በሕወሓት ቁጥጥር ስር ባሉ የአማራ ክልል አበርገሌና የጻግብጂ ወረዳ ሕይወት እየጠፋ ነው

በህወሓት ስር የሚገኙ በአማራ ክልል ዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳ ነዋሪዎች ለክፍተኛ ርሀብና በሽታ መጋለጣቸውን የመንግስት ኃላፊዎች ተናገሩ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበትን ሁኔተ መንግስት እንዲያመቻችላቸውም ጠይቀዋል፡፡ የሁለቱ ወረዳ ነዋሪዎች ከሁለተ ዓመታት በላይ በህወሓት ቁጥጥር ስር ሲሆኑ ከማራ ክልልም ሆነ ከትግራይ ክልል በኩል የምግብ እርዳታና ህክምና እያገኙ ባለመሆናቸው ለከፍተኛ ስቃይና ለሞት እየተዳረጉ እንደሆነ ነው የብሔረሰብ ስተዳደሩ ኃላፊዎች የሚናገሩት፡፡የዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ኪዳት አየለ በአሁኑ ወቅት በተለይ ቆላማ በሆነው የአበርገሌ ወረዳ የወባ ህምም ተስፋፍቶ ከፍተኛ ህይወት እያጠፋ መሆኑን ጠቁመው በሌሎች የጤና ችግሮች በሁለቱ ወረዳዎች ህይወት እየጠፋ ነው ብለዋል፡ የፃግብጂ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሱ ደሳለኝ በህክምና እጦት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ወራት 15 እናቶች ህይዎታቸው ማለፉን፣ በርሀብም የተጎዱ እንዳሉም ነው ያመለከቱት፡፡

Bahir Dar | Binnenflüchtlinge aus Waghemra ፎቶ ከማኅደር፦ የዋግኅምራ ተፈናቃዮች

እርዳታ ሰጪ ተቋማት ወደ አካባቢዎቹ እንዲደርስ በርካታ ጥረት ቢደረግም ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም ይላሉ ዶ/ር ኪዳት አየለ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ኃላፊ፡፡
የብሔረሰብ አስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ ሌሎች በጦርነት ለነበሩ አካባቢዎች የሚደረገው ድጋፍ ለሁለቱ ወረዳ ነዋሪዎችም ሊሰጥ እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡ አንዳንድ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በአስቸኳይ ወደ ቀያችን መንግስት ይመልሰን የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የፃግብጂ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሱ ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት በወሓት ስር ወደሚገኘው ፃግብጂ ወረዳ ተፈናቃዮችን ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ እንዳለ ለማየት ወደ ቦታው የተንቀሳቀሱ የብሔረሰብ ዞኑ ሰዎች ከህወሓት ታጋዮች ጋር ተጋጭተው የተወሰነ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል፣ በመሆኑም ተፈናቃዮችን ማንቀሳቀስ እንዳልተቻለ ነው የገለጡት፡፡
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምግብ ዋስትና የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ ወ/ሮ ዝናሽ ወርቁ ከሁለቱ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ከ67 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ደግሞ በተለያዩ መጠለያዎችና ከህብረተሰቡ ጋር ይኖራሉ ብዋል፡፡