ጠ/ሚ “ከራስ ለራስ” በሚል ሃሳብ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ የሚውል የገቢ ማሰብሰቢያ ንቅናቄን በይፋ አስጀምረዋል።


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

(ኢዜአ ) – ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የህክምና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ኢትዮጵያን የጤና ቱሪዝም መዳራሻ ማድረግ እንደሚገባ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ “ከራስ ለራስ” በሚል ሃሳብ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ የሚውል የገቢ ማሰብሰቢያ ንቅናቄን በይፋ አስጀምረዋል።

በተጨማሪ በሆስፒታሉ እድሳት ሲሳተፉ ለነበሩ አካላት የእውቅና ሰርተፍኬት የሰጡ ሲሆን፤ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያስገነባውን ህንጻንም መርቀው ከፍተዋል።

“የልኡል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል” በሚል ስያሜ በ1954 ዓ.ም አገልግሎት የጀመረው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል 40 የህክምና መስጫ ብሎኮች (ዋርድ) አሉት።

ከእነዚህም ወስጥ ስምንቱ በክረምት የበጎ ፈቃደኞች እድሳት ተደርጎለታል።

በቀጣይ ዓመት ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ በማካሄድ ሆስፒታሉን ሙሉ ለሙሉ ለማደስ እቅድ መያዙም ይፋ ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚህ ወቅት “በክረም በጎ ፈቃደኞች የተከናወኑ ተግባራት ኢትዮጵያውያን ከወሰኑ ትልቅ ነገር እንደሚሰሩ ማሳያ ነው” ብለዋል።

በጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ኢትዮጵያን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሴክተሩ ረዥም ዓመት የሰሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውና ኢትዮጵያ ያላት ምቹ የአየር ንብረት ደግሞ ለጤና ቱሪዝም መስፋፋት መልካም እድሎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይ አስር ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያን ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው አምስት የአፍሪካ አገራት ተርታ ለማሰለፍ ስራ መጀመሩን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም ስኬት ዜጎች በጋራ መቆም አለባቸው ብለዋል።

የጤና ሚንስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንዳሉት በክረምቱ የበጎ አድራጎት ተግባር በአዲስ አበባ ሰባት ሆስፒታሎች እድሳት ተደርጎላቸዋል።

በክልሎች የተጀመሩ መሰል ሰናይ ተግባሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አውስተው፤ በቀጣይ ዓመት በሆስፒታሎች የምግብ አቅርቦት ለማሻሸል ሰራ መጀመሩን አክለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርቆ የተከፈተው የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያስገነባው አዲስ ህንጻ 320 አልጋዎች ያሉት ሆኑንና ይህም የሆስፒታሉን አጠቃላይ አልጋ 530 አድርሶታል።

ይህም የሆስፒታሉን አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻልና በአንድ ጊዜ አልጋ ይዘው የሚታከሙ ተገልጋዮችን ቁጥር ለመጨመር ያስችላል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በፌደራል መንግስት ወጪ በአዲስ አበባ ሌሎች መሰል ግንባታዎች መጠናቀቃቸው ይታወሳል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጥር 1955 ዓ.ም “የሳንባ ነቀርሳ መታከሚያ ቤት” በሚል አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ።