ሕወሃት ጌታቸው ረዳ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ መምረጡን የክልሉ ቴሌቪዥን አረጋገጠ።

የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የፓርቲውን ቃል አቀባይና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጌታቸው ረዳ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ትናንት በአብላጫ ድምጽ መምረጡን የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ዛሬ ዘግቧል።

የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር የሚያዋቅረው፣ ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመውና ጀኔራል ታደሠ ወረደ የሚመሩት ክልል ዓቀፍ ኮሚቴ ነው። ኮሚቴው፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሁሉን አካታች እንደሚሆን ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት የሚያቀርበው ግን ሕወሃት እንዲሆን እንደተወሰነ ቀደም ሲል ተገልጧል።

DW : አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ የሚቋቋመው ግዚያዊ አስተዳደር እንዲመሩ በህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ተመረጡ። የአቶ ጌታቸው ሹመት የፌደራሉ መንግስቱ ይሁንታ ይጠብቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ተቃዋሚው ፓርቲ ዓረና ትግራይ ለሉአለዊነት እና ዴሞክራሲ በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የማቋቋሙ ሂደት ላይ የፌደራል መንግስቱ እና ህወሓት ወቅሷል።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት በትግራይ ይቋቋማል የተባለው ግዚያዊ አስተዳደር እንዲመሩ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ተሰብስቦ አቶ ጌታቸው ረዳን መምረጡ ያረጋገጡልን ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን፣ ይኽ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ውሳኔ በቅርቡ ለፌዴራሉ መንግስት ቀርቦ ሊፀድቅ እንደሚጠበቅ ተመልክቷል። ሌላው የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ዛሬ በይፋዊ የትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት “አቶ ጌታቸው ረዳ ለትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መሪነት እጩ እንዲሆኑ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ መወሰኑ” ገልፀዋል። የአቶ ጌታቸው እና ሌሎች የግዚያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ሹመት ህወሓት ከፌዴራሉ መንግስት ጋር ተወያይቶ ተቀባይነት ካገኘ ወደ ስራ ይገባሉ ሲሉ ምንጮቻችን ጨምረው ገልፀውልናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ከአራት በላይ ወር በላይ ቢቆጠርም ይቋቋማል የተባለው ግዚያዊ አስተዳደር እስካሁን እውን ባለመሆኑ የተለያዩ ችግሮች እየተከሰቱ መሆኑ አስተያየት ሰጪዎች ይጠቁማሉ። በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ትላንት ባወጣው መግለጫ “ቅቡልነት እና ሕጋዊነት ያጣ ግዚያዊ አስተዳደር ፍትህና ዴሞክራሲ ሊያረጋግጥ አይችልም” ብሎታል። ዓረና በመግለጫው በትግራይ ጦርነት እንዲቀሰቀስ፣ ሚልዮኖች እንዲፈናቀሉ፣ በርካቶች እንዲሞቱ እና እንዲጎዱ ምክንያት የሆኑ ህወሓት እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት፣ ሌሎችን በማግለል ብቻቸው በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ለማቋቋማ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ቅቡልነት የለውም ሲል አክሏል።

Äthiopien Mulatu Techome Internationale Investment Ausstellung in Addis Abeba ያነጋገርናቸው የዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ማእከላይ ኮሚቴ አባል አቶ ሃፍታይ ገብረሩፋኤል “ሁለቱ የችግሩ ምንጮች የሆኑ ሀይሎች መፍትሔ ሊፈጥሩ አይችሉም” ሲሉ የገለፁ ሲሆን፣ እስካሁን የተያዘው አካሄድ ግን ካለፈው ትምህርት የተወሰደበት አይመስልም ሲሉ አክለዋል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ሃፍታይ በትግራይ ያለው ዘርፈ ብዙ ችግር ለመፍታት ሁሉን ያካተተ የሽግግር ስርዓት መዘርጋት ይጠበቃል ብለዋል።

በግዚያዊ አስተዳደሩ ማቋቋም ሂደት ዙርያ ከህወሓት ወገን ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልተሳካም። ከዓረና ውጭ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ ባይቶናና የትግራይ ነፃነት ፓርቲ የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከግዚያዊ አስተዳደር የማቋቋም ሂደቱ ማግለላቸው ይታወሳል። DW

የጀርመን ድምጽ ከመቀሌ የዘገበው ….