በአ/አ ለኦሮሚያ ልዩ ጥቅም እሰራለሁ አለ አዴፓ/ብአዴን፣ ክፍል 1 #ግርማካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

ዶ/ር አምባቸው መኮንን የአማራ ክልል ርእስ መስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ከተማን አስመልክቶ ከተሳታፊ በተነሳላቸው ጥያቄ፣ በሰጡት ምላሽ ከፍተኛ ተቃዉሞና ዉግዘት አስተናግደዋል። ብዙዎች “ዶ/ር አማባቸው ፈንጂ ረገጡ” እስከማለትም የደረሱ አሉ። ከዚህም የተነሳ አዴፓ/ብአዴን በመግለጫ ማብራሪያ ለመስጠት የተገደደ ሲሆን፣ ዶ/ር አምባቸውም ራሳቸው ከምሁራን ጋር ባደረጉት ስብሰባ፣ ጉዳዩን አንስተው ምላሽ ሰጥተዋል።

ዶ/ር አምባቸው አዲስ አበባን በተመለከተ በአምቦ ፣ “አዲስ አበባን በተመለከተ ሕግ መንግስቱ (ወያኔና ኦነግ በሕዝቡ ላይ የጫኑትን ማለታቸው ነው) ያስቀመጠውን የሚሸራርፍ አቋም ማንም የለውም .… የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሕግ መንግስታዊ መብት አለው። ልዩ ሕገ መንግስታዊ መብቱ እንዲከበርለት ደግሞ እኛም እንታገላለን” ነበር ያሉት። “ሕግ መንግስቱ ያስቀመጠውን” ሲሉም አንቀጽ 49ን ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው።

ይህ በሕግ መንግስቱ ላይ ያለው፣ በአዲስ አበባ የኦሮሚያን ክልል “ልዩ ጥቅም” የተባለው መከበር አለበት ብሎ የሚደነግገው አንቀጽ ፣ ግልጽ ያልሆነና ሆን ተብሎ በአዲስ አበባ ጉዳይ  ላይ ንትርክ ለመፍጠር በሕወሃት ተሰንቅሮ ሕገ መንግስቱን ውስጥ የገባ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። የዚህ አንቀጽ አሻሚነቱና አወዛጋቢነቱ በብዙ መልኩ ሊገለጽ ይችላል።

አንደኛ – አንቀጹ አዲስ አበባ ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብት አላት ይልና፣ በሌላ በኩል በአዲስ አበባ የኦሮሞ ክልል ልዩ ጥቅም ይጠበቃል ይላል። ይሄም እርስ በርሱ የሚቃረን፣ የኦሮሞ ክልል በአዲስ አበባ ጉዳይ የይገባኛል ጥያቄ እንዲያቀርብ  የገፋፈውን ምክንያት ሆኗል።

ሁለተኛ  – የኦሮሞ ክልል ልዩ ጥቅም ይኖረዋል ብሎ አንቀጹ ሲያስቀምጥ፣ ጥቅሞቹ ምን እንደሆነ አልተገለጸም። “ጥቅም” ማለት ጽ/ቤት አዲስ አበባ ውስጥ ማድረግ ነው ? በአዲስ አበባ ከሚሰበሰበው ግብር የተወሰነውን መቀበል ማለት ነው ? ኦሮሚያ ማለት የኦሮሞ ክልል ማለት ነው። የኦሮሚያ ባለቤት በኦሮሚያ ክልል ሕግ መንግስት መሰረት ኦሮሞው ነው። የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ማለት ደግሞ የኦሮሞ ልዩ ጥቅም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ስለዚህ ልዩ ጥቅም ሲባል ኦሮሞው ከሌሎች ማህበረሰበት የበለጠ፣ የተለየ ጥቅም ያግኝ ማለት ነው ? ከሁለት አመታት በፊት በኦህዴድ የተዘጋጀ ጥናታዊ ሰነድ ለፌዴራል መንግስት ቀርቦ እንደነበረ የሚታወስ ነው።  በሚስጥር ተይዞ የነበረው ሰነድ አፈትልቆ ወጥቶ በወቅቱ ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር። ሰነዱ የአዲስ አበባ ባለቤት ኦሮሞ መሆኑን አስቀምጦ፣ በአዲስ አበባ በኮታ የስራ አድል ለኦሮሞዎች እንዲሰጥ፣ የአዲስ አበባ የተለያዩ መንገዶች በኦሮሞ ስም እንዲጠሩ፣ በአዲስ አበባ ኦሮምኛም የስራ ቋንቋም እንዲሆን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን አካቶ ነበር። ልዩ ጥቅም ሲባል እነዚህ በሰነዶችይ የተቀመጡትን ተግባራዊ ማድረግ ነው ? ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

ሶስተኛ – አንቀጹ ከሃረር፣ ከጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከአፋር ፣ ምን አልባትም ከሶማሌና ትግራይ ክልሎች በቁጥር የበለጠ ህዝብ የሚሆነውን የአዲስ አበባ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብቱን የሚገፍ ነው። የኦህዴድ/አዴፓ ከፍተኛ አመራር አንድ ወቅት “የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት አለው እንጂ የራሱን እድል በራሱ ግን የመወሰን መብት የለውም” ማለታቸው እዚህ ጋር ማስታወሱ ሊረዳ ይችላል። (በነገራችን ላይ የአዲስ አበባ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ራሱን በራሱ የማስተዳደርን መብቱ ተገፏል። በመረጣቸው ሳይሆን በኦህዴድ/ኦዴፓ በተሾሙ፣ ሹመኞች ነው እየተዳደረ ያለው)

አራተኛ ፣ አንቀጹ በኦሮሞ ክልል ስለተከበቡት እንደ ሃረር ያሉ ከተሞችን አላካተተም። ከአማራ ክልል የአባይ ወንዝ ወደ ቢኔሻንጉል ክልል ይሄዳል። ከኦሮሞ ክልል የአዋሽ ወንዝ ሶማሌና አፋር ክልል ይገባል። የገናሌና የሸበሌ ወንዞች ሶማሌ ክልል ያልፋሉ። የአማራ ክልል በቤኔሻንጉል ክልል፣ የኦሮሞ ክልል በሶማሌና በአፋር ክልሎች.…ወንዞች ከነርሱ መሬት ስለሚነሱ ልዩ ጥቅማቸው በዚህ አንቀጽ አልተካተተም። ያ ማለት አንቀጹ መስፈርት ብሎ ያስቀመጠውን፣ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለሁሉም ቦታዎች ተግባራዊ አላደረገም። አድሎአዊ አንቀጽ ነው።

ይህንን አንቀጽ ፣ ከኦሮሞ ብሄረተኞች በስተቀር፣ የአዲስ አበባን ህዝብ ጨምሮ፣ ሌላው ማህበረሰብ አጥብቆ የሚቃወመው ነው። በተለይም ደግሞ ዶ/ር አምባቸው እመራዋለሁ የሚሉት የአማራ ክልል ሕዝብ፣ ይሄን አንቀጽ ጨምሮ ሕግ መንግስቱ ራሱ፣ እርሱን እንደማይወክል፣ መሻሻል እንዳለበት በተደጋጋሚ ገልጿል። በአጭሩ አነጋገር እነ ዶ/ር አማባቸውና አዴፓ ፣ ይሄን የልዩ ጥቅም አንቀጽ ለማስከበር እንታገላለን ማለታቸው፣ የሕዝቡን ሳይሆን የኦህዴዶችን አቋም እያንጸባረቁ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

ዶ/ር አምባቸውና የአዴፓ አመራሮች በዶ/ር አምባቸው ላይ የተሰነዘረዉን ተቃዉሞ በጸጋ ተቀብለው ለማሻሻል ቢሞክሩ የተናገሩትን እንደ ስህተት ቆጥረን፣ “ስህተት የማያደርግ ማንም የለም፣ ቁም ነገሩ ስህተቶችን ማረም ነው” በሚል ማለፍ እንችል ነበር። ነገር ግን ስህተቶቻቸውን ለማመንና ለመቀበል አልፈለጉም። እንደውም ተቃዉሞ ያነሱትን ዉሸታሞችና ጸረ-ኦሮሞዎች እንደሆኑ፣ ሰብዊነት እንደሌላቸውና ህዝብ ከሕዝብ ለማጣላት እንደሚፈልጉ አድርገው ነው ለማቅረብ  የሞከሩት።

ዜጎች አስተያየት የሰጡት በፈጠራ ወሬ ሳይሆን ዶ/ር አምባቸው የተናገሩትን ሰምተውና አድምጠው ነው። ለተናገርነው ነገር ሃላፊነት መዉሰድ ትልቅነት ነው። በአንጻሩ ሌሎች ላይ ጣቶቻችንን መቀሰር ደግሞ ደካማነት ነው። ዶ/ር አምባቸው ጣታቸውን ወደ ሌላው ከሚዘረጉ ወደራሳቸው ቢያዞሩ ጥሩ  ነበር።

አንቀጽ 49 ትክክለኛ አንቀጽ የሆነ ይመስል፣  ዶ/ር አምባቸው  በዚህ አንቀጽ ላይ የተቀመጠውን፣ ህዝብ የሚቃወመው ኢፍታዊ የልዩ ጥቅምን ፖለቲካ እንዲከበር እንታገላለን ማለታቸው፣  በኔ እይታ እጅብ በጣም ትልቅ ስህተት ነው። ይሄንንም የምልበት ምክንያት

አንደኛ – በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም መከበር አለበት ሲሉ፣ የሚከበረው ጥቅም ምን እንደሆነ ባልተገለጸበት፣ እነርሱም በማያወቁበት ሁኔታ በአደባባይ ይሄንን አንቀጽ ደግፎ መናገር ፖለቲካቸው የካድሬነትና የአገልጋይነት ፖለቲካ መሆኑንና በእውቀት ላይ አለመመስረቱን ፣ የበፊቱን አሰራር ለማስቀጠል መፈለጋቸዉን የሚያሳይ  በመሆኑ፣

ሁለተኛ – ኦህዴዶችና የኦሮሞ ብሄረተኞችን ለማስደስት  ተብሎ፣  የአዲስ አበባ ህዝብን ፍላጎትና ስሜት ከግምት አለማስገባታቸውን፣ ለአዲስ አበቤዎች ደንታ ቢስ መሆናቸውን አመላካች በመሆኑ፣

ሶስተኛ – ልዩ ጥቅም ብለው ሲናገሩ በአዲስ አበባ ላይ አንዱ ከሌላው የበለጠ መሆኑን ፣ አፓርታይድን አምነው መቀበላቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ ነው።

ዶ/ር አምባቸውና አዴፓ “ልዩ ጥቅም” ሲደገፉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ዉሃ የማይቋጥር ማብራሪያ ለመስጠት ሞከረዋል። ለገበሬው በመብት ብለን ነው በሚል።፡በክፍሉ ሁለት የገበሬው መብትና ልዩ ጥቅም በጭራሽ የማይገናኙ መሆናቸው የሚያሳይ ተከታይ ጽሁፍ ይዤ እመለሳለሁ። የገበሬዎች መብት ማስከበር ሰብአዊነትና መንግስታዊ ግዴታ ነው። ልዩ ጥቅም ግን አፓርታይድና ዘረኝነት ነው፡