ላቲን የኦሮሞ ልጆችን ክፉኛ ጎድቷል #ግርማካሳ

አባ አናሲሞስ ነሲብ፣ ከአንድ መቶ አመት በፊት መጽሀፍ ቅዱስን በኦሮምኛ በኢትዮጵያ/ግእዝ ፊደል የተረጎሙ የወለጋ አባት ነበሩ። የኦሮሞ አባት ያላልኩት አባ አናሲሞስ ኦሮምኛ ተናጋሪ የነበሩ ቢሆንም ኦሮሞ ስለመሆናቸው ግን ማረጋገጫ ስለሌለኝ ነው። ለምን በወለጋ ብዙ ማህበረሰቦች ኦሮሞ ሳይሆኑ ኦሮምኛን ግን በግዳጅ እንዲናገሩ የተደረጉ ስላሉ።በወረራ። ( በነገራችን ላይ አጤ ሚኒሊክ ወለጋን በወረራ አላስገበሩም። ነገር ግን የኦሮሞ አባ ገዳዎች በወረራ ነው በዚያ የሚኖሩ ብሄረሰቦችን በነርሱ ስር ያደረጉት)

እንግዲህ ኦሮምኛ ቋንቋ በበቂ ሁኔታ በግእዝ ፊደል መጻፍ እንደሚቻል ከአንድ መቶ አመት በፊት አባ አናሲሞስ አሳይተዉናል፡፡ በግእዝ ብቃት ላይ በርካታና ዝርዝር ሳይንሳዊ መረጃዎች በብዛት አሉ። ያለ ምንም ጥርጥር የግእዝ ፊደል ለኦሮምኛ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሁሉ ብቁ ነው። ብቁ ብቻ ሳይሆን ከላቲን በእጅጉ የተሻለ ነው።

ሆኖም የጥቁር ፈረንጆች የሆኑ፣ የኦሮሞን ማህበረሰብ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ለመነጠል የሚፈልጉ፣ ኢትዮጵያዊ የሆነን ነገር የሚጠየፉ ጠባቦች አሉ። ኦሮምኛ አባ አናሲሞስ እንዳደረጉት በግእዝ ፊደል ከተጻፈ፣ ኦሮሞ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ትስስሩ ይቀጥላል የሚል ፍርሃት ስላለባቸው፣ ለግእዝ ፊደል ካላቸው ጥላቻ የተነሳ፣ ሕዝብ ሳይፈልግ ነው ኦሮምኛ በላቲን እንዲጻፍ ያደረጉት። በግድ፣ በጉልበት።

ያንንም በማድረጋቸው በተወሰነ መልኩ ተሳክቶላቸዋል። ብዙ የኦሮሞ ልጆች ላቲን ብቻ ነው ማንበብና መጻፍ የሚችሉት። ግን የነዚህ ሰዎች መጠነኛ ስኬት ለኦሮሞ ማህበረሰብ ጉዳት ነው የሆነው። የግእዝ ፊደልን፣ አማርኛ እንዲጠሉ ተደርጎ ስላደጉ ፣ አማርኛ ማንበብን መጻፍ አይችሉም። ከዚህም የተነሳ ከተወሰኑ የኦሮሞ ክልል አካባቢዎች ውጭ ስራ የማግኘት እድላቸው ዜሮ ነው የገባው። በአዲስ አበባ፣ በአማራ ክልል፣ በደቡብ ክልል፣ በፌዴራል መንግስት ውስጥ …ተወዳድረው ስራ ማግኘት አልቻሉም። ስለዚህ የስራ አጥነቱ በኦሮሞ ክልል እጅግ በጣም አስፈሪ በሆነ መልኩ ጣራ ላይ የወጣ ነው።

በቅርቡ አዲስ አበባ ሳለሁ አንድ ያየሁትን፣ ሌላ ደግሞ የሰማሁት ልቤን የሰበሩ ሁለት ነገሮች ላካፍላችሁ።

አንዲት እህት ናት። ከነጆ/ወለጋ ነው የመጣችሁ። በጣም ትሁት ናት። ሴክሬታሪያል ሳይንስ ተመርቃለች። በወለጋ ስራ ማግኘት ስላልቻለች አዲስ አበባ ትመጣለች። አማርኛ መጻፍና ማንበብ አትችልም። ላቲን ነው የምትጽፈው። አማርኛ፣ ትንሽ ትንሽ ትናገራለች። ይች እህት አዲስ አበባ የቤት ሰራተኛ ሆና ነው ያገኝኋት። ልቤ በጣም አዘነ። ለነገሩ ስራ አይናቅም፣ ግን ይች እህት አማርኛ ማንበብና መጻፍ ብትችል ኖሮ ከቤት ሰራተኛነት ውጭ ሌላ ስራ የማግኘት እድሏ የሰፋ ነበር። የቀጠሯትን ሰዎች አማርኛ እንዲያስተምሯት፣ ሞራሏን እንዲጠብቁላትና በቶሎ ሌላ ስራ እንድታገኝ ለማድረግ እንዲሞክሩ ነገርኳቸው። በኋላ ስሰማ ግን ይች እህት ተስፋ ቆርጣ ወደ ነጆ ተመለሰች።

ከአንድ ወዳጄ ጋር ስንጫወት፣ አንድ ሌላ ታሪክ ነገረኝ። ጠበቃ ጓደኛ አለው። የዚህ ጠበቃ የወንድም ልጅም ሕግ ተምሮ ተመርቋል። በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ነው የሕግ ዲግሪ ያገኘው። ግን በተማረበት የሕግ ሞያ ሊሰራበት አልቻለም። በኦሮሞ ክልል በኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች ውጭ መስራት አልቻለም። በዚያ ደግሞ ብዙ በሞያው እንዲያድግ አላደረገውም።፡አዲስ አበባ ይመጣል። ሆኖም ስራ ማግኘት አልቻለም። በፊዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃም ሆኖ አቃቤ ሕግ ሆኖ ለመስራት፣ ለተለያዩ የግል መስሪያ ቤቶች የሕግ አማካሪ ለመሆን፣ አማርኛ ማንበብና መጻፍ ያስፈልጋል። ይሄ የሕግ ምሩቅ አማርኛ ማንበብና መጻፍ ስለማይቻል የትም መሄድ አልቻለም። ምን ቢሆን ጥሩ ነው፣ የወንድሙ ልጅ ዘበኛ አድርጎ ቀጠረው።

እስቲ አስቡት የኢትዮጵያ ሰባ አምስት በሞት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለው አዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ነው። ትልቁ ቀጣሪ የፌዴራል መንግስቱ ነው። ከዚያ በመቀጠል እንደ ባህር ዳር፣ አዋሳ፣ ድረዳዋ፣ አዳማ፣ ጂማ .…ያሉ ከተሞች ናቸው። በአዳማና ጂማ በክልል፣ ወረዳ፣ ቀበሌ ጽ/ቤቶች በላቲን ይሰራል፤ ከዚያ ውጭ ግን በአዳማና ጂማ ያሉ የንግድ ተቋማት፣ የግል መስሪያ ቤቶች የሚሰሩት በአማርኛ ነው። ታዲያ ላቲን ብቻ የሚያውቀው የኦሮሞ ወጣት የት ሄዶ ነው የሚቀጠረው? አዲስ አበባ ለገሃር ያለው የኦሮሚያ ባህል ማእከል ????

እንግዲህ ይሄን ያህል ነው የኦሮሞ ልጆች ወደ ኋላ እንዲቀሩ የተደረጉት። ይሄን ያህል ነው ትልቅ የኢኮኖሚክ በደልና ግፍ የተፈጸመባቸው። ይሄን ያህል ነው በኢኮኖሚው መሰላል እንዳይወጡ፣ ከሌላው እኩል ተፎካካሪ እንዳይሆኑ የተደረጉት።

ኦሮምኛ በግእዝ ፊደል እንዲጻፍ ቢወሰን ኖሮ፣ የኦሮሞ ልሂቃን ነን ባዮች፣ ከጥላቻ ሳይሆን በሳይንስና በመረጃ ላይ ውሳኔዎች ቢያሳልፉ ኖሮ፣ የኦሮሞ ልጆች ኦሮምኛን በግእዝ ፊደል ስለሚማሩ፣ አማርኛንም ማንበብና መጻፍ በቀላሉ ይለምዱ ነበር። በአንድ ድንጋይ በርካታ ወፎችን ይገድሉ ነበር።

ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ በላቲን ኦሮምኛ እንዲጻፍ መደረጉ እመኑኝ የበለጠ የሚጎዳው የኦሮሞ ልጆችን ነው። ወደ አንድ ትዉልድ የሚሆኑ የኦሮሞ ልጆች ትልቅ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ያንን ጉዳት ለመጪው ትውልድ እንዲቀጥል ማድረግ አያስፈልግም።

እንግዲህ ይህን እላለሁ።፡ለኦሮሞ ልጆች የምናስብ ከሆነ፣ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ፣ ስራ የማግኘት እድላቸው ከፍ እንዲል፣ ኦሮምኛም የበለጠ በሌላው ማህበረሰብ ተደራሽነቱ እንዲሰፋ ኦሮምኛ በላቲን ሳይሆን በግ እዝ ፊደል እንዲጻፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ቋንቋን እንደ ማንነት መገለጫ ሳይሆን ከመግባቢያነት ያለፈ እንዳለሆነም ማስተማር ያስፈለጋል።

(ከዚህ በታች የአባ አናሲሞስ ፎቶ፣ በደርግ ጊዜ በኦሮምኛ ይጻፍ የነበረው የበሪሳ ጋዜጣ፣ በኦሮምኛ ከተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደና በቅርቡ የታተመው ስርአታ ቅዳሴ መጽሐፍ፣ በአማርኛና በኦሮምኛ በግእዝና በላቲን ፊደል የተጻፈ ነው። ኦሮምኛ በግ ዘ ፊደል እንደሚጻፍ እነዚህ ሰነዶች ግልጽ ማሳያ ናቸው)