ሱማሊያና ግብጽ የምድር፣ የአየርና የባሕር ኃይሎች ወታደራዊ ልምምድ ሊያደርጉ ነው

ሱማሊያና ግብጽ በሱማሊያ ግዛት ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ በመዘጋጀት ላይ እንደሆኑ ተገለጸ

ሱማሊያና ግብጽ በሱማሊያ ግዛት  ውስጥ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ በመዘጋጀት ላይ ስለመሆናቸው የሱማሊያ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

በመስከረም ወር ይካሄዳል በተባለው በዚህ ወታደራዊ ልምምድ፣ የሁለቱ አገራት የምድር፣ የአየርና የባሕር ኃይሎች እንደሚሳተፉ ዘገባዎቹ ጠቁመዋል።

ሁለቱ ሀገራት እናደርገዋለን ያሉት ወታደራዊ ልምምዱ በትክክል መቼ እንደሚጀመር፣ ምን ያህል ወታደሮች እንደሚሳተፉበትና ለምን ያህል ቀናት እንደሚቆይ የዜና ምንጮቹ አልጠቀሱም።

ሁለቱ ሃገራት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ መወሰናቸው የተገለጸው፣ ግብጽ ወታደሮቿንና ጦር መሳሪያዎችን ወደ ሞቃዲሾ በላከችበት ማግስት ነው።

የሁለቱ ሀገራት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እናደርጋለን ይፋ የተደረገው ግብጽ የናይል ወንዝ ድርሻዋን ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንደምትወስድ በገለጠችበት ወቅት መሆኑም አይዘነጋም።

በዚህ ጉዳይ ላይ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ በኩል የተባለ ነገር ባይኖርም ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ እንደማትመለከት አሳውቃ ፤ በቀጣናው የብሄራዊ ደህንነቷን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ በንቃት እየተከታተለች እንደሆነም አመላክታለች።