ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እድሜ ልክ እና 15 ዓመት ከሚያስፈርዱ ሁለት ክሶች ነፃ ተባለ !
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሐምሌ 2014 ዓ.ም. “ጥብቅ የመከላከያ ሠራዊትን ምስጢር ማባከን”፣ “መከላከያ ሠራዊቱን መከፋፈል” እና “የመከላከያ ሠራዊቱን ስም ማጥፋት” የሚሉ ሦስት ክሶች ተመስርተውበት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆኖ ለስድስት ወራት በእስር ላይ ነበር።
ሆኖም ግን ፤ በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሕገ-መንግሥት እና የሽብር ወንጀል ችሎት ሰብሳቢ የሆኑት የተከበሩ ዳኛ ዘላለም ተስፋዬ እና የተከበሩ የቀኝ ዳኛ ወ/ሮ ሐረገውይን ተክሉ ተሰይመው የመጀመሪያ እና ሁለተኛውን ክስ ውድቅ አድርገው፣ ሦስተኛው ክስ ደግሞ አንቀጽ ተቀይሮ እንዲከላከል በመወሰናቸው ከወህኒ ቤት በዋስ መፈታቱ ይታወሳል፡፡
ይሁንና፣ የፌደራል መንግሥት ዓቃቢ ሕግ ጋዜጠኛው ነፃ የተባለባቸው ከ15 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እና ከ10 እስከ 15 ዓመት ከሚያስፈርዱበት ሁለት ክሶች “ነፃ መባል አልነበረበትም” በሚል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የይግባኝ ቅሬታውን አቅርቧል፡፡ ጋዜጠኛውም በጠበቃዎቹ ቤተማርያም አለማየሁ እና ሄኖክ አክሊሉ በኩል ሲከራከር ቢቆይም፣ ጉዳዩን እየመረመረው በነበረው በአቶ ሽምሱ ሲርጋጋ ሰብሳቢነት የሚመራው ችሎት ላይ “የዳኛ ይቀየርልኝ” ጥየቄ አቅርቦ ውድቅ ተደርጎበት ነበር፡፡
ይህም ሆኖ፣ በወርሃ ሚያዚያ 2016 ዓ.ም ሦስቱም ዳኞች ተቀይረው፣ በምትካቸው ሰብሳቢ የተከበሩ ዳኛ ምጽላል ኃይሌ፣ እንዲሁም የተከበሩ ዳኛ ከበቡሽ ወርቁ እና የተከበሩ ዳኛ ኡመር መሐመድ የግራ እና ቀኝ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል፡፡
በትናንትናው እለት ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም በተከበሩ ዳኛ ምጽላል ኃይሌ ሰብሳቢነት የሚመራው ችሎት “የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ትክክልና የሚነቀፍ ሆኖ ስላላገኘነው ጋዜጠኛው በነፃ እንዲሰናበት የተሰጠው ውሳኔ ጽንቷል” በሚል ፍርድ ሰጥተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ፣ የዚህ ዜና ዘጋቢ ጋዜጠኛውን “ውሳኔው የፍርድ ቤቶችን ገለልተኝነት ያሳያል ወይ?” ብሎ ላቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ “ፈጽሞ አያሳይም” ካለ በኋላ፤ “ለእኔ እውነተኛ ዳኝነት የሰጡኝ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኞችም ሆኑ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ለህሊናቸው ታማኝ እና ፍትሃዊ በመሆናቸው፣ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ጠንካራ በመሆናቸው ብቻ የመጣ ውጤት ነው፡፡ በተረፈ፣ ከእነዚህ ጥቂት ዳኞች በቀር፣ ፍርድ ቤት ላይ ፈጽሞ እምነት የለኝም፤ ገለልተኛም ነው ብዬ አላምንም፡፡ እንደተቋም ብዙ የሚያሳዝኑ ጉዳዮች አሉ፤” ብሏል፡፡
ይድነቃቸው ከበደ