የህክምና ሙያ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመለሱ ተባለ

ትምህርት አቋርጠው የነበሩ አብዛኛዎቹ የህክምና ሙያ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሳቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የመጨረሻ አመት (ኢንተርን) ተማሪዎችና ስፔሻሊቲ (ሬዚደንት) ተማሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ከተወያዩ በኋላ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።

መንግስትም ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።

ይሁን እንጅ በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ባለፉት ቀናት ትምህርታቸውን አቋርጠው እንደነበርም በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ሚኒስቴሩም ከዛሬ ጀምሮ ወደ ትምህርት ገበታቸው በማይመለሱ ተማሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ መግለጹ የሚታወስ ነው።

በዛሬው እለትም ትምህርት አቋርጠው የነበሩ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ መመለሳቸውን ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው ከዛሬ ጀምሮ ወደ ትምህርታቸው በማይመለሱ ተማሪዎች ላይም ተቋማት ባላቸው የአካዳሚክ ህግ እርምጃ እንደሚወስዱም ነው የተናገሩት።

የመጨረሻ አመት የህክምና ተማሪዎች ላነሷቸው ጥያቄዎችም በዝርዝር አጥንተው ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጡ ግብረ ሃይሎች ተቋቁመዋልም ነው ያሉት።

ግብረ ሃይሎቹ በዛሬው እለት በቢሾፍቱ እየተወያዩ ሲሆን፥ በሳምንቱ መጨረሻ የጥናት ግኝታቸውን ለሚኒስቴሩ እንደሚያቀርቡ አስረድተዋል።

FBC