" /> የኑሮ ውድነት የየዕለቱ የሕይወት ፈተና እንደሆነባቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች አመለከቱ። | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

የኑሮ ውድነት የየዕለቱ የሕይወት ፈተና እንደሆነባቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች አመለከቱ።

DW : የኑሮ ውድነት የየዕለቱ የሕይወት ፈተና እንደሆነባቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች አመለከቱ። በተለይ የሽንኩርትና የጤፍ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በመጨመሩ በልቶ ማደር አስቸጋሪ መሆኑን ነው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የሚናገሩት። ዘይት እና ሥጋ ለመመገብ ዋጋው በመወደዱ ቅንጦት ሆኗል እና አልቻልንምም ይላሉ።

ዛሬ ረፋዱ ላይ ወደ ጤፍ ገበያ ጎራ አልኩ፣ ፀጥ ረጭ ብሏል። ሻጭ እንጂ ገዥ አይታይም፡፡ ምክንቱን ጠየቅሁ፣ ድምፁን ለመቀረፅ ያልፈለገ ወጣት «የጤፍ ዋጋ መናር ገዥን ይዞ ተሰውሯል።» ሲል ቀለደ። ጎጃም ሲነሳ ማኛ ጤፍ አብሮ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ጤፍ በከፍተኛ ደረጃ ከሚመረትባቸው አካባቢዎችም ጎጃም አንዱ ነው። የጎጃም ጤፍ በጥራቱና በተመራጭነቱም ብዙ ጊዜ ይነሳል። የኅብረተሰቡ የመጀመሪያ ደረጃ የምግብ ምርጫ እንደሆነም በስፋት ታወቃል ጤፍ። የብዙዎች የምግብ ምርጫ ጤፍ ቢሆንም አሁን አሁን ግን ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ  በተለይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጤፍን ሸምቶ ለመብላት ፈተና ሆኖባቸዋል። ጤፍ ለጎጃም ብርቅ ሆኗል ሲሉም ተሳልቀዋል።በባሕር ዳር ከተማ ያነጋገርኋቸው አንዳንድ ነዋሪዎች እንደሚሉት የጤፍና የሌሎች ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ የእህል ዓይነቶች ዋጋ በእጅጉ አድጓል። ከሌሎች ወጪዎች ጋር ተዳምሮ እህል ሸምቶ ቤተሰብን ለማስተዳደር መቸገራቸውን ይናገራሉ።

Lebensmittel im Bahir Dar lokalen Markt Äthiopien (DW/A. Mekonnen) ሌላዋ የባሕር ዳር ነዋሪም ቢሆን በተለይ የቀይና የነጭ ሽንኩርት፣ የጤፍ ዋጋ በአስደንጋጭ ደረጃ መጨመሩን ተናግረዋል። የዋጋ ጭማሪው በተወሰኑ ምግብ ፍጆታዎች ላይ ሳይሆን አጠቃላይ ያልጨመረ ነገር እንደሌለ የሚናገሩት ሌላዋ ነዋሪ ዘይት እና ሥጋ መመገብም ቅንጦት ሆኗል፣ ዋጋውን አልቻልነውም ነው ያሉት።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዓለምነህ ዳምጤ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት የሚያጠኑ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ጥናት እያደረጉ ነው። ከሚመለከታቸው የንግዱ ማኅበረሰብ  ጋርም ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑንም አብራርተዋል። መንግሥት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲፈልግም ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

የመረጃ ቲቪ አባል ይሁኑ - JOIN US