እኛ አብይን የደገፍነው እንደልባችን መናገር፣ መቃወም፣ መተቸት ስላስቻለን ነው – ሩታ አለሙ

መረጃ ቲቪን ሰብስክራይብ በማድረግ ወቅታዊ ዜናዎችን፣ ትንተናዎችን፣ የኪነጥበብ ፕሮግራሞችን እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ማግኘት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

ሩታ አለሙ

በለገጣፎ ጉዳይ ዶ/ር አብይ ተቃውሞ ገጠመው ብለው የሚፈነጩ የህወሃት አክቲቪስቶችን እዛም እዚህም እያየን ነው!

እኛኮ አብይን የደገፍነው… በሀብት ላይ ሀብት ስለደረበልን አይደለም… ከህወሃት ዘመን በተለየ በቀን ሶስቴ ጠግበን መብላት ጀምረን አይደለም… መንገድና ህንፃ በመገንባትማ መለስ ተወቅሶበት አያውቅም። እኛ አብይን የደገፍነው እንደልባችን መናገር፣ መቃወም፣ መተቸት ስላስቻለን ነው!

ለውጥማ ድብን አድርጎ አለ!!

በፊትም ወጣት በጅምላ ይታፈስ ነበር። አሁንም ሲታፈስ አይተናል… ቢያንስ ግን ለምን ታፈሱ ብለን ኡኡ ብሎ የመጮህ መብት አለን ዛሬ። የህዝብን ጩኸት ፈርቶ እርምጃውን የሚያርም፣ የታሰሩት የሚፈታ መሪ አግኝተናል።

በፊትም የዜጎችን ቤት አፍርሶ ጎዳና የሚጥል መንግስት ነበረን። አሁንም ነገሩ ሲደገም እያየን ነው። ነገር ግን ዛሬ ለምን ቤት ፈረሰ ብለን በመፃፋችን እስርና እንግልት ይደርስብናል ብለን አንፈራም። ተዘቅዝቀን አንገረፍም። ብልታችን ላይ ኮዳ አይንጠለጠልም!

በፊትም መንግስትን ተቃውሞ ህዝብ ሰልፍ ይወጣ ነበር። ዘንድሮም እንደዛው። ዘንድሮ ግን ባዶ እጁን ሰልፍ የወጣ ህዝብ ላይ ጥይት አይተኮስም። በፖለቲካ አቋሙ ምክኒያት ህዝብ በሽብርተኝነት አይፈረጅም። ብሄር ከብሄር እያጣላ ዘመኑን የሚያረዝም ተንከሲስ መንግስት የለንም። ቢያንስ ቦታው ላይ ያሉ ሰዎች ሀገራቸውን ይወዳሉ። ሀላፊነት ይሰማቸዋል።

በፊትም ምርጫ ነበረን፤ ዘንድሮም ይኖረናል! መቶ ፐርሰንት የሚመረጥ መንግስት እንደማይኖረን ግን እርግጠኞች ነን። አንጭበረበርም። አንታለልም።

አብይን የደገፍነው እንደልቡ እንድንቃወመው ስለፈቀደልን ነው። ሲያጠፋ እንወቅሳለን። ሲያለማ እናመሰግናለን። ጥፋቱ ከልማቱ ከበለጠብን በምርጫ በክብር እናወርደዋለን። ይሄንን ማድረጉ በራሱ በታሪክ መዝገብ ላይ ስሙን አድምቀን እንድንከትበው ያደርገናል!

ቅር ስንሰኝ መንግስትን መቃወም ወላዋይነት አይደለም። መብታችንን የምናስጠብቅበት መንገድ ነው። መንግስትም ቢሆን እጅ እግራችንን ሰብስበን እንድናመልከው አይጠብቅብንም!

ስለዚህ (ድሮ እኛን ትጠሩበት በነበረው ስያሜ ልጥራችሁና) እናንት “የድሮ ስርአት ናፋቂዎች”… የአብይ መንግስት ሺ ጊዜ ቢበድለን ወያኔ ማሪን የምንልበት ጊዜ ፈፅሞ አይመጣም!!

መንግስትን ስንተች ትሻለን ፍለጋ እንጂ ትብስን ናፍቀን አይደለም። ስንቃወም እንኳ እየደገፍን ነው!