ፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ተግዳሮት እየገጠማቸው መሆኑን ምርጫ ቦርድ ገለጸ

ቦርዱ የመንግሥት አካላት በወንጀል እንዲጠየቁ ጠይቋል

ፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የተከራዩትን አዳራሽ በመከልከልና ማዋከብ እየተፈጸመባቸው መሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ቦርዱ ፓርቲዎችን የማስተዳደር፣ የማገዝ እና ቁጥጥር ማድረግ ኃላፊቱን ለመወጣት በሚያደርገው ክትትል፣ ፖርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ከማድረጋቸው በፊትና በኋላ እንግልትና ማዋከብ እንደተፈጸመባቸው ማረጋገጡን ዛሬ በሰጠው መግለጫ ጠቁሟል።

የተፈጸመው የሕግ ጥሰት አሁን ያለው ቦርድ አመራር ኃላፊነት ከተረከበ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ጥሰት የተፈጸመበት ነው ተብሏል።

ጠቅላላ ጉባኤ እንዳያደርጉና የጀመሩትን ሂደት እንዳያጠናቅቁ የተከለከሉት እናት ፓርቲ፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እና ለጉራጌ አንድነት ፍትሕ ፓርቲ(ጎጎት) ናቸው ተብሏል።

በፓርቲዎች ላይ የተፈጸመውን ሕገ ወጥ ድርጊት ተቀባይነት የለውም ያለው ቦርዱ፣ የፓርቲዎች እንቅስቃሴ መገደብ ቦርዱ የተቋቋመበትን መሰረታዊ ሥራ እንዳይሰራ የሚያደርግ መሆኑን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ተናግረዋል።

ድርጊቱን የፈጸሙ የሕግ አስፈጻሚዎች ግዴታቸውን ከመሳታቸው፣ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ አንቀጽ 490 ሕጋዊ ስብሰባ ስለመከልከልና ስለማወክ የተደነገገውን በመተላለፍ ወንጀል ፈጽመዋል ተብሏል።

በመሆኑም፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እና የጸጥታ ኃይሎች ልዩ ትኩረት በመስጠት በፓርቲዎች ላይ ያለው ገደብ እንዲያቆሙ ቦርዱ ጠይቋል።

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶት አዳራሽ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ክፍት እንዲሆኑ የጠየቀው ቦርዱ፣ ፍትሕ ሚኒስቴር የተፈጸመውን የሕግ ጥሰት መርምሮ የሕግ ተጠያቂነትን እንዳረጋግጥ ተጠይቋል። ለፓርቲዎቹ የገጠማቸው ገደብ አሳሳቢ መሆኑን የገለጸው ቦርዱ፣ የተፈጸመውን ጥሰት በዝምታ አላልፍም ሲልም ገልጿል።

 (አዲስ ማለዳ)