በአማራ ክልል በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ የመልሶ ማቋቋም ፈንድ ፅሕፈት ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ተገለጸ

በአማራ ክልል በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ የመልሶ ማቋቋም ፈንድ ፅሕፈት ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን የአማራ ክልል የምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማሰተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ምክንያት በአማራ ክልል ብዙ አካባቢዎች መውደማቸው ይታወቃል፡፡

አካባቢዎቹ ላይ የደረሰው ጉዳት ቀላል የሚባል እንዳለመሆኑ መጠን፤ ሰፊ ሥራ እንደሚያስፈልግና የመልሶ ግንባታ ሥራውን በሚገባ ለማከናወንም የመልሶ ማቋቋም ፈንድ ፅሕፈት ቤት መቋቋሙን የክልሉ የምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማሰተባበሪያ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ እያሱ መስፍን አስታውቀዋል።

በክልል ደረጃ የቋቋመው የመልሶ ማቋቋም ፈንድ ፅሕፈት ቤት የተለያዩ የሚመለከታቸው መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋዥ ድርጅቶችን ያካተተ ግብረ ሀይል እንደሆነ ገልጸው፤ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ወደ መልሶ ግንባታ ሥራ የገባ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም ከመልሶ ግንባታው ሥራ ጎን ለጎን በአካባቢው ያሉ ሰዎች ጊዚያዊ እርዳታዎች የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ የዕለት ደራሽ እርዳታዎችን እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አክለውም በመልሶ ማቋቋም ሥራው ህብረተሰቡ የሚያስፈልገውን መሰረታዊ የምግብ ፍጆታ በአካባቢው አልምቶ ራሱን የሚችልበትን መንገድ የማመቻቸት ሥራ እየሰራ እንደሚገኝም ማመላከታቸውን አሐዱ ራዲዮ ዘግቧል፡፡