ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል የሚያስችል አዲስ መድሃኒት በስኬታማ ሁኔታ ተሞከረ

ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል የሚያስችል አዲስ መድሃኒት በስኬታማ ሁኔታ ተሞከረ
በሚመጣው እሁድ ወይም በጎርጎሮሲያኑ ታህሳስ 1 ቀን የዓለም የኤድስ ቀን ታስቦ ይውላል። በሽታው በ1980ዎቹ መጀመሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም በመስፋፋቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተህዋሲው የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል። ይሁንና ኤች አይ ቪ ኤድስ አሁንም አልጠፋም። የሙያው ተመራማሪዎች አሁንም መድሃኒት ፍለጋውን ቀጥለዋል። በየሳምንቱ በጤና ጉዳይ ላይ የሚዘግበው “ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲስን” ይፋ እንዳደረገው ሌናካፓቪር (Lenacapavir) የተባለ መድሃኒት በየስድስት ወራት መከተብ በ ኤችአይቪ ተህዋሲ መያዝን በተሳካ ሁኔታ ይከላከላል። በአሁኑ ጊዜ ኤች አይ ቪን ለመከላከል በተህዋሲው የተያዙ ሰዎች በየቀኑ መድሃኒት መወሰድ ግድ ይላቸዋል። ይሁንና አዲሱ የሌናካፓቪር ሕክምና በዓመት በሰው 42,000 ዶላር ያህል ወጪ ስለሚያስወጣ እጅጉን ውድ ነው ተብሎለታል።
እንደ ተባበሩት መንግስታት የኤድስ ፕሮግራም UNAIDS ባለፈው የጎርጎሮሲያውያን ዓመት 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በኤች አይ ቪ ተህዋሲ ተይዘዋል። 630,000 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ የኤድስ ታማሚዎችን ይበልጥ በሚያጠቁ በሽታዎች ሞተዋል። ለንፅፅር ከ 20 ዓመት በፊት በበሽታው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 2.1 ሚሊዮን ነበር።