በጎንደር ከተማ ታግታ የነበረች የሁለት አመት ህፃን በጭካኔ መገደሏን የተቃወሙ ነዋሪዎች በፀጥታ አካላት ጥይት ተመቱ

  • በጎንደር ከተማ ታግታ የነበረች የሁለት አመት ህፃን በጭካኔ መገደሏን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ
  • – ግድያውን በመቃወም ሰልፍ የወጡ በርካታ ሰዎች በጥይት ጉዳት ደረሰባቸው

(መሠረት ሚድያ)– ባሳለፍነው አርብ ነሀሴ 24 ጎንደር ከተማ ውስጥ ከታገተች በኋላ እስከ ትናንት ድረስ በየመንገዱ እና በየቤተክርስቲያኑ ገንዘብ ሲሰበሰብላት የነበረችው የሁለት አመት ህፃኗ ኖላዊት ዘገዬ በአጋቾች በጭካኔ መገደሏን የከተማው ነዋሪዎች ለመሠረት ሚድያ ተናገሩ።

በጎንደር ከተማ ቀበሌ 03 (ደብረ ብርሃን ስላሴ ሰፈር) የታገተችው ህፃን ኖላዊት ቤተሰቦች የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል ስላልቻሉ ከህዝብ ሲያሰባስቡ ቆይተው በመጨረሻ ቢከፍሉም “ክፍያውን አዘገያችሁ” ያሉት አጋቾች ህፃኗን እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ ገድለው ቤተሰቦች ደጃፍ መጣላቸው ታውቋል።

“ብሩን ከተቀበሉ በኋላ ህፃኗን ገድለው ጥለዋት አስከሬኗን ተቀብለን ከባድ ሀዘን ላይ ነን” ያለ አንድ ነዋሪ የከተማው ነዋሪ መላ የከተማው ህዝብ ሀዘን ላይ እንዳለ ገልጿል።

አባት የህፃኗን አስከሬን በመያዝ “ፍረዱኝ” ብሎ ዛሬ ቀትር አካባቢ አደባባይ የወጣ ሲሆን አባትየውን የተቀላቀሉ ነዋሪዎች ከፀጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት በርካቶች እንደተመቱ ታውቋል፣ ህይወታቸው እንዳለፈ የጠቀሱም አሉ።