በአዲስ አበባ የገበያ ማዕከላት ካለምንም ማስጠቀቂያ በመንግስት አፍራሽ ሃይሎች እየፈረሱ መሆኑ ተሰማ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት የሚገኘውና ረዥም ዓመታት ያስቆጠረው “የረር ጉሊት” ያለማስጠንቀቂያ እና ድንገት እንዲያፈርሱ መታዘዛቸውን በቦታው ላይ በመስራት ላይ የሚገኙ ነጋዴዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በቦታው ላይ ከ20 ዓመት በላይ በንግድ ሥራ ላይ የቆዩ ነጋዴዎች፤ ቦታው እንዲፈርስ የተወሰነው ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ድንገት መሆኑን ተከትሎ፣ ዕቃቸውን ወዴት እንደሚወሰዱ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

ያለቅድመ ማስጠንቀቂያ የሥራ ቦታቸውን እንዳፈርሱ የተነገራቸው ነጋዴዎች፣ ዛሬ አፍርሰው ዕቃቸውን የማያነሱ ከሆነ ነገ በዶዘር እንደሚያፈርሱባቸው እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡

ነጋዴዎቹ ድንገት አፍርሰን ዕቃችንን ወዴት እንውሰደው የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም “እቃችሁ ላይ ከምናፈርሰው ብታወጡ ይሻላችኋል” ከሚል ማስጠንቀቂያ ውጪ ችግራቸውን የሚያረዳቸው አካል አለማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በገበያ ቦታው ላይ የተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ከ130 ነጋዴዎች ለረዥም ዓመት የሠሩ ሲሆን፤ የሥራ ቦታቸው ከመፍረሱ በላይ ጊዜያዊ ዕቃ ማሰረፊያ እንኳን በማመቻቸት ፈንታ የወረዳው አመራሮች ችግራቸውን ለመስማት ፈቃደኝነት ማጣታቸው እንዳሳዛዘናቸው ጠቁመዋል፡፡