" /> በእንተ ለገ ጣፎ ወለኩላ ኢትዮጵያ – አምሃ ልዑልሰገድ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

በእንተ ለገ ጣፎ ወለኩላ ኢትዮጵያ – አምሃ ልዑልሰገድ

ከአምሃ ልዑልሰገድ

መማር ማወቅ መጠየቅ መረዳትና መመርመር ለባለጌ እንዳልተሰጡ በግልጥ ያሳየን የትናንቱ ገቢረ ጣፎ ነው። በቀዬአችን ተክለው ያሳደጉትን ዛፍ ለሥራ ፈልገው ሊቆርጡ የወጡ ገበሬዎች ብዙ የወፍ ጎጆ ከተመለከቱበት ሳይቆርጡ ያልፉታል። የዛፉ መቆረጥ ግድ ቢሆን እንኳ ለሥራ በማይውል ጠማማ ወይም ለመቆረጥ ወዳልተመረጠ ዛፍ የወፎቹን ጎጆ አዘዋውረው ይቆርጡታል።

ልማት በሰው ለሰው የሚከወን ካልሆነ ምን ፋይዳ አለው? እንኳን ለሰው ለፍጥረት ሁሉ ተስማሚ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ የተሰራው የእስከዛሬው ልማት ለምን አላስተማረንም? አዲስ አበባ እኮ ከማዘጋጃው ፈጥኖ ጥንቧን የሚያነሳላት የዱር አውሬ ነበር እንደ ዛሬው የብሎኬት ደን ሳይከባት በፊት። ስለዚህ ልማታችን ለፍጥረት ሁሉ ተስማሚ ካልሆነ ልማት ሳይሆን ጥፋት ነው። እሱ ነው ሕገ ወጥነት። ይሔንን አሰራራችንን ነው በሐሳብ ዶዘር ማፍረስ ያለብን። እንጂማ ሰውን እያፈረስን ለማነው የምንገነባው?

ሕገ ወጥ ማለት ምን ማለት ነው? ማነው ማንን ሕግ አክባሪ እና ሕግ አስከባሪ የሚለው? ስለ ሕግና ሕጋዊነት ምንም የማያውቁ ከአስተዳደጋቸው ጀምረው ጋጠወጦችና ነጣቂዎች ሆነው በንፍገትና በስግብግብነት ያደጉ ጥቂቶች በሕዝብ ውክልና ለኃላፊነት ሳይሆን በብልግና ልኬት የተሾሙ ጠማሞች ብዙሃኑን ሲያስለቅሱ ሲገድሉ ዝም የሚል ሰው አይኑር። በሃይማኖትም፣ በመንግስትም ይሁን ሰው በመሆን ሥልጣን የምንገኝ ከግፉአን ጋር ብንገፋ የሚሻለውን እናገኛለን። “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንዲሉ ለግፈኞች ያላቸው አጭር ጊዜ ስለሆነ በዚህ ግፋቸው እንዲቀጥሉ እድል አንስጥ።

ከትናንት መማር ያልሆነለት የሐገሬ ሰው ዛሬም ትናንትን እየደገመ ነገ ላለመኖር በመሥራት ተጠምዷል። ሕሊና አለን የምትሉ ባለሥልጣናት የየትኛውም እምነት መሪዎች እባካችሁ ግፍ ይብቃን ተው በሏቸው። የግፍ ጽዋችሁ ሞልቶ የፈሰሰለት … በሏቸው። የተማራችሁ አስተምሩ። የተመከራችሁ ምከሩ። የተገሰጻችሁ ገስጹ። በዚህም አልስተካከል ያላችሁን ምድሪቷን የበለጠ እንዳያጎሰቁል ፈጣሪ ይወስደው ዘንድ አስቸግሩት። ምናልባት እዛ ይስተካከላል!


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV