" /> መስሎ መኖር ከእራስ እውነታ ጋር ሲጣረስ – ፀጋ ወርቅ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

መስሎ መኖር ከእራስ እውነታ ጋር ሲጣረስ – ፀጋ ወርቅ

ከፀጋ ወርቅ

ይህንን ጽሁፍ ስናነብ ውሕድ ማንነታቸውን በአግባቡ ተቀብለውት ለዘመናት በአብሮነት ሃገራቸውን የመሩ ፣ ለሃገራቸው ህልውናና ፍቅር እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ እና እኛን የወለዱ የምንኮራባቸው ጀግኖች ቀደምቶቻችንን ሁል ግዜ ክብራቸው ክብራችን ጉድለታቸው ጉድለታችን ብለን ተቀብለን መሆኑ እንዳይዘነጋ።

መስሎ መኖር ከእራስ እውነታ ጋር ሲጣረስ ሊያመጣ የሚችለው ውጤት ምን እንደሚሆን ገምተውት ያውቃሉ? ሰዎች በውሕድነታችው ምክንያት ሊወያዩባቸው የሚችሉት ጉዳዮች በርካታ ቢሆኑም ዛሬ ጥቂቶቹን በግርድፍ ልናይ መርጠናል።

ባለፈው ውይይታችን ላይ ውሕድ ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ማንነት የለውም ከተባለ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ላይ መወያየት ሲቻል በተናጠል ውሕዶችን ብቻ የሚመለከት ውይይት ለምን አስፈለገ የሚል ሃሳብ ተነስቶ ነበር። የውይይቱ መድረክ አስፈላጊነት ውሕድነት የራሱ የሆነ ስብእና ስላለው በጋራ የሚጋራው የማንነት ጥያቄዎች እና በተለይም በዘር እና ቋንቋ ተኮር ብድኖች ስብስቦች እና አስተዳደሮች የተደፈጠጠና ፍጹም ቦታ ያልተሰጠው በመሆኑ ምክንያት የሚፈጠሩ መብት ነክና ስነልቦናዊ ችግሮችን በጋራ ለመወያየት እና መፍትሔም ለመፈለግ ስለሚረዳ ነው ። የሰዎች የማንነት ጥያቄ ከግል ህይወት ጀምሮ እስከ ሃገር ግንባታ ድረስ ትልቅ ሚና ስላለው ውሕድነት ሊፈተሽ ሊመረመር እና በሰፊው ሊሰራበት ይገባል ወደሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል። በተለይም ቋንቋና ዘር ተኮር ክልል እና አስተዳደር ባለበት ሃገር ላይ ውሕዶች ምን ቦታ እንዳላቸው መነጋገር የምርጫ ጉዳይም ሳይሆን የህልውናም ጉዳይ ጭምር ነው። የተወሰነውን ሕብረተሰብ ማንነት የሚያከብር ሥርዓት ለመመሥረት በሚል ሰበብ የተቀረውን ሕብረተሰብ ማንነት መደፍጠጥ ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም። እነዚህ ውይይቶች ግን አንድ ወጥ ማንነት ያላቸውን ወይም አለን ብለው የሚወስዱ ሌሎች ህዝቦችን አግላይ አይደሉም። ውሕድ የተገኘው ወጥ ማንነት ካላቸው ወላጆች በመሆኑ በውሕድ ማንነት ውስጥ አንድ ወጥ ማንነት ሁሌም ይንጸባረቃል። በተጨማሪም በቀጣዩ ትውልድ ዛሬ ያሉ ማንነቶች እየተደባለቁ ውሕድ ማንነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ስለሚፈጠሩ ወጥ ማንነትን የተቀበሉ ሰዎችም በውሕድ ማንነት መከበር እና መዳበር ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸው የባለራዕይነታቸው ድርሻ ይሆናል።

በርግጥም የውሕድ ኢትዮጵያዊ ማንነት ከኢትዮጵያዊ ማንነት ውጭ ማንነት የሌለው ፣ በብሄር ስም በሰው ሰራሽ ክልሎች ሊከለል እና ሊወሰን የማይችል ፣ የታሪክ ሂደት፣ ተፈጥሮና ተጣምሮት የኢትዮጵያ የአንድነት ምሰሶ ያረገው ማንነት ነው። በዚህ ዘመን የብሄር ፖለቲካ ጥግ በደረሰባት ሃገራችን ላይ የተለያዩ ቡድኖች በዘውግ ወይንም በዜግነት ማንነት ራሳቸውን ሲገልጹ ይታያሉ። አንዱ በዘር መደራጀት ሃገርን ይበታትናል ሲል ሌላው ደግሞ በዜግነት መደራጀት አሐዳዊነትን ይፈጥራል ይላል። በነዚህ ሁለት የጎሉ የቡድን ክርክሮች መሃል ግን በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከሁለት እና ከዚያም በላይ ዘር ያላቸው ውሕድ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ጎልቶ ወጥቶ ለውይይት ሲቀርብ አይታይም። ውሕድ ኢትዮጵያዊው በሃገራችን ካሉት ከ80 በላይ ከሚሆኑ ብሄር ጋር በህዝብ ብዛት ሲወዳደር ከላይኞቹ ተርታ እንደሚሆን ለመገመት አዳጋች አይደልም። ሆኖም በማንኛውም ሃገራዊ ውይይቶች ላይ በአስፈላጊው መጠን አለመካታቱ ለምን ይሆን ? ውሕዶች በብዛት መኖራችንን በተገቢው መጠን አለማሳወቃችን ይሆን ? ይሄስ ከምን ይመናጫል? ከሥጋት? ከመሸበር? ውገናን ከመጥላት?

በ2007 የህዝብ ቆጠራ ለምሳሌነት ብንወስድ 22 ብሄሮች እያንዳንዳቸው (100 እስከ 10 ሺ) ፣ 35 ብሄሮች እያንዳንዳቸው (ከ10 ሺ እስከ 100 ሺ) ፣ 20 ብሄሮች እያንዳንዳቸው (ከ100 ሺ እስከ 1ሚሊየን) ፣ 5 ብሄሮች እያንዳንዳቸው (1 ሚሊየን እስከ 5 ሚሊዮን) የህዝብ ብዛት ሲያስመዘግቡ 2 ብሄሮች ደግሞ ከ20 ሚሊዮን በላይ አስመዝግበዋል። በዚህ ቆጠራ ሁለት የተለያዩ ብሄር ወላጆች አሉን ብለው የተቆጠሩት 36,570 ውሕድ ኢትዮጵያን ሲሆኑ በህዝብ ብዛት 40ኛውን ቦታ ይይዛሉ።
ይህ ቁጥር ግን ከእውነታው በእጅጉ ያነሰ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። የኢትዮጵያ የቋንቋ ፌደራሊዝም በፈጠረው ባለቤትነትን ወይም መጤነትን በሚያላብስ ሕገ መንግሥት ተሸብረው እና ሠግተው ንብረታቸውን ላማትረፍ፣ ላለመሰደድ፣ ላለመገለል፣ ከሥራ ገበታ እና እድል ላለመከልከል ሲሉ ሰዎች ውሕድ ማንነታቸውን ቢደብቁ የሚያስገርም አይሆንም። ኢትዮጵያ ውስጥ ውሕድ ማንነት እጅግ የበረከተ መሆኑን ብዙ ሰው ጎረቤቶቹን እና አካባቢውን በማሰብ ብቻ ሊያስተውለው የሚችለው ጉዳይ ነው። ይህንን እውነታ ለማረጋገጥ ብዙም ወደ ኋላ ሳንሄድ እስከ አያት ቅድመ አያታችን እንኳን ብንቆጥር አብዛኞቻችን የተለያየ ብሄር ካላቸው ወላጆች መወለዳችን እሙን ነው። በተጨማሪም ዘመዶቻችንን እና በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች በመጠየቅ ፣ የሃገራችንን መሪዎች እና ታዋቂ የሆኑን ግለሰቦች የትውልድ ሃረግ በማየት ልናረጋግጠው የምንችለው ሃቅ ነው ።

ሰዎች ውሕድ ማንነታችውን በግልጽ ላለመናገር የተለያየ ምክንያቶች ይኖራቸዋል ከነዚህም ውስጥ የአባት ዘር ብቻ መቁጠር ፣ የተለያዩ ብሄር ወላጆች አሉኝ የሚል ምርጫ እንዳለ አለማወቅ ፣ በአካባቢው ገናና ከሆነው ዘር ጋር እራስን ማስጠጋት ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞችን ከሚያስገኝ ዘር ጋር እራስን ማስጠጋት ፣ በትውልድ ከተገኘ ተፈጥሮአዊ ማንነት ይልቅ ከአስተዳደግ እና አብሮ ከመኖር የተገኘን ማንነት የራስ ብሎ መቀበል እና ከላይ የተጠቀሰው የሥጋትና የሽብር ስሜት ይገኙበታል። እንደ አካባቢው ስለ አንድ ጎሣ የሚነገሩ መልካም እና አወዳሽ አባባሎች ወይም በተቃራኒው ስብእናን የሚነኩ ወይም ቂም በቀል የሚገልጹ ንግግሮች እና አባባሎች በሰዎች የብሄር ምርጫ ላይ በመጠኑም ቢሆን የራሳቸው የሆነ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል። ውሕዶች የራሳቸውን ማንነት ተቀብለውት ኮርተውበት እንዲኖሩ ምን መደረግ ያለበት ይመስልዎታል?

በውይይቶቻችን መሃል ከሚነሱት እና በአካባቢያችን ከታዘብናቸው ውስጥ ውሕድ ኢትዮጵያዊ ከትውልድ ሃረግ ውስጥ አንዱን ማንነት በምን ምክንያት ይመርጣል? የሚኖርበት አካባቢ በትውልድ ሃረግ ምርጫው ላይ ምን አይነት አስተዋጽዖ/ ተጽዕኖ ያደርጋል? በአግባቡ ያለተስተናገደ ውሕድነት በግል እና ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ምን ይመስላል? መሰልን መርጦ መሰባሰብ የሰዎች ተፈጥሮዊ ባሕሪ ነው ወይ? እነዚህ ሃሳቦች እያንዳንዳቸው ጥልቅ ምርምር የሚያስፈግጋቸው ቢሆኑም ለአሁኑ በሃሳብ ደረጃ እናነሳቸዋለን።

1 – የሚኖሩበት አካባቢን በማንነት መውሰድ
በአንዳንድ ከተሞች አካባቢ ማንነት የግል ጉዳይ እንጂ የማህበረሰብ ችግር ሆኖ አይታይም። ብሄሬ ሰፈሬ ነው ሃገሬ ኢትዮጵያ ናት ፥ ያራዳ ልጅ ዘር የለውም የሚሉ አባባሎች በሰፊው ይነገራሉ። በእንደዚህ አይነት ቦታዎች ላይ ውሕድ ኢትዮጵያዊ እንደማንኛውም ዜጋ ይኖራል እነርሱን ብቻ ነጥሎ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ችግር የሚያደርስባቸው የለም። አንድ ውህድ ቤተሰብ ጫና ካለደረገበት በቀር ሰው መሆኑን ነው እንጂ የሚያውቀው ስለ ብሄር ገፍቶ አይመራመርም። በፍላጎት እና በራስ ውሳኔ የአባት ወይንም የእናት ማንነት ወስዶ በአንዳቸው ብሄር ብቻ እራሱን የሚገልጽም አለ። ሰው በሰውነቱ ብቻ በሚታይበት እና ብሄር በማይቀነቀንበት አካባቢ ይህ ሰው በምርጫው የሚደርስበት ጉዳት አይኖርም። ምርጫው ሌላውን ለመጉዳት ሳይሆን እራሱን ለመግለጽ እና በሚመቸው ባህል እና ወግ ለመኖር ይረዳዋል። ከቤቱ ውጪ ከሌሎችም ጋር ተሰባጥሮ መኖር ችግር አይሆንበትም። ይህ በከተሞች ብቻ ሳይሆን በቀድሞው በብሄር ያልተደራጀ የጦር ሰራዊት ካምፖች አካባቢ ያደጉ ልጆች አንድ ሰፈር ተወልደው ማደጋቸውን እንጂ እንኳን የጎደኞቻቸውን የራሳቸውንም ዘር በቅጡ የማያውቁም አሉ። የዘር ጉዳይ ለአብሮነታቸው ምንም አሉታዊ ተፅእኖ አልነበረውም ማለት ይቻላል።

2 – በውዴታ ዘርን መምረጥ
በእናት ወገን እና በአባት ወገን ተመጣጣኝ ሃይል ወይንም መከባበር ባለበት ቤተሰብ ልጆች ሁለት የባህል እና ያኗኗር ዘቤዎችን አቆራኝተንው ይይዛሉ። ቋንቋ ፣ አለባበስ ፡ አመጋገብ ፡ ሃዘን እና ደስታን አገላለጽ ፣ ዘፈን ፣ የበዓላት አከባበር የሁለቱም ወላጆቻቸው ወገኖችን ይጋራሉ። አንዳንዴም በእናታቸው ወገን እና በአባታችው ወገን በኩል የሚጠሩበት ሁለት ስሞች በሁለት የተለያየ ቋንቋ ሊኖራቸው ይችላል። መከባበር ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ከአንድ ቋንቋ በላይ መናገር ፡ ከአንድ ባህል በላይ ባለቤት መሆን ከፍተኛ አሴት ነው። ያደጉበት ቦታ ደግሞ ከወላጆቻቸው ትውልድ ቦታ ውጭ ከሆነ ያደጉበትን መንደር ባህል እና ማንነት በሶስተኛ ማንነት ይይዛሉ። ቤተሰቦቸው የተለያየ እምነት ተከታዮች ከሆኑ ደግሞ ማንነታቸው በይበልጥ ይወሳሰባል። ይሁን እንጂ መከባበር ባለበት ቤተሰብ ውስጥ እነዚህ ሁሉ ልዩነቶች ይጠቅማሉ እንጂ ለከፋ ጉዳት አይዳርጉም። ይህም በኢትዮጵያ እጅግ በስፋት የሚስተዋል ነበር።

3 – ዘርን ደብቆ መኖር
በሌላ መልኩ ደግሞ ዘር ተኮር አስተዳደር ባለበት አካባቢ በምርጫውም ይሁን በውጭ ተጽዕኖ አንድ ውሕድ ውሕድነቱ ሸሽጎ የሚኖርበት ሁኔታ አለ። በነዚህ ቦታዎች ላይ <ንጹህ ዘር> ያለው የክልል ባለቤትነት የተሰጠው የበላይነት ቦታን ስለሚይዝ ውሕድ ወይም የሌላ ብሔር ማንነቱ ቢታወቅ ባላቤት ነህ በተባለው ብሔር አባላት ሊገፋ፣ ሊበደል፣ ሊቀማ ስለሚችል ከአሁን አሁን ማንነቴ ታወቀብኝ በማለት በመሳቀቅ እና በጭንቀት ኑሮውን ይመራል። የማንነቱ መታወቅ በንብረቱ በስራው እና በማህበራዊ ኑሮው ላይ የሚያመጣው ችግር ከፍተኛ በመሆኑ እራሱን ሆኖ ከመኖር ይልቅ አካባቢውን መስሎ መኖር ይገደዳል። የዘር ልዩነት ጫናው በሚበዛበት ቦታዎች ላይ የህልውና ስጋት ስለሚጨምር ጥንቃቄውም ይጨምራል። የሌላ ብሄር የሆኑ ዘመጆቹን እስከ መካድ እና አላውቃቸውም እስከ ማለት ይደርሳል። የሚያውቀውን ቋንቋ እንኳን ላለመናገር ባስተርጎሚ ማውራት ይጀምራል። በተለይ ባለፉት 40 አመታት ውስጥ አንዱ ዘር በዳይ ፣ ገዳይ ፣ ጨቋኝ አውሬ፣ መጤ ሌላውን ተገዳይ እና ተጨቋኝ ነባር ተደርጎ በስፋት የተዘራ መርዘኛ ትርክት ባመጣው አንዱ ዘር ሌላውን ዘር የመበቀል እሩጫ ከሁለቱንም ዘር የሚጋራው ውሕድ ከመሃል ተቀምጦ አጥፊ ነኝ ጠፊ በሚል ውዝግብ ውስጥ እራሱን ያገኝዋል። በትምህርት ቤት በአካባቢው እና በጓደኞቹ በተደጋጋሚ ዘራችንን ጨፈጨፈ ብለው እንደ አውሬ የሚያዩት ዘር በሱነቱ ውስጥ ስላለ የዚያ የክፉ አውሬ ዘር አለብኝ በሚል በማፈር ፣ በመሸማቅ እና በጥፋተኛነት ስሜት እራሱን ዝቅ አድርጎና ቀብሮ ኑሮውን እንዲገፋ ይገደዳል።

4 – በተጽዕኖ ዘርን መምረጥ
4-1 በቤተሰብ ዙሪያ
በተለያዩ ውጫዊ ተጽዕኖ ምክንያት አንድ ውሕድ ሰው ከአባቱ ወይንም ከእናቱ ብሄር አንዱን ብቻ ለመምረጥ የሚገደድባቸው ሁኔታዎች አሉ። ይህ የማንነት ውዝግብ መጀመሪያ ሰላም እና መከባበር በሌለው ቤተሰብ ውስጥ ይጀምራል። የውሕድ ማንነት እራሱን ችሎ የቆመ ማንነት ቢሆንም አንድ ውሕድ ቤተሰቦቹን ለማስደሰት ሁለቱንም ሆኖ መገኝት ይጠበቅበታል። ይህ ግጭት በልጆች ላይ ከፍተኛ ስነልቡናዊ ተጽኖን ይፈጥራል። በዚህም በዚያም ወገን የሚሰነዘሩ ጉንተላዎች ልጆችን በራስ የመተማመን አቅማቸውን ያሳጣቸዋል። የእኔ ብለው የሚይዙት ማንነት ስለማይኖራቸው በግድ ወደ አንዱ ለመጠጋት እና አንዱን ለመካድ ይገደዳሉ። ወይንም በተፈጥሮ ያገኙትን ሁለቱንም ማንነታቸውን ትተው ያደጉበትን ህብረተሰብ ለመምሰል በአካባቢ ወደሚገኝ ማንነት ይደላሉ።

በቤተሰብ ውስጥ የተጀመረ የውሕድ ውስጣዊ የማንነት ፍጭት በልጆች ላይ የተዛባ ባሕሪን ይፈጥራል። እያደገ ሲሄድ በሰፈር በመንደር በትምህርት ቤት በስራ ቦታ ብሎም በሃገር ላይ የራሱ የሆነ የከፋ አሻራን እየጣለ ያልፋል። በተለይም ዘር ላይ በተመረኮዘ ማንኛውም ስብስብ ውስጥ በሚገቡበት ግዜ ጎዶሎ የሆነ ማንነት እንደያዙ ሲለሚሰማቸው ከአስፈላጊው በላይ በመስራት በቡድኑ ውስጥ ታማኝነትን እና ተቀባይነትን ለማግኘት ጥረት ይደረጋሉ። <ንጹህ ዘር> አለን ብለው ከሚሉት በላይ ያንን ዘር ሆኖ ለመገኝት ያልተሳካ ጥረት ያደርጋሉ። ይሄም በቀልና አግላይነትን ማእከል ባደረገ ሥርዓት ውስጥ ብዙዎችን እጅግ የከፋ በደልና ወንጀል እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል። ይሄንን በግልጽ ለመረዳት የበቀል እና የስድብ ፊታውራሪዎች የሆኑትን ያለፉት ሰላሳ ዓመታት የፖለቲካ ገጸ ባሕርያት መቃኘት ትልቅ ትምህርት ይሰጣል።

ይህም ሆኖ ግን በዘር ተኮር ስብስቡ ውስጥ የአንድ ውሕድ የስራ አፈጻጸም ወይንም ውሳኔ በራሱ ጭንቅላት የሚያምንበትን ወሰነ አደረገ ከመባል ይልቅ ወደ አባቱ ዘር አደላ ወደ እናቱ ዘር ተንሸራተተ ፣ ዘር ከልጓም ይስባል ከሚሉ ትችቶች አይድንም። ድሮስ ምኑ ይታመናል ፣ ወዴት እንደሚያደላ አይታወቅም ፣ ወላዋይ ፣ ማህል ሰፋሪ ፣ ሲከፋም ከሌላ አገር ሰው እንደተወለደ ሁሉ ዲቃላ ከሚሉ ትችቶች አያመልጥም። በዚህ ተጽዕኖ ስር ያሉ አብዛኛቹ ውሕዶች በስራቸውም በቤተሰቦቻቸውም ላይ ከመደበኛ ዜጋዊ እንቅስቃሴዎች ውጭ የሆኑ ያልተለመዱ ተግባሮችን ለመፈጸም ይዳረጋሉ።

በውጫዊ ተጽዕኖ ስር ያለ ውሕድ የትዳር አጋሩ ከእርሱ የተለየ ብሄር እንዳላት እያወቀ ትዳር መስርቶ ከባለቤቱ ብሄር ጋር ግን በውጭ ሲጣላ ፣ ሲወጋገዝ እና ሲጠፋፋ ይታያል። በጋራ ያፈሯቸውም ልጆች ያንዱን ብሄር ብቻ እንዲይዙ ታላቅ ተጽዕኖ ይደረግባቸዋል። ባለፉት 40 አመታት ውስጥ የዘርን መሰረት ያደረገ ስርዓት እየከረረ ሲመጣ የልጆቻቸውን የመጠሪያ ስም በብሄራቸው ቋንቋ የቀየሩ ወላጆች ነበሩ። ትምህት ቤት ሲከፈት ስማቸው ተቀየሮ የሚመጡ ልጆች ብዙ ነበሩ። እነዚህ ልጆች በአዲሱ ስማቸው ምክንያት በጓደኞቻቸው ስለሚጎነተሉ የባህሪ ለውጥም ያመጡ ነበሩ። የዘረኝነቱ ሀገራዊ ጦስ በወጉ ባልተስተናገደበት ቤተሰብ ውስጥ ትዳርን አፍርሶ ልጆችን በትኖ የራስን ብሄር አባል ፈልጎ እስከ ማግባት ድረስ ተኪዷል። በዚህም ከሁለት ያጡ ውሕድ ልጆች ለእንግልት ተጋልጠዋል። በፍቅር ላይ ያሉም ጥንዶች በግልም በቤተሰብም ግፊት እየተዋደዱ ትዳር ሳይመሰርቱ የቀሩ ብዙዎች አሉ። የሚያፈቅሩትን ትተው የማይወዱትን በዘር መመሳሰል ብቻ ያገቡም ብዙዎች ናቸው።

በማንኛውም ምክንያት ትዳር በሚፈርስበት ግዜ በልጆች ላይ የሚደርስ ስነልቡናዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው። ሃገር ሲፈርስ ደግሞ በበለጠ የሚጎዱት ውሕድ ልጆች ናቸው። በምሳሌነት ኢትዮጵያና ኤርትራ ሲከፋፈሉ ብዙ ቤቶችን ፈርሰዋል ፣ ልጆችም ተበትነዋል። ልጆች ከአባት እና ከእናት አንዱን መምረጥ ተገደዋል ፣ ከሚያውቁት አካባቢ እና ማንነት ተለይተው አዲስ ማንነትን ይዘዋል ፣ ከሃያ ሰባት አመታት በኋላ እድለኞች የሆኑት በህይወት ካሉት ከዘመዶቻቸው ጋር ሲገናኙ ሌሎቹ በሃዘን ተሸማቀው ቀርተዋል ። በመጀመሪያው አመታት ዘር በአባት በኩል ብቻ ይቆጠር ስለነበር ልጆች የፈለጉትን ሃገር እንኳን መርጠው ለመቀመጥ ወይም ለመሄድ ያልቻሉበት ወቅት ነበር።

4-2 ከቤተሰብ ውጭ የሚያስከትለው ተጽዕኖ
በማህበረሰብ እና በስራ ቦታ ሲታይ እነዚህ የማንነት ችግር ያለባቸው ውሕዶች ተቀባይነትን ፍለጋ ባለጊዜ እና ጉልበተኛ ለሆነው ብሄር ታማኝነታቸውን ለማስመስከር በሌላው ዘር ላይ አሰቃቂ ድርጊቶችን እስከመፈጸም ይደርሳሉ። በአብዛኛውን ግዜ የድርጊታቸው ጽንፈኝነት፣ ክፋት ወይም ጠላትነታቸው ከአንድ ወጥ ዘር <ንጹህ ዘር> ካለው ብሄርተኛ፣ ጽንፍ ከያዘው እንኳን ቢበልጥ እንጂ ያነሰ አይደለም። በዘር ተኮር ግጭቶች ውስጥ ግንባር ቀደም ቦታዎችን ይይዛሉ። በምሳሌነት ላለፉት አመታት በፖለቲካ ድርጅቶች በአመራር ላይ ያሉትን ግለሰቦች እና አክቲቢስቶች ማየት ይቻላል። በግልጽ የትውልድ ሃረጋቸው ከአንድ በላይ ማንነት እንዳላቸው ቢያሳይም እንሱ ግን እራሳቸውን አንድ ብሔር ውስጥ በመቅበር በብሔሩ ተቀባይነትን ለማስመስከር ከልክ ያለፈ መረን የለቀቀ ክፍፍሎችን በመፍጠር ሃገርን እስከመገነጣጠል ድረስ ሲመክሩና ለማስፈጸም ሌት ተቀን ሲደክሙ ይታያሉ። ከራስ ያልታረቀ ማንነት ለሃገርም መቅሰፍት ነው። ይህ የማንነት ቀውስ የቱ ጋ ነው የተፈጠረው? ብሎ መመርመር እጅጉ ያስፈልጋል። በርግጥ ሌሎችም ለዚህ ድርጊት ገፊ ምክንያቶች ሊኖራቸው ይችላል ። የአንዱ ወላጄ ብሄር የሌላውን ወላጄን ብሄር ከብዙ አመታት በፊት በድሎታል ብሎ ሃገር ማመስ ከምን አይነት ስነ ልቦናዊ ውዥቀት እንደሚመጣ አስበውት ያውቃሉ?

5 – ውሕድነትን በአግባቡ አለመቀበል የሚያስከትለው ብዥታ
በአሁኑ ግዜ መሪዎች ከአንድ ሰው ሰራሽ የዘር ክልል ወደ ሌላው ሰው ሰራሽ የዘር ክልል ጥቂት ሰዎችን ይዞ በመሄድ የብሄር በሄረሰቦችን አንድነትን አብሮ መኖርን መቻቻልን አቃፊነትን እንደ አዲስ ለመገንባት ደክመው ሲሰሩ ይታያል። የሚገርመው አብዛኛዎቹ መሪዎች እራሳችው ከብዙ ብሄር የተወለዱ ብቻ ሳይሆኑ አልፈው ተርፈው እራሳችውም ከሌላ ብሄር ሰው ጋር ትዳር መስርተው ወልደው ከብድው የልጅ ልጅ ያዩ ግለሰቦች መሆናቸው ነው ። በታሪካችን ለሺህ አመታት የሁለት ብሄር ህዝቦች አብሮ ለመኖራቸው ፣ ለመጋባታቸው ፣ለመውለዳቸው ቋሚ ምስክሮች ከእንሱ ከራሳቸው በላይ ማምጣት አይቻልም። ሆኖም ሚስጢሩ በማይገባ መልኩ ራሳቸውን በምሳሌነት ከማቅረብ ይልቅ ማንነታቸውን ደብቅው ህዝብን ቀላቀልን የሚል ትያትር መሰል ድርጊቶች በሰፊው ሲሰሩ ይታያሉ። ማንነታቸውን ለመደበቅ ያስገደዳቸው በመረጡት የዘር ፖለቲካ ተጽዕኖ ይሆን? ከሆነ እራሳቸውን ነጻ ያላወጣ መንገድ መከተልን ለምን መረጡ? እውነት ሃገር በዘር ተከፋፍላ ነው ወይንስ በእነሱ ጭንቅላት ውስጥ ነው የፈረሰችው? ለምሳሌ አማራን ፍለጋ ባህርዳር መሄድ ያስፈልጋል? ትግራዋይንስ ፍለጋ መቀሌ? ኦሮሞን ፍለጋስ ባሌ? አማራ ወለጋ፣ ትግሬ ደሴ፣ ኦሮሞ ባሕር ዳር የለም? ለሽርሽር መጥቶ ሳይሆን ወልዶ ከብዶ ተጋብቶ አያት ቅድመ
አያቶቹ እዚያው እትብታቸው ተቀብሮ? ጎጃም ኦሮሞ ካልሆነ ዴንሳ፣ ሜጫ የሚባሉ አውራጃዎች ከየት መጡ? ሸዋ አክሱማዊ ካልሆነ እነ ምድረ ከብድ፣ ዝቋላ፣ ዝዋይ፣ የረር ከየት መጡ? እውነት በሃያ ሰባቱ ዓመታት በትግራይ ውስጥ ከነበረውና ከትግራይ ውጭ ከነበረው ትግራዋይ ቁጥሩ የትኛው ይበዛ ነበር? እና ከትግሬ ጋር አብሮ መኖርን ለማሳየት አዲግራት ድረስ መሄድ ያስፈልግ ነበር? ጎረቤቶች የሉንም?

ሌላው የሚያስደንቀው ደግሞ የህዝብ ቆጠራው በነዚህ ሰው ሰራሽ የዘር ክልሎች ውስጥ በርካታ የተለያዩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጎሳዎች እንደሚኖሩ ያሳያል። ከ5000 በላይ በተሰጣቸው የሰው ሰራሽ ክልል ውጭ የሚኖሩ ህዝቦች በትግራይ ክልል (አማራ ፣ አፋር ፣ አገው ፣ ኦሮሞ ፣ ሌሎች) በአፋር ክልል (አማራ ፣ አርጎባ ፣ ትግራይ ፣ ኦሮሞ ፣ ወላይታ ፣ ሌሎች) በአማራ ክልል (ኦሮሞ ፣ ትግራይ ፣ ጉምዝ ፣ አኝዋክ ፣ ሱማሊ ፣ በርታ ፣ ሌሎች) በሱማሊ ክልል (አማራ ፣ ኦሮሞ ፣ ጉራጌ ፣ ሌሎች ) በቤንሻንጉል ክልል ውስጥ (አማራ ፣ ኦሮሞ ፣ አገው ፣ ትግራይ ፣ ሌሎች) በጋንቤላ ክልል (አማራ ፣ ኦሮሞ ፣ ትግራይ ፣ ሌሎች) በሐራሪ ክልል (አማራ ፣ ኦሮሞ ፣ ጉራጌ ፣ ትግራይ ፣ ሌሎች) ይገኛሉ። በዚህ መረጃ ለዘመናት እነዚህ ሕዝቦች ተቀላቅሎ በመኖር የፈጠሯቸውን ውሕድ ዜጎች መገመት የቻላል። ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ጥቂት ሰዎችን በመውሰድ ለመጀመሪያ ግዜ ይሄ ጎሳ ወደ እዚኛው ጎሳ ክልል የሄደ የሚያስመስሉ ተውኔቶች መተወን ለምን ተፈለገ? ለአንድነት እና ለዘመናት አብሮ ለመኖሩ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑትን በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ውሕዶችን ማሳየት ለምን አልተቻለም ? እውን ኦሮሞ ዘንድሮ ነው ዓባይን የተሻገረው? በአውቶቢስ? አሜሪካኖች በታሪካቸው ላይ የሚቀልዱትን ሰቅጣጭ ቀልድ የሚያስታውስ ነው። ኮሎምበስ አሜሪካን ያገኘ የመጀመሪያው ሰው ነው ብለው ልጆቻቸውን ያስተምራሉ። ብዙ ሚሊዮን ሰዎች ለአእላፍ ዘመናት የኖሩበትን እና እየኖሩ ያሉበትን አገር ኮሎምቦ አንድ ጣልያን ትናንት አገኘው የሚለው ትርክት ካለማወቅ ሳይሆን ከፖለቲካ እና ስነልቡናዊ ስሌት የመነጨ የሰዎችን ሰብዓዊነት የሚክድ፣ ያለፈውን፣ የዛሬን እና የነገን እድል የሚያጨልም ክፋት ነው።
እኛስ ለአእላፋት ዘመናት በኖረች ሀገር፣ ለሺህ ዘመናት አብረው በኖሩ ሕዝቦች መካከል እንዲህ ዓይነት ፌዝ ያስፈልገናል?

ሌላው ውሕድ መሪዎች ከሰው ሰራሽ ክልል ወደ ሰው ሰራሽ ክልል በሚጓዙበት ወቅት ወይንም በአንድ ቦታ በሚሰበሰቡበት ግዚያቶች መቻቻልን እና አንድነትን ለማሳየት ውሕድ ማንነታቸውን ከመግለጽ ይልቅ በባህላዊ ልብስ ለመግለጽ ልዩ ጥረት ሲያደርጉ ነው። ውሕዶች ከብዙ ብሔር እንደ መፈጠራቸው ብዙ ባህላዊ ልብሶችንም ይጋራሉ ። በአንድ ግዜ ከአንድ ባህላዊ ልብስ በላይ መልበስ ስለማይቻል አንዱን መርጦ ለብሶ መውጣት ግድ ነው። የስብስቡ ሃሳብ ግን አንድነትን ማጠንከር ከሆነ እራሳቸውን ሲያስተዋውቁ እኔ የእዚህ የእዚህ የእዚህ ዘር ውጤት ነኝ ብለው ያለባቸውን ዘሮች ሁሉ በዝርዝር ቢያስተዋውቁ በራሳቸው መተማመንን ከማጎልበታቸው በላይ ከሌሎችም ጋር ያላቸውን ጠንካራ ትስስር መስካሪ ይሆን ነበር ። አብሮነታቸው በመቻቻል ሳይሆን በመዋሃድ ፣ በመዋለድ ተሳስሮ የነበረ ፣ አሁንም ያለ እና ለወደፊትም የሚኖር መሆኑንም በቀላሉ ማሳየት ይቻል ነበር።
ውሕድ መሪዎቻችን በውዴታም ይሁን በተጽዕኖ ከዘር ሃረጋቸው አንዱን ብቻ መርጠው ተጠግተው ባገኙት ማንነት ይህ የእኔ ክልል እና ብሄር ሌላውን ክልል ብሄር አቃፊ ነው ሲሉን ምን ማለታቸው ይሆን? እንሱስ እራሳቸው በወጥ ዘር <ንጹህ ዘር> ብለው እራሳቸውን በሚገልጹ ህዘባች ዘንድ አቃፊ ናቸው ወይንስ ታቃፊ? ልክ እንደነሱው በታሪክ አጋጣሚዎች በብዙህ ሺህ አመታት ተዋልዶ የተፈጠረን ውሕድ ህዝብ እንደማንኛውም ወጥ ብሄር የሃገር ባለቤትነቱን ከማረጋገጥ ባነሰ በተለጣፊነት እንዲኖር ለማሳመን ለምን ይሞከራል? ይህ ከራስ አልፎ ሌላውን የሚያኮሰስ ባህሪ በግዜውና በወጉ ያልተስተናገድ የውሕድ ማንነት ችግር ነው ብሎ ማየት ይቻላል? ምን ይመስልዎታል?

6 መሰልን መስሎ መሰባሰብ
የማንነት ጥያቄ በሃገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን በሚሰደዱበት ሃገራትም ጭምር ይታያል። የሰው ልጅ በባህሪው ማንነቱን የመፈለግ እና የመጠጋጋት ጸባይ አለው ቢባል ውሽት አይሆንም። በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከየት ነው የመጣችሁት የሚል ጥቃቄዎችን ይጠየቃሉ። በተለይም አሜሪካን ከተለያዩ ሃገር የመጡ ዜጎችን ያያዘች እንደመሆንዋ መጠን ውይይቱን ለመቀጠል እናንተስ መጀመሪያ ከየት ነው የመጣችሁት ብሎ የአጸፋ ጥያቄ ማቅረብ የተለመደ ነው። በተለይ ነጮቹ በብዛት ይህንን ለመመለስ መቼ በተጠየቅን ብለው ሲጠባበቁ የቆዩ እስከሚመስል ድረስ በደስታ በእናታቸው እና በአባታቸው እስከ ቅድም አያቶቻቸው የወንዱንም የሴቱንም ዘር ይዘረዝራሉ። በብዛት ቤተሰቦቻቸው ወደ አሜሪካን ተሰደው የመጡበትን መርከብ ስም ከነመጡበት ዘመን ጭምር በግልጽ ይናገራሉ። ለዚህ ዝርዝር መልሳቻቸው ነገሮችን በጥልቅ የማስረዳት ችሎታቸው እንዳለ ሆኖ በግልጽነት ማንነታቸውን መቀበላቸው እና መረጃው በአሜካን ዜግነታቸው፣ በመብትና ግዴታቸው ላይ ምንም ችግር አለመፍጠሩን በማወቃቸውም ጭምር ሊሆን ይችላል።

በአሜሪካ በህገ መንግስት ደረጃ ሁሉም ዜጋ ከየትም ይምጣ ከየትም እኩል እንደሰው ስለሚታይም ማንነትን መደበቁ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። (በሕግም ሆነ ከሕግ ውጭ ያለው ዘረኝነት፣ ጭቆና እና መገለል በቆዳ ቀለም ላይ የተመሰረት ስለሆነ ለዚህ ደግሞ ዘር ጥየቃ አያስፈልግም። ይቺ በቅንፍ ትቀመጥልኝ።) በትውልደ ኢትዮጵያውያኖችም መካከል መቼ መጣችሁ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እድሜን ለበደበቅ ካልሆነ በቀር በዜግነት መብት ላይ የሚያመጣው ልዩነት ስለሌለ ያለፍርሃት ሲመልሱ ይታያል። በሃገራችን ላይ ግን አንድን ዘር መቼ ወደዚህ ቦታ መጣህ ተብሎ ቢጠየቅ ጥያቄው ከክልል ባለቤትነት ጋር ሲለሚያያዝ ብዙ አቧራ ያስነሳል። መጤ እና ሰፋሪ መባባል እይተለመደ በመምጣቱ ጥያቄው ባይነሳ ይመረጣል። መቼ መጣህ መቼ ሰፈርክን ያስከትላል። ወራሪ እና ሰፋሪ። ተወራሪ፣ ተባራሪ፣ ተመልሶ ወራሪ፣ ሰፋሪ፣ ከዚያ አባራሪ፣ ወይ ተባራሪ? ማለቂያ የሌለው ውዝግብ ይሆናል።

በአሜሪካ ልዩነት የሚስተናገድው በቆዳ ፣ በአይንና በጸጉር ቀለም በመሳሰሉት ጎልተው በሚታዩ ውጫዊ ገጽታዎች ላይ በመሆኑ ተደባበቆ እና አስመስሎ ለመኖር አያመችም። ከነጭ ከጥቁር ከኤዥያን ከሂስፓኒክ የተወለዱ የውጭው ገጽታቸው የተቀላቀለ የዘር ማንነት እንዳላቸው ይገልጻል። ይህንን ማንነት የያዙ እራሳችውን የሚመስል የማንነት ቦታ ሲፈልጉ ይታያሉ። በግድ ወደ አንዱ ልጠጋጋም ቢሉ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ማግኘቱ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። በምሳሌነት ፕሬዘዳንት ኦባማን መውሰድ ይቻላል። ይህንን ስናይ አለማችን የውሕድ ማንነት ለመቀበል ዝግጁ ነች ወይ ? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን።

የትውለደ ኢትዮጵያዊያን ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው ወደ ኮሎጅ በሚገቡበት ሰአት የማንነት ጥያቄ ይገጥማቸዋል። ነጩ ከነጩ ጋር ጥቁር አሜሪካዊው ከጥቁር አሜሪካዊው ጋር ሲሳሳብ የራሳቸውን ማንነት የሚገልጽ ቡድን ይፈልጋሉ ። በኮሎጆች ውስጥ በባህል መጠጋጋት ላይ መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያዊያን እና የኤርትራዊያን የተማሪ ማህበር መስርተው በራሳቸው ዙሪያ ሲሰባሰቡ ይታያሉ። በቤተስቦቻቸው የብሄር ልዩነት እንዳለ እንኳን የሚነገራቸው ለልዩነት ቦታ ሳይሰጡ በአብሮነት ሲተጋገዙ በብዛት ይታያል።

በአሜሪካ ዲሞክራሲ አድጓል በሚባልለት ሃገር እና በህግ የግለሰብ ማንነት በተረጋገጠበት ቦታ ላይ እንኳን ሰዎች የሚመስላቸውን ዘር ፈልጎ መጠጋት ይታይባቸዋል። ሰው ከሚመስለው ጋር መሆኑ በእርሱነቱ የሚያደርሱበትን ማህበራዊ ችግሮችን በጋራ ለመፈታት አልፎም ማንነቱን የገነባውን ባህል ለመጠበቅ ይረዳዋል።

ውሕድ በማንነቱ ምክንያት ሊደርሱበት የሚችሉ ጉዳዮችን በግልጽ መነጋገር ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ ድርስ የሚጫንበትን የማንነት ቀውስ በመጠኑ ይቀንሳል። ሃሳብን በጋራ መወያየት በራስ መተማመንን ከመገንባትም በላይ በጋራ የምንኖርባትን ሃገራችንን ለውሕድ ተስማሚ ቦታ ለማድረግ ከፍተኛ ድርሻ አለው። የውሕዶች ሃገር ሙሉ ኢትዮጵያ እንደሆነች ለማሳወቅም ይረዳል።

በዚህ ጽሁፍ ላይ በግርድፍ የተነሱ ሃሳቦችን በጥልቅ እስከምንመለስባቸው ድረስ እናንተም አስቡባቸው።

ቸር ይግጠመን


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV