝግጅት የተደረገ መሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡

የኃይል መቆራረጥ ዜሮ ማድረግ ባይቻልም የመቆራረጥ ሁኔታን ለመቀነስ የሚያስችሉ ቅደመ ዝግጅት መደረጉን አገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ተናግረዋል።

ከበዓሉ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ የሆነ የኃይል ፍላጎት ሊያጋጥም ስለሚችል፤ የድንጋይ ወፍጮ፣ የብረታ ብረት፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የሲሚንቶ፣ የፕላስቲክ፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓት ፋብሪካዎች ከጳጉሜ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ከንጋቱ 12፡00 እስከ መስከረም 1 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽቱ 12፡00 ድረስ ከዋናው የኃይል ቋት /ከግሪድ/ የምታገኙትን ኃይል እንድታቋረጡ የተለመደ ትብብራችሁን እንጠይቃለን ብለዋል ኃላፊው፡፡

እንዲሁም ኤሌክትሪክ በሚቋረጥበት ጊዜ የጥገና ስራ ለማከናወን የተቋሙን መታወቂያ ወይም የስራ ትዕዛዝ የያዙ ባለሞያዎቻች በተለያዩ አካባቢዎች ለስራ ጉዳይ ሊንቀሳቀሱ ስለሚችሉ፤ ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ህብረተሰቡ የሃይል መቆራረጥና ሌሎች ችግሮች ሲከሰቱ በነፃ የጥሪ ማአከል 905 ላይ በመደወል አገልግሎት ማግኘት ይቻላል ብለዋል ዳይሬክተሩ።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE