ሰራዊቱ መውጣት የለበትም የምንለው ከአቅም አንፃር አይደለም። ህገወጥ፤ አገር አፍራሽ ስለሆነ ነው!
መከላከያ ሰራዊት ከግንባር መውጣት የለበትም ሲባል አማራው አቅም ስለሚያንሰው አስመስለው የሚስሉት አሉ። ይህ ፈፅሞ ስህተት ነው። አማራው ራሱን ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ሰራዊቱንም አገርንም ታድጓል። መከላከያ ሰራዊቱ መውጣት የለበትም እየተባለ ያለው ከአገር ጥቅምና ከህጋዊነቱ አንፃር ነው።
1) የደም ዋጋ የተከፈለበት የሰላም ስምምነት ሰራዊቱ ከአማራ ክልል እንዲወጣ ሳይሆን ትግራይን እንዲቆጣጠር ነው የሚያዝዘው። የሚጠበቀውም። በዋነኛነት ስምምነቱ እየተጣሰ ነው። ይህ ደግሞ ለሌላ ትርምስ ይዳርጋል።
2) መከላከያ ሰራዊቱ እየወጣ ያለው ትህነግ ትጥቅ ባልፈታበትና ሌላ ወ*ረ*ራ ለመፈፀም እየተዘጋጀ ባለበት ሁኔታ ነው። የመከላከያ ሰራዊቱ አመራሮች ይህን ሁኔታ ለባለስልጣናቱ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ይህን አገራዊ ሁኔታ እየታወቀ ሰራዊት እንዲወጣ መደረጉ የአገር አንድነትና ሰላም ላይ የሚመጣውን ችግር ያለማሰብ ብቻ ሳይሆን ችግር እንዲፈጠር እገዛ ማድረግም ጭምር ነው። አገር እንዲፈርስ ማገዝ ነው።
3) ሰራዊቱ ሲወጣ በርካታ ደባዎችና ማጭበርበሪያዎች ተደርገዋል። የሰራዊቱ አመራሮች በርካታ መረጃዎችን አቅርበው “መውጣት የለብንም” በማለታቸው ስልጣን ላይ ባሉት ተፈርጀዋል። ተገምግመዋል። “መውጣት አልነበረብንም ብላችሁ ለህዝብ ተናግራችኋል” በሚል ተገምግመዋል። ይህ አልበቃ ብሎ ህዝብን ለማወናበድ ተሞክሯል። ሰሞኑን ከግንባር የሚወጣው ኃይል ምዕራብ ዕዝ ሆኖ እያለ የሚወጣው ሰራዊት “ምስራቅ ዕዝ” የሚል ባነር ለጥፎ ነው የወጣው። መጀመርያ ነገር ለደህንነቱ ሲባል ሰራዊት የዕዙን ስም በባነር ሰቅሎ እያሳየ አይወጣም። ተደርጎ አያውቅም። ህዝብን ለማወናበድ ምዕራብ እዝ ምስራቅ ዕዝ ተብሎ ተፅፎበት ወጥቷል። ይህ ውንብድና ነው። ለምን ማጭበርበር አስፈለገ?
በጣም በከፋ ሁኔታ ደግሞ አንዴ “ሰራዊቱ ከግንባር የሚወጣው ኦነግ ሸኔን ለማጥፋት ነው” ሌላ ጊዜ “ሶማሊ ላንድን ይዘን ወደብ ለማስመለስ ነው” የሚል የለየለት የሀሰትና የእብደት ምክንያት ተሰጥቷል። ሁለቱም ውሸት ነው። ኦነግ ሸኔ ጋር አብረው እየሰሩ ነው። ወደብ እንይዛለን የሚሉትም (በሚዲያ ሁሉ አሰርተዋል) ቅጥፈትና እብደት ነው። ይህ ሁሉ የሀሰት ምክንያት ለምን አስፈለገ? በዚህ ደረጃ ደባና ማጭበርበሩ ለምንድን ነው?
4) መከላከያ ሰራዊት የአገርን ዳር ድንበር የማስጠበቅ ግዴታ አለበት። እንደ ህዝብ መብት ከተጠየቀም የአማራ ህዝብ ሰራዊት አድኗል። የሰራዊቱ ከባድ መሳርያዎችም ህይዎት ገብሮ የማረካቸው፣ ሰራዊቱን አግዞ ያስቀራቸው ናቸው። የደሙ ውጤት ናቸው። ሊጠበቅባቸው ይገባል። በሰራዊቱ መጠበቅ መብቱ ነው።
5) ሰራዊቱ እየወጣ ያለው ከሰሞነኛ የፖለቲካ ሙቀትና ከቡድን ፍላጎት አንፃር እንጅ በግዴታም፣ በአስፈላጊነትም፣ በምክንያትም አይደለም። በህግ፣ በግዴታ፣ በምክንያት ቢሆን ሙሉ በሙሉ ትግራይን መቆጣጠር ይገባ ነበር። ከሞራል፣ ከተከፈለው ዋጋ አንፃር ተጨማሪ ኃይል ያስፈልግ ነበር። ይህ ከአስፈላጊነት፣ ከወቅታዊና ቀጣይ ሁኔታ፣ ከህግ በተቃራኒ በቡድን ጥቅም የሚደረግ ስምሪት መከላከያ ሰራዊቱን እንደ ተቋም የጥቂቶች መጠቀሚያ እንጅ የአገር ተቋም አያደርገውም። ይህ አካሄድ ተቋሙን ያፈርሰዋል። ችግር ይፈጥራል።
6) ይህ የፖለቲካ ስምሪት ለግጭት የሚዳርግ ነው። የሰላም ስምምነቱን ጥሶ፣ የአገርን ወቅታዊና ቀጣይ ስጋት ዘንግቶ፣ ህዝብን እያታለሉ የሚደረግ የቡድንን ጥቅም ብቻ ያሰበ ስምሪት ሌላውም የራሱን እንዲያስብ ያደርገዋል። አማራው የትህነግን ቀጣይ ወ*ረ*ራ ቀድሞ ለመመከት ሲል መቀሌ ድረስ ልግባ ቢል የፌደራል መንግስቱም ሆነ መከላከያ እንደ ተቋም “ተው” የማለት መብትም ሞራልም የለውም። የሰላም ስምምነቱን ራሱ ጥሷል። ህዝብና አገር የመጠበቅ ግዴታውን ለቡድን ጥቅም ሲባል አልተወጣም። ሌላው ራሱን ለመከላከል መቀሌን እይዛለሁ ከሚለው ይልቅ መቀሌን እስካሁን ያልያዘው ይባስ ብሎ ከሌሎቹም የወጣው መንግስት ነው ህግ የሚጥሰው።
7) አሁን ሰራዊቱ የሚወጣባቸው ወልቃይት ጠገዴና ሌሎች አካባቢዎች የዘር ፍጅት የተፈፀመባቸው፣ ሌላ የዘር ፍጅት ለመፈፀም ከሱዳንም ከትግራይም ትህነግ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው። ይህ በሆነበት ህዝብን ለዘር ፍጅት የሚያጋልጥ፤ አሸባሪን የሚያበረታታ፣ ሌላ ግጭት እንዲቀሰቀስ እድል የሚሰጥ ስምሪት የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል በሚል ሁሉ ከህግም፣ ከሞራልም፣ ከአገር ሉአላዊነትም፣ ከህዝብ ደህንነትም መወገዝ ያለበትና በአስቸኳይ ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ ነው።
መታወቅ ያለበት ይህ ውሳኔ የወታደራዊ ትንተናን ያልተከተለ፣ የሰራዊቱን ፍላጎት ያላገናዘበ መሆኑ ነው። ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለይምሰል እንዲቆይ የተደረገውን ሰራዊትም ለሌላ እልቂት የሚዳርግ ከባለፈው ትምህርት ያልተወሰደበት ውሳኔና አካሄድ ነው።