" /> በስህተት በተፈጸመ የተኩስ ልውውጥ የአንድ ግለሰብ ህይወት አለፈ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

በስህተት በተፈጸመ የተኩስ ልውውጥ የአንድ ግለሰብ ህይወት አለፈ

(ኢዜአ) – በሰቆጣ ከተማ በስራ ላይ የነበሩ የፖሊስ አባላት ትላንት ሌሊት ከአንድ ግለሰብ ጋር በስህተት በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ የግለሰቡ ህይወት መጥፋቱን የከተማው ፖሊስ አስታወቀ።

በከተማው ፖሊስ የጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ደባሽ ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት ችግሩ የተፈጠረው በከተማው 02 ቀበሌ ማይ ቡሊት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጳጉሜን 2/2011 ዓ.ም ከሌሊቱ 5፡30 ላይ ነው።

በጸጥታ ስራ ላይ የተሰማሩ ፖሊሶች እና በግል መሳሪያ የታጠቀ አንድ ግለሰብ መካከል “ማነህ? ማነህ?” በሚል በተካሄደ የተኩስ ልውወጥ በግለሰቡ ላይ ጉዳት መድረሱ ተመልክቷል።

ጉዳት የደረሰበት ግለሰብም ወዲያውኑ ወደ ተፈራ ሃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱ መትረፍ እንዳልቻለ ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ችግሩን የፈጠሩት የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተፈጠረው ችግር ሌላ የንብረትም ሆነ የአካል ጉዳት አለመድረሱን ጠቁመው “በጨለማ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ሰው ወደ ተኩስ ልውውጥ ከመግባቱ በፊት ማንነቱን ሲጠየቅ ቀድሞ ቢያሳውቅ እንደዚህ ዓይነት ጥፋት አይደርስም ነበር” ብለዋል።

በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ህይወቱ ያለፈው ግለሰብም በሰቆጣ የቀብር ስነ-ስርዐቱ መፈጸሙን ገልጸው የተጎጂ ቤተሰብም የችግሩን አጋጣሚና መንስኤ በሰከነ መንገድ በማጤን ጉዳዩን በህግ እንዲከታተሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የከተማው ማህበረሰብ የአካባቢውን ጸጥታ የማስከበር ስራውን እንደተለመደው ሁሉ ከፖሊስ ጎን በመቆም እንዲያስቀጥል ዋና ኢንስፔክተሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።


የመረጃ ቲቪ አባል ይሁኑ - JOIN US