- ” በረራውን ለማቋረጥ የተገደድኩት ገንዘብ እንዳላንቀሳቅስ በመታገዴ ነው ” – የኢትዮጵያ አየር መንገድ
የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚያደርገው በረራ ከመስከረም 20፣ 2016 ዓ.ም ጀምሮ እንዲቆም የሚያሳውቅ ደብዳቤ ጽፎ እንደነበር ይታወሳል።
ዛሬ አየር መንገዱ በሰጠው መግለጫ ውሳኔው ይሻሻላል በሚል ሲጠብቅ እንደነበር እና የኤርትራ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንን ለማናገር በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ አለማሳካቱን አስታውቋል።
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በመግለጫው እንደጠቀሱት በአስመራ የሚገኘው ተወካያቸው ከሽያጭ የተሰበሰበ ገንዘብ ለማስገባት ሲል ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ መላክ እንደማይቻል ተነግሮታል። ይህ የሆነው ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ አማካኝነት ነው።
” ‘ ከነሐሴ 25/ 2016 ዓ.ም በኋላ ሂሳባችሁ ታግዷል ለሀገር ውስጥ ወጪም (oppration fee) መጠቀም አትችሉም ‘ መባሉን ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ በረራውን ለማቋረጥ ተገደናል። የበረራ ወጪያችንን መሸፈን ባለመቻላችን ተገደን ወጥተናል ” ሲሉ ነው የገለጹት።
አየር መንገዱ እንዳያንቀሳቅስ የታገደበት ገንዘብ መጠን ስንት ነው ?
ይህ ጥያቄ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የገንዘቡን መጠን ከመግለጽ ተቆጥበው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አየር መንገዱ በኤርትራ ሁለት አካውንት እንዳለው የገለጹት አቶ መስፍን፥ አንዱ የናቅፋ አካውንት ሲሆን የቆየ እንዲሁም ወደ ዶላር መቀየር ያልተቻለ የማይንቀሳቀስ የሂሳብ አካውንት መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው የባንክ አካውንት ደግሞ የዶላር ሲሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኬት ሲሸጥ የነበረው በውጭ ምንዛሬ መሆኑን ገልጸው ይህንን ገንዘብም እገዳው እስከተላለፈበት ቀን ድረስ በተለያዩ ጊዜዎች ገንዘቡን ሲያንቀሳቅስ እንደነበረ ገልጸዋል።
” የበረራ እገዳውን ካወጡብን በኋላ ነው Block ያደረጉብን ” ሲሉ ነው የገለጹት።
አቶ መስፍን አክለውም ፥ “ለእኛ ገንዘቡ ካልተለቀቀልን ከዚህ በኋላ የሁለቱ ሀገራት ጉዳይ ነው የሚሆነው ” ሲሉ ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ለሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን እና ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቃቸውን ገልጸዋል።
” አየር መንገዱ ከኤርትራ የወጣው ተገዶ ነው ” ያሉት አቶ መስፍን ዋናው ችግሩ ለምን እንደታገድን አለማወቃችን ነው፤ በተጻፈው ደብዳቤም ላይ ምንም የተገለጸ ነገር የለም ብለዋል።
” ከዚህም በተጨማሪ በደብዳቤም በስልክም ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም ” ሲሉ ገልጸዋል።
የአየር ቀጠናውን አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሁን ባለው ሁኔታ በኤርትራ የአየር ክልል መብረር እንዳልተከለከሉ ገልጸው የሚያስገድድ ጉዳይ ካለ ግን አማራጭ መጠቀም እንደሚችሉ አንስተዋል።