ከእንረዳዳ የሸማቾች ማህበር ለልማት በሚል የተወሰዱ ሁለት የመሬት ይዞታዎች በአዲሶቹ ባለቤቶች በደላላ በኩል ለሽያጭ ቀረቡ

ከእንረዳዳ የሸማቾች ማህበር ለልማት በሚል የተወሰዱ ሁለት የመሬት ይዞታዎች በአዲሶቹ ባለቤቶች በደላላ በኩል ለሽያጭ ቀረቡ

(መሠረት ሚድያ)– ቦሌ አትላስ አካባቢ ከሚገኘው ከእንረዳዳ የሸማቾች ማህበር ተወስደው ለአንድ ግለሰብ እና ለሌላ ድርጅት ‘ለልማት’ በሚል ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተሰጡ ሁለት የመሬት ይዞታዎች በአዲሶቹ ባለቤቶች በደላላ በኩል ለሽያጭ መቅረባቸውን መሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።

ከ1969 ዓ/ም ጀምሮ በማህበሩ ይዞታ ስር የቆዩትን እነዚህ ሁለት ቦታዎች ለባለሀብቶች ልቀቅ የተባለው የእንረዳዳ የሸማቾች ህብረት ቦታውን ለቆ የወጣው ከአንድ ወር ተኩል በፊት ነበር።

ከ220 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ንብረት ሆኖ ሲተዳደር የቆየው ይህ የሸማቾች ህብረት አንደኛው 5,000 ካሬ፣ ሌላኛው ከ2,000 በላይ ካሬ የሆኑ ቦታዎች ነበሩት።

እነዚህን ቦታዎች በግዢ የተረከቡት አቶ ታደለ ገመቹ በ91 ሚልዮን ብር፣ ሌላኛው ለአኮርዲያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በ175 ሚልዮን ብር በሊዝ መሸጡ የታወቀ ሲሆን እኚህ ግለሰብ እና ይህ ድርጅት አሁን መሬቱን ከፍ ባለ ገንዘብ ለመሸጥ በደላላ በኩል እንቅስቃሴ መጀመሩን መሠረት ሚድያ ሰምቷል።

በዚህም ከደሳለኝ ሆቴል ጀርባ ያለው መሬት እስከ 160 ሚልዮን ብር እንዲሁም ሁለት ሬስቶራንቶች የነበሩበት 5,000 ካሬ ገደማ ግቢ ደግሞ 265 ሚልዮን ብር እየተጠየቀባቸው እንደሆነ ታውቋል።

አሁን የፈረሰውን የማህበሩን ህንፃ ተከራይተው የሚገኙ እና በአመት 50 ሚልዮን ብር ግምት ያለው ታክስ ሲከፍሉ የነበሩ፣ ከ200 በላይ ሰራተኛም ሲያስተዳድሩ የቆዩት ሴቨር እና ናታን የተባሉ ሬስቶራንቶች በስፍራው ይገኙ ነበር።