በተከሰከሰው ቦይንግ አውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ማንነት የመለየት ስራ ተጠናቀቀ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

ወደ ኬኒያ ሲያመራ በተከሰከሰው ቦይንግ አውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ማንነት የመለየት ስራ ተጠናቀቀ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

Image may contain: 2 people, people on stage and people standing

ከኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ ሲያመራ በተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎችን ማንነት የመለየት ስራ ተጠናቀቀ፡፡

ከስድስት ወር በፊት ከኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ ሲያመራ የነበረውና በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ተከስክሶ በውስጡ የነበሩ መንገደኞች መሞታቸው ይታወሳል።

የጉዳቱን አጠቃላይ ሁኔታ ለማጥናትም በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቅርብ ክትትል የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።

ኮሚቴው አራት ንዑስ ኮሚቴዎች ያሉት ሲሆን ከዚህ ውስጥ በፌደራል ፖሊስ የሚመራው እና 8 መስሪያ ቤቶችን ያጣመረው የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ማንነት ለማጣራት የተቋቋመው ንዑስ ኮሚቴ አንዱ ነው፡፡

ይህ ንዑስ ኮሚቴ ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው አደጋው ከደረሰበት ስፍራ፥ የሰው ቅሪተ አካል፣ ቦርሳዎች፣ የመንገደኞች ማስረጃዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶች መሰብሰባቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ተናግረዋል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በተሰራ ጊዜያዊ የላቦራቶሪ ማዕከል መረጃዎቹን በጥንቃቄ በማስቀመጥም በተለያየ ምርመራ ማንነታቸውን የመለየቱ ስራ መሰራቱንም ነው የተናገሩት።

በዚህም በዘረመል፣ በጣት እና መዳፍ አሻራ እንዲሁም በጥርስ ኦዶንቶሎጂ በመጠቀም ማንነታቸውን የመለየቱ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

የሟች ቤተሰቦችም በቀጥታ ኢትዮጵያ በመምጣት እና ካሉበት ሃገር የማመሳከሪያ የዘረመል ናሙና በመሰብሰብ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ማንነታቸውን ለመለየት ተችሏልም ነው ያሉት፡፡

በተለይም በዘረመል እና በጣት እና መዳፍ አሻራ በተሰበሰቡ 8 ሺህ 185 ናሙናዎች የተደረገው ምርመራ ውጤታማ ነበር ተብሏል፡፡

ምርመራው ከእንግሊዝ ሃገር ተወዳድሮ ከመጣው ሴልማክ ከተባለ የላቦራቶሪ ተቋም፣ ከኢንተር ፖል እንዲሁም ከፌደራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት የተካሄደ ነው።

በፌደራል ፖሊስ የሚመራው አይ ዲ ቦርድ ኮሚቴ የቀረበውን የምርመራ ሪፖርት ውይይት ካደረገበት በኋላ ተስማምቶበት ተቀብሎታል።

በቀጣይም ለሟች ቤተሰቦች እና ኤምባሲዎች በደብዳቤ ማንነታቸውን የሚገልጸውን ሪፖርት እንደሚሰጥም ነው ንዑስ ኮሚቴው የገለፀው፡፡