የኦሮሞ ብሄረተኞች ከአገር አልፈው ለአህጉር የበቁትን ወደ ጎጥ እያወረዷቸው ነው #ግርማካሳ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ለኦህዴድ/ኦዴፓ ቅርበት አለው የሚባለው ጦማሪ፣ ደረጄ ገረፋ ቱሉ(፣ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ላይ ብእሩን አንስቷል። “ቴዎድሮስ ፀጋዬ በርዮት የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩን በተመለከተ አዲስ መረጃ ይዘናል በሚል የተክደናል እና ተታለናል ረጅም ሙሾ አውርዷል” ሲል ጦማሩን የጀመረው ደረጄ ፣ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ባልተጣራ መረጃ ላይ አስተያየት እየሰጠ እንደሆነ ነቅፏል።

ስለ ዶ/ር አብይም ደረጃ ሲጽፍ አንደኛ ዶክተር አብይ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ያላቸው ፅኑ አቋም እና ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅር፣ ሁለተኛ ለገዳ ስርዓት ያላቸው አድናቆትና የገዳ ስርዓት እሴቶች ለሀገር ግንባታ እና ለህዝቦች ወንደማማችነት በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ደጋግመው ስለመናገራቸው፣ ሶስተኛ ስለ አፋን ኦሮሞ እና ሌሎች ቋንቋዎች በሀገራችን በተጨማሪነት በሁሉም አከባቢ በስራ ላይ መዋል ለሀገር አንድነት ትልቅ እንዳለው እንደሚያምኑ ይነገርናል።

ስለ ዶ/ር አብይ ያስቀመጣቸው ሶስቱ ነጥቦች ላይ ብዙም የሚከራከር ይኖራል ብዬ አላስብም። ጋዜጠኛ ቴዎድርስ ጸጋዬም ሆነ ሌሎች እያነሷቸው ያሉ መሰረታዊ ሌሎች ጥያቄዎች ግን አሉ፣ እስከ አሁን ዶክተር አብይ ለመመለስ ፍቃደኛ ያልሆነባቸው።

ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ላይ ትችት ስናቀርብ ፣ አንድ መረሳት የሌለበት ትልቅ ጉዳይ ቢኖር፣ ቴዎድሮሶ ጸጋዬ በግልጽና በአደባባይ ዶክተር አብይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያላቸውን አቋም ምን እንደሆነ ጠይቆ፣ ዶክተር አብይ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን በሚል ምላሽ ለመሰጠት ፍቃደኛ እንዳልነበሩ ነው። ጦማሪ ደረጄም ሆነ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ላይ ትችት የሚያቀርቡ ወገኖች “ለምን ተጠየቀ? ለምን ተጻፈ? …” በሚል ዜጎች ጥያቄ በማንሳታቸው መከፋት ሳይሆን እንደውም ለሚነሱ ጥያቄዎች ግልጽ ምላሽ እንዲሰጥ እነርሱም ግፊት ማድረግ ነበር የሚገባቸው።ምን ጊዜም የተሸፋፈነ ነገር አያዋጣም። ግልጽነት አስፈላጊ ነው።

በዚህ አጋጣሚ ለጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ያለኝን አድናቆት መግለጽ እወዳለሁ። ብዙዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ተቃዋሚ ነን ባዮች ፣ ከባለ ዘመኖች ጋር አብረው በሚያጨበጭቡበት ወቅት፣ የዶ/ር አብይን ስም እየጠሩ በሚምሉበት ወቅት፣ ህዝብ መረጃ እንዲኖረው ለማድረግ የሚሰሩ፣ የሚጠይቁ፣ የማይፈሩ ጋዜጠኞች ትልቅ ክብር ይገባቸዋል።

ከሁለት አመት በፊት፣ ጠቅላይ ሚኒስተር ሳይሆኑ፣ ዶ/ር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ ዙሪያ ወደ ተናገሩት ስንመለስ ፣ አንድ ልናሰምርበት የሚገባ ነጥብ ቢኖር ቪዲዮዉን የለቀቁት ኦህዴዶች መሆናቸውን ነው። ዶክተር አብይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ከዚህ በፊት ተጠይቀው መልስ እንዳልሰጡበት እያወቁ፣ ዶክተር አብይን ወደ ጥግ ለመግፋት፣ on the defensive ለማድረግ፣ ሆን ተብሎ በኦህዴዶች በራሳቸው የተሰራ ሴራ ይመስለኛል።

ዶ/ር አብይ፣ ነገሮችን በመደባበስ፣ በመሸፋፈን፣ ላይ ላዩን ፍቅር ፣ መደመር እያሉ፣ አንድ እግራቸውን ጎጂ የሆነው የኦሮሞ ብሄረተኘንት ውስጥ አድርገው፣ ሌላ እግራቸውን አንድነት ጎራ ውስጥ ከተው አገር ለማስተዳደር እየሞከሩ ነው። ይሄ አካሄዳቸው ለተወሰነ ጊዜ ሰርቶላቸው ይሆናል። ከአሁን በኋላ ግን በጭራሽ አይሰራም።

ያኔ የተናገሩት ነገር የኦህዴድ አመራር የነበሩ ጊዜ የተናገሩት እንደመሆኑ ብዙም ሳያምኑበት ተናግረዉት ሊሆን ይችላል። አምነዉበት ከነበረ ያንን የተናገሩት፣ የአመለካከት ለውጥ ሊያደረጉም ይችላሉ ። ህዝብ በፊት የተናገሩትን ይዞ ፊቱን ከርሳቸው አያዞርም። ነገር ግን አሁን ያላቸውን አቋም ማወቅ ግን ይፈልጋል ። ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስተሩ ምላሽ መስጠት አለባቸው።

አንደኛ – በአዲስ አበባ ዙሪያ የዶ/ር አብይ አቋም ምንድን ነው? አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት ይላሉ ወይንስ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ናት ይላሉ?

ሁለተኛ – በአዲስ አበባ “የኦሮሞያ ክልል ወይንም የኦሮሞው (ለምን ኦሮሚያ ማለት የኦሮሞዎች ክልል በመሆኗና ኦሮሞዎችም አንደኛ ዜጋ በመሆናቸው) ጥቅም ይጠበቅ ፣ ለኦሮሞ ልዩ ጥቅም ይሰጠው” የሚል አቋም ነው ያላቸው? ወይንስ በከተማዋ የሚኖሩ ሁሉ ዜጎች በከተማ የተወለዱ ሆነ ያልተወለዱ፣ አማርኛ በደንብ የሚናገሩ ይሁኑ የማይናገሩ፣ የፈለገ እምነት ይኖሯቸው.፣ የፈለገ ብሄረሰብ አባል ይሁኑ፣ በከተማዋ ሕግ መሰረት የከተማዋ ነዋሪ እስከሆኑ ድረስ ሁሉም እኩል ናቸው ብለው ያምናሉ?

ሶስተኛ – ኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ይሁን ሲሉ፣ ትግሪኛስ፣ ሶማሌኛስ? ጉራጌኛስ ….እርሳቸወ ከኦሮሞ ማህበረሰብና ኦሮሞን ከሚወክል ድርጅት ስለሆኑ ነው ኦሮሞኛ ብቻ የስራ ቋንቋ ይሁን ብለው ትግሪኛ፣ ሶማሌኛን፣ ጉራጌኛን ..የማይጨምሩት?

አራተኛ – ኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ይሁን ሲባል በኦሮሞ ክልል ለምሳሌ በሸዋ ዞኖች ከግማሽ በላይ ሕብረ ብሄራዊ የሆነ ማህበረሰብ እንደመኖሩ ከኦሮምኛ ጎን ለጎን አማርኛ የስራ ቋንቋ እንዳይሆን ለምን ድርጅታቸው ኦህዴድ ያግዳል? ለምንስ ለምሳሌ ሰባ አምስት በመቶ አማርኛ ተናጋሪ የአዳማ ከተማ ህዝብ፣ በከተማዋ አስተዳደር፣ በቀበሌዎች ከወለጋና ቦረና የመጡ ሹማምንት ተሹመዉበት ፣ በከተማዋ በላቲን እያስተረጎመ ካልሆነ አገልግሎት እንዳያገኝ ይደረጋል?

አምስተኛ – ኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ይሁን ሲባል በግርግር፣ በድርድርና በተጽኖ ለማስወሰን ከመሞከር፣ ታከለ ኡማ በአሻጥር እንደተሾመው፣ ሕዝብ መጠየቅ የለበትም ወይ?

ህዝብ ለነዚህና ለሌሎች መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ይፈልጋል።

ከላይ እንደገለጽኩት ዶ/ር አብይ ሁለት የተለያዩ ቦታዎች እየረገጡ መቀጠል የሚችሉ አይመስለኝም። መምረጥ ያለባቸው መሰለኝ። ከኢትዮጵያ አልፈው፣ በአገር ደረጃ ትልቅ ከበሬታ አግኝተዋል። ከአገር አልፈው በአህጉር፣ ከአህጉር አልፈው በአለም ደረጃ። አሁን እንደገና ወደ ታች፣ ወደ ጎጥና ወደ ኦሮሞነት ከወረዱ በጣም ያሳዝናል።

ዶ/ር አብይ አህመድ ሆነ ድርጅታቸው ኦህዴድ፣ በድርጅታቸው ውስጥ እንዲሁም ከድርጅታቸው ውጭ ባሉ ጸረ-ኢትዮጵያ፣ ያልተደመሩ፣ ዘረኛ የኦሮሞ ብሄረተኛ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ወደ ታች እየተጎተቱ መታሰር የለባቸውም። እነዚህን ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄረተኘንት ላለማስከፋት እያሉ፣ ኦሮሞ ለኦሮሞ በሚል ጠባብ አስተሳሰብ፣ የነ አቶ ገዱ ብአዴን/አዴፓንና የደሃዴኖችን ትእግስት ወደ ጎን እያደረጉ፣ አራት ኪሎ መቀመጥ የሚችሉ አይመስለኝም።

የኦሮሞ ማህበረሰብ ጥያቄ ልማት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ነጻነት ነው። የኦሮሞ ማህበረሰብ ሌላውን አቃፊ እንጂ ጨፍላቂ አይደለም። በኦሮሞ ስም የሚነግዱ ፣ ብዙዎቹም በኦህዴድ ውስጥ ያሉ ዘረኛ የፖለቲካ ነጋዴዎች ናቸው፣ ኦሮሞውን ከሌላው ለማቃቀር እየሰሩ ያሉት። በመሆኑም ዶክተር አብይ ድርጅታቸውን ማጥራት መቻል አለባቸው።

ኦሮምኛ በአዲስ አበባና በሌሎች ቦታዎች ማስተማር፣ ከተማ በሰፋ ቁጥር ገበሬዎች በቂ ካሳ እንዲያገኙ ማድረግ፣ ኦሮምኛ ብቻ የሚችሉ በኦሮምኛ መንግስታዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ማመቻቸት፣ ኦሮሞዎች በብዛት የሚኖሩባቸው የተረሱ የወደቁ አካባቢዎች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የመሳሰሉ ጥያቄዎች የሚደገፉ ጥያቄዎች ናቸው። የኦሮሞነት ጥያቄዎች ሳይሆኑ የሰብአዊ መብት ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች ሌላውም ማሀብረሰብ ካለው ጥያቄ ጋር በማዛመድ ሕዝብን አንድ አድርጎ ማሰለፍ ይቻላል። ችግር የለውም።

ይህ እንዳይሆን እንቅፋት የሆኑት ግን የኦሮሞ ብሄረተኞች ናቸው። የኦሮሞ ብሄረተኝነት ኦሮሞ የበላይ እንጂ ኦሮሞ እኩል እንዲሆን አይደለም የሚፈልጉት።

እነ ዶ/ር አብይ፣ እነዚህ ቡድኖችን በማባበልና በመለማመጥ የያዙትን ትልቅ ራእይ ማጨናገፍ የለባቸውም። ደግሜ እላለሁ ፣ አክራሪዎችና ዘረኞችን እያግበሰበሱ ዘመናዊ ፖለቲካ ማራመድ፣ አገርን ከቀውስ ማውጣት አይችሉም።

አዲስ አበባ የነውሪዎቹ ናት!!!!!
ኢትይጵያ ትቅደም፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት ይዉደም !!!!