የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር ሺመልስ አብዲሳ ክልሉ ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች በፋኖ ታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የመንግሥት ኃይሎች እንዳይከላከሉ በዋናነት እንቅፋት የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አማጺዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው ሲሉ ትላንት በነቀምት ከተማ በተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ተናግረዋል።
ሽመልስ ከዚህ ቀደም በምሥራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ በምሥራቅ ሸዋ እና በቅርቡ ደሞ በሰሜን ሸዋ ዞኖች “ጽንፈኛ” ሲሉ የጠራቸው የፋኖ ታጣቂዎች ለሚፈጽሟቸው ጥቃቶች በዋናነት ኃላፊነቱን የሚወስደው ኦሮሞን ነጻ አወጣለው ብሎ የሚንቀሳቀሰው አማጺ ቡድን ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የተባሉት ኃይሎች የፋኖ ታጣቂዎች ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች አይጠጉም ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ራሱን እንዳይከላከል አስቀድመው ትጥቅ በማስፍታት ለጥቃት ያጋልጡታል በማለት ከሰዋል።
ኹለቱ ኃይሎች የጥፋት ሥራቸውን ተናበው እንደሚሠሩ በመግለጽም፣ መንግሥት አማጺዎቹን ከከልሉ በቅርብ ቀናት በማጥፋት ሰላምን እንደሚያረጋግጥ ቃል ገብተዋል።