በኢትዮጵያ ያለው ግጭት ከዩክሬን፣ ጋዛ እና ሱዳን ጦርነት ጋር ሲተያይ ‘የተሻለ ነው’ የሚያስብል ነው?

(መሠረት ሚዲያ)– ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከሰሞኑ ባለሐብቶች በተገኙበት አንድ የውይይት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ያለው ግጭት በዩክሬን፣ ጋዛ እና ሱዳን ካለው ጦርነት ጋር ሲተያይ ‘የተሻለ ነው’ ማለታቸው ተሰምቶ ነበር።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠቀሷቸው አገራት ያለውን ሁኔታ እና የቁጥሮችን ንጽጽር እንመልክት፡

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት:
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ቢሮ መረጃ እስከ የካቲት 2024 ድረስ በዩክሬን ውስጥ ወደ 3.7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሲሆን ወደ 6.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ደግሞ አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል። የተመድ ሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ፅህፈት ቤት እንደገለጸው እስከ የካቲት 24 ድረስ 11,600 ገደማ ንፁሀን ዜጎች ተገድለዋል፣ ከእነዚህ ውስጥ 600 ገደማ የሚሆኑት ህጻናት ናቸው። የአሜሪካ ኮንግረስ ያወጣው አንድ መረጃ ደግሞ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ተዋጊዎች ከሁለቱም ወገን በጦርነቱ ሞቷል።

የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት
እንደ Council on Foreign Relations መረጃ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እስካሁን 15 ሺህ ገደማ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 8.2 ሚልዮን ሰዎች ተሰደዋል፣ ይህም አሁን ላይ በአለማችን ትልቁ የስደተኞች ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል። አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ ቻድ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ተሰደዋል።

የእስራኤል- ሀማስ ጦርነት:
በእስራኤልና ሐማስ ጦርነት ምክኒያት ከ40,000 በላይ እጅግ የሚበዙት ፍልስጤማውያን የሆኑ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 92,401 ቆስለዋል፣ 2.3 ሚሊዮን ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።

የኢትዮጵያ ግጭት
የዛሬ አራት አመት ገደማ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት በክፍለ ዘመኑ ከተደረጉ እጅግ አሰቃቂ ጦርነቶች አንዱ እንደሆነ መረጃዎች ያስረዳሉ፣ ከ600 ሺህ እስከ 800 ሺህ ህዝብ ህይወት እንደቀጠፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁንና ለዚህ ንፅፅር ይህን በፕሪቶርያ ስምምነት የቆመ ጦርነት ወደጎን አድርገን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩበት መንፈስ አሁን እየተደረጉ ያሉ ግጭቶችን እንመልከት።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች፣ በተለይም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል እየተካሔዱ ያሉ ግጭቶች 4.4 ሚሊየን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እንዳስከተሉ አለም አቀፉ የተፈናቃዮች ድርጅት IOM መረጃ ያመለክታል፡፡ የዘንድሮውን ሳይጨምር በፈረንጆቹ 2023 በትንሹ 1,251 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መግስታት ደርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ተፋላሚዎች ላይ እየደረሰ ያለ የጉዳት መጠንን በተደራጀ መልኩ ማግኘት ባይቻልም በመንግስት አካላት እና በታጣቂዎቹ የሚለቀቁ መረጃዎች በርካቶች በየቀኑ ህይወታቸውን እያጡ እንደሆነ ያሳያል (መረጃዎቹ ግነት ወይም ቅነሳ ሊኖርባቸው ቢችልም)። በሁለቱ ክልሎች አሁን ድረስ በቀጠለው ግጭት በርካቶች እየተፈናቀሉ፣ እየተገደሉ፣ እየታገቱና የወሲብ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ የረድኤት ሰራተኞች ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ በየእለቱ የሚሞቱ፣ የሚቆስሉ፣ የሚሰደዱ እና የተለያየ ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎችን ቁጥር ለማወቅ ቢያዳግትም በአለማችን በከፍተኛ ቴክኖሎጂ በተደገፈው እና በሐያላን አገራት ገንዘብ፣ መሳሪያ እና ሞራል ድጋፍ በሚደረግበት በእስራኤል – ሐማስም ሆነ፣ ሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት የሞተው ሰው ቁጥር በኢትዮጵያ እየተከሰተ ካለው የሞት እና መፈናቀል ቁጥር ጋር ተቀራራቢ ሊባል የሚችል እንደሆነ እነዚህ መረጃዎች ይጠቁማሉ።