ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ ተወሰነ፤ ዕጩዎች ለሰኔ 30 ቀርበው ሐምሌ 9 ቀን ይሾማሉ

  • ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ ተወሰነ፤

* ዕጩዎች ለሰኔ 30 ቀርበው፣ ሐምሌ 9 ቀን ይሾማሉ፤

* ባለፈው ሹመታቸው አወዛጋቢ ከነበሩት መስፈርቱን የሚያሟሉት ሊካተቱ እንደሚችሉ ተመልክቷል።

+++++

Image(አደባባይ ሚዲያ):– የቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ አከራካሪውን የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት በተመለከተ፣ ዛሬ ሰኞ፣ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በነበረው የቀትር በኋላ ውሎ ከስምምነት ላይ ደርሶ፣ ተከታዩን ውሳኔ አሳልፏል፤ ከዐማራ ክልል አህጉረ ስብከት በቀር፣ ለኦሮሚያ እና ለደቡብ፣ ሶማሌ፣ ድሬዳዋ እና አሶሳ አህጉረ ስብከት የሚሾሙ ዘጠኝ ዕጩዎች ተለይተው እንዲዘጋጁ ወስኗል፤

– አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበት የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ ሠይሟል፤ እነርሱም፦ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ (ሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ)፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ (የሐዲያ ከምባታ እና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) እና ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ (የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ምሥራቅ አፍሪቃ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) ናቸው፤ – አስመራጭ ኮሚቴው እስከ መጪው ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕጩዎቹን ለይቶ ያቀርባል፤

– ዕጩዎቹ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተገምግመው እንዲሾሙ ከተወሰነ በኋላ በዓለ ሢመቱ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በቅዱስ ፓትርያርኩ አንብሮተ እድ ኤጲስ ቆጶስነት ሢመቱ ይፈጸማል። – በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ምልዓተ ጉባኤ ደግሞ፣ ለዐማራ ክልል ብቻ ተጨማሪ የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት እንደሚኖር ተመልክቷል።

– ከኦሮሚያ አህጉረ ስብከት በተጨማሪ ለደቡብ፣ ለሶማሌ፣ ለአሶሳ እና ለድሬዳዋ አህጉረ ስብከት ነው የአሁኑ ሹመት የሚካሔደው። የዐማራ ለቀጣይ ጥቅምት ምልዓተ ጉባኤ ተጠንቶ እንዲመጣ ነው የተወሰነው።