በባቱ (ዝዋይ) በመንግሥት እና በ‹‹ሸኔ›› ታጣቂዎች መካከል ግጭት መኖሩ ተገለጸ

በባቱ (ዝዋይ) በመንግሥት እና በ‹‹ሸኔ›› ታጣቂዎች መካከል ግጭት መኖሩ ተገለጸ

 (አዲስ ማለዳ)

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ባቱ (ዝዋይ) ወረዳ እና አካባቢው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ኃይል መካከል ግጭቶች መኖራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ በወረዳው በተለይም በገጠራማ ቀበሌዎች ሕዝቡ በከፍተኛ ሰቆቃ ውስጥ እንደሚገኝ ተናገረዋል፡፡

የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ‹‹ሸኔን ትደግፋላቸሁ›› ሲሉ፤ ራሱን የኦሮሚያ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ደግሞ ‹‹የመንግሥት ኃይሎች ትደግፋላቸሁ›› በማለት የአካባቢው ነዋሪ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ንጹኃንን በማገት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መጠየቅ፣ የአርሶ አደሩን እንሰሳት አርደው መብላት፣ ዝርፊያ እና ማስፈራራት የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን የዕለት ከዕለት ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሆኖም የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ግፍና በደል እየተፈጸመበት ቢሆንም፤ በሥፍራው ያሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ነዋሪውን ሊታደጉ አልቻሉም ተብሏል፡፡

የታጣቂ ቡድኑ አባላት በአካባቢው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ፣ ለማህበረሰቡ ወጥቶ መግባት እና ሥራ መስራት ፈተና እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በዚህ ሳቢያ በወረዳው የሰዓት እላፊ ገደብ የተጣለ ሲሆን፣ ማንኛውም ተሽከርካሪ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ በከተማዋም ሆን በዙሪያዋ ባሉ አጎራባች አካባቢዎች መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ተጠቁሟል፡፡

‹‹በመንግሥት እና በታጣቂ ቡድኑ መካከል የሠላም ድርድር ከተደረገ በኋላ ነገሮች ይስተካከላሉ ብለን አስበን የነበረ ቢሆንም፣ ችግሮች እየባሱ እንጂ እየተስተካከሉ አልመጡም›› ሲሉ ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት፡፡

ስለሆነም መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ወስዶ የሕዝቡን ሠላም በዘላቂነት እንዲያስጠብቅ በአጽንዖት ጠይቀዋል፡፡

መንግሥት እና ራሱን የኦሮሞ ታጣቂ ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በታናዛኒያ ራስ ገዝ በሆነቸው ዛንዚባር ደሴት ለኹለት ሳምንታት ሲደራደሩ ቆይተው፤ ባለመግባባት መጠናቀቁን በመግለጽ ኹለተኛውን የድርድር ምዕራፍ በቅርቡ እንደሚጀምሩ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡