እነ ዶ/ር መራራ ማሳመን ሲያቅጣችው ማስፈራራቱን እንደ ስትራቲጂ እየተጠቀሙበት ነው #ግርማ_ካሳ

ዶ/ር መራራ ጉዲና አሁን ያለውን የጎሳ ፌዴራል አወቃቀር መቀጠል አለበት እያሉ ነው። ችግሩ ያለው ፌዴራሊዝሙ ላይ ሳይሆን አተገባበሩ ላይ ነው ያሉት ዶ/ር መራር ፣ ወደ ቀድሞ አስተዳደር መመለስ ዋጋ እንደሚያስከፍል ይናገራሉ። አሁን ያለው አወቃቀር ዋጋ እንዳላስከፈለ።

‹‹የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የሶማሌ፣ የጋምቤላ …ነፃ አውጭ ድርጅቶች ባሉበት፤ የአማራ ነፃ አውጭ የሚመስሉ ድርጅቶች እየተፈጠሩ ባሉበት ሁኔታ ወደቀድሞው አስተዳደር ሥርዓት (ጠቅላይ ግዛት) ለመመለስ መሞከር ዋጋ ያስከፍለናል” ያሉት ዶ/ር መራራ፣ መፍትሔው አሁን ያለውን የፌዴራላዊ ሥርዓት በሕዝቦች ፈቃድ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ ነው ይላሉ።

ዶ/ር መራራ አሁን ያለው የፌዴራል አወቃቀር የሚቃወሙ ወገኖች ለምን እንደሚቃወሙ ጠንቅቀው ያውቃሉ ብዬ አስባለሁ። ቅንጅት፣ አንድነት፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓ፣ መኢአድ ..በአገር ውስጥ ሲንቀስቀሱ የነበሩና የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄረተኛ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና አክቲቪስቶች፣ አሁን ያለውን የጎሳ አወቃቀር ሲቃወሙ ፣ ወደ ድሮ አሃዳዊ፣ ፌዴራል ያልሆነ ስራዓት እንመለስ በማለት አይደለም። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፌዴራሊዝምን አይቃወምም። ፌዴራሊዝም ላይ ምንም ችግር የለም። ማንም የድሮውን አሃዳዊ ስርዓት ይምጣ አለለም።

ይሄን እውነታ ዶ/ር መራራ ጠንቅቀው እያወቁ፣ የድሮውን ፣ አሃዳዊ የሆነውን አስተዳደር ስለመመለስ ለምን እንደሚያወሩ ግልጽ ሊሆንልኝ አልቻለም።

አሁን ያለውን የጎሳ አወቃቀር ይቀየር በሚባልበት ጊዜ የጎሳ አወቃቀሩን የሚደገፉ ወገኖች፣ አሁን ያለውን የጎሳ አወቃቀር ለምን የተሻለ እንደሆነ አሳማኝ መከራከሪያ ከማቅረብ ይልቅ ፣ በሐሳብ ማሸነፍ ሲያቅታቸው፣ “ወደ ድሮው ስርዓት ሊመለሱን፣ ነው፣ አሃዳዊ ስርዓት ሊያመጡበን ነው፣ ደም መፋሰስ ነው የሚሆነው… .ወዘተረፈ” እያሉ ደጋፊዎቻቸውን በዉሸት በማታለልና ሌላውን በማስፈራራት የጎሳ አወቃቀሩ እንዳይቀየር የማድረግ ታክቲክና ስትራቴጂ ያላቸው ነው የሚመስለው። ዶር መራራ ይሄንኑ ታክቲክ ነው ሞደሬት በሆኑ መልኩ ለመጠቀም የሞከሩት።

ዶ/ር መራራ አሁን ያለው ፌዴራል አወቃቀር መቀጠል አለበት ሲሉ፣ አንድ አብረው የተናገሩት አባባል አለ። “የፌዴራል ሥራ’ዓቱ በሕዝቦች ፈቃድ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ” ይላሉ። ይሄ የሚደገፍ አባባል ነው። ግን ይሄን አባባል አስበዉት የተናገሩት አይመስለኝም። ለምን እርሳቸው እንዳሉት የሕዥብ ፍላጎት ከተጠየቀ የጎሳ አወቃቀሩ ስለሚቀየር። ይኸው እኮ እያየን ነው የደቢብ ክልልን ነዋሪዎች አንቀበልም እያሉ ነው ፣ በይፋ።

አሁን ያለው ፌዴራሊዝም በሕዝብ ስምምነት የተደረገ ፌዴራሊዝም አይደለም። በሕወሃትና ኦነግ ፖለቲከኞችና ባላስልጣናት የኦነግንና የሕወሃት ፍላጎት ያንጸባረቀ ፌዴራል አወቃቀር ነው። በተለይም የአማራውና አማርኛ ተናጋሪዉን፣ እንዲሁም ሕብረብሄራዊ የሆነውን የኢትዮጵያ ብሄረተኛው ጥቅምና ፍላጎት ያካተተ አይደለም። እንደውም እነዚህን ማህበረሰባት የጎዳ ነው። በመሆኑም አማራው፣ የብዙ ብሄረሰቦች ድብልቅ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄረተኛው ፍቃድና ፍላጎት ከተጠየቀ አሁን ያለው የጎሳ አወቃቀር መቀየሩ የማይቀር ነው።

ዶ/ር መራራ “የአማራ ነጻ አውጭ” ስላሉት አባላል ትንሽ ልበል። በኢትዮጵያ ውስጥ በጉልህ ሁኔታ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የአማራ ድርጅቶች አብንና አዴፓ ናቸው። እስከሚገባኝ ድረስ እነዚህ ድርጅቶች የአማራ ነጻ አውጭ ድርጅቶች አይደሉም። እንደ ኦነግና ሕወሃት ኦሮሚያንና ትግራይ ነጻ እናወጣ ብለው የተደራጁ አይደለም።

ዶ/ር መራራ ምን አልባት መረጃው ከሌላቸው እነዚህ ድርጅቶች አሁን ያለው የጎሳ አወቃቀር ፈርሶ፣ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚያስተዳደር ፍትሃዊ ፣ ዘመናዊ፣ ከዘር ጋር ያልተገናኘ ፌዴራል አወቃቀር ከመጣ፣ በአማራ ስም ተደራጅተው መቀጠል የማይፈለጉ ናቸው። የነዚህ የአማራ ድርጅቶች ጥያቄ “አማራው ለብቻ የራሱ ክልል ይኑረው፣ አማራው ብቻ ይጠቀም” የሚል ሳይሆን “አማራው ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት በተለይም በትግራይና በኦሮሞ ብሄርተኞችን በደል ስለደረሰበት፣ ስለተፈናቀለ፣ አሁንም እየተፈናቀለ ስላለ፣ በኦሮሞ ክልል ፈንታሌ ወረዳ ሰሞኑን እንደሆነው፣ አማራው መበደል የለበትም፣ ከሌላው እኩል መሆን አለበት” ብለው የእክልነትና የሕልዉና ጥያቄ አንስተው የተነሱ ናችው።

ከዚህ በፊትም በኦፌኮ የዶ/ር መራራ ጉዲና ምክትል አቶ በቀለ ገርባ ተመሳሳይ ንግግር ተናግረው ነበር። በአገራችን ለተከሰቱ የጎሳ ግጭቶች ምክንያቱ የጎሳ ፌዴራል አወቃቀሩ ሳይሆን የዲሞክራሲ እጦት ነው ብለው። ይመስለኛል ዶ/ር መራራ የፌዴራሊዝም አተገባበሩ ላይ ችግር ያሉትን ዲሞክራሲያዊ አልነበረም ከሚል ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ኖሮ አያውቅም። ምን አልባት አሁን በቅርብ እናይ ይሆናል። ከኢሕአዴግ በፊት የነበረው ወታደራዊ ደርግ ነበር። ከደርግ በፊት ደግሞ ንጉሳዊ አገዛዝ ነበር(absolute monarchy) ። በአጤ ሚኒሊክ ጊዜ ደግሞ በተወሰነ መልኩ ፌዴራል አስተዳደርም ነበር ማለት ይችላል። በወላይታ ንጉስ ጦና፣ በወለጋ ደጃዝማች ሞረዳ፣ በጂማ፣ ጂማ አባ ጂፋር፣ በጎጃም ንጉስ ተክለሃይማኖት …ያስተዳድሩ ነበር።

ሆኖም ግን በኢሕአዴግ ዘመን እንዳየነው ፣ የጎሳ ግጭቶችን፣ ከሚናገሩት ቋንቋ፣ ከዘራቸው፣ ከጎሳቸው የተነሳ ዜጎች ሲፈናቀሉ ያየንበት ሁኔታ አልነበረም። የዲሞክራሲ እጦት ቢኖር ኖሮ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እንደሚሉን በደርግም ነገስታቱ ዘመንም መፈናቅሎች በብዛት ይኖሩ ነበር።

አሁን ባለንበት ጊዜ በትግሬና በአማራ፣ በጉሙዝን በኦሮሞ፣ በሲዳማና ወልያታ፣ በኦሮሞና በጌዴዎ፣ በሃረሪና በኦሮሞ ..መካከል ግጭቶችን አይተናል። በአማራና በኦሮሞ መካከል ደግሞ አሁን ያለው የጎሳ አወቃቀር ከቀጠለ፣ በሸዋ ጉዳይ ደም መፋሰስ መኖሩ የማይቀር ነው። አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት የሚኖሩባቸው አካባቢዎች በተለይም ሸዋ በኦሮሞ ክልል በጭራሽ መቀጠል አይቻልም። ወይም ኦሮሞው ከሌላው እክሉ ሆኖ ተከባብሮ ሕብረ ብሄራዊ በሆነ ክልል መኖር ከፈለገ አማራውም ይስማማል። አለበለዚያ ግን አማራው አይቀበልም። ጉራጌዎች ወሊሶ የኛ ነው ይላሉ። ሲዳማዎች ሻሸመኔ የኛ ነው ይላሉ። ብዙ ብዙ የተወሳሰቡ አስችጋሪ ጥያቄዎች አሉ። ይህ የጎሳ አወቃቀርን መቀጠል ትርፉ ደም መፋሰስ ብቻ ነው።

ለጊዜው ሌላውን ሁሉ ትተን የጎሳ አወቃቀሩን አስከፊነት ለማየት በሶማሌዎችና በኦሮሞዎች መካከል ያለውን ግጭት ብቻ ለማየት እንሞክራለን።

ከዚህ በታች የምታዩት በሰው ሰራሽ(የጎሳ ግጭቶችና) በተፈጥሮ ችግሮች(ደርቅ፣ ረሃብ…) ምክንያት በሶማሌና በኦሮሞ ክልል የተፈናቀሉትን ዜጎች ቁጥር ያስቀምጣል። በድርቅ ምክንያት በሶማሌ ክልል 341425 በኦሮሞ ክልል ደግሞ 111936 ዜጎች ተፈናቅለዋል። በአጠቃላይ ወደ 453341 ሺህ ህዝብ።

በጎሳ ግጭቶች ደግሞ. እንደ ጥናቱ 453341 ሲፈናቀሉ፣ 565346 ኦሮሞዎች ተፈናቅለዋል። በአጠቃላይ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ናቸው። በጎሳ ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች በዋናነት በሶማሌና ኦሮሞ ድንበር አካካቢ ፣ በምስራቅ ሃረርጌ ሃረርና ጂጂጋ አካባቢ፣ በምእራብ ሃረርጌ ሜኤሶ ወረዳ፣ በሞያሌ፣ በሊበንና ቦረና ዞኖች ነው። እነዚህ አካባቢዎች ሶማሌዎችና ኦሮሞዎች ከሌሎች ጋር አንድ ላይ ሆነው ለዘመናት የኖሩባት አካባቢዎች ናቸው። ሆኖም አሁንም ባለው የጎሳ አወቃቀር መሬቶች በዘር ስለተሸነሸኑ፣ የሶማሌ፣ የኦሮሞ ስለተባለ ብዙ ሶማሌዎች በኦሮሞ ክልል፣ ኦሮሞዎች ደግሞ በሶማሌ ክልል በመጠቃለል በአገራቸው እንደ መጤና ሁለተኛ ዜጋ እንዲቆጠሩ አድርጓል። ያም አድልዎ ፈጥሮ፣ መብት እንዲረገጥ ሁኔታዎች አመቻችቶ ፣ ግጭቶችን አስከትሏል።

ስለሶማሌና ኦሮሞ ክልል ስንሄድ ደግሞ ድሬዳዋንና ሞያሌ ሳይጠቅሱ ማለፍ አይቻልም። ድሬዳዋ የቻእርተ ከተማ ናት። ሶማሌዎች፣ ኦርሞዎችም የኛ ናት ስላሉ፣ ስላልተስማሙ፣ ድሪዳዋ የማን ሳትሆን በፌዴራል ስር ነው ያለችው። ሞያሌ ከተማን ደግሞ ለሁ፤እ ትከፍለዋታል። ከዋናው መንገድ በስተምስራቅ ሶማሌ ሲሆን ደግሞ በስተ ምእራብ ደግሞ ኦሮሞ ነው። ለዘመናት በፋር የኖሩ ከተሞችን ሁሉ አሁን ያለው አወቃቀር እያተራመሰ ነው።

አሁን ያለውን የጎሳ አወቃቀር መቀየር ዶ/ር መራራ እንዳሉት ዋጋ አያስከፈልም። ይልቅ ይሄ የተረገመ ሰይጣናዊ፣ ከፋፋል አፓርታይዳዊ አወቃቀር ወደዚያ ጥለን በተሻለ፣ ለአስተዳደር አመች በሆነ፣ ማንም ዜጋ በዘሩና በጎሳ ልዩነት እንዲደረግበት የማይፈቀድ፣ ኢትዮጵያዉያን በሁሉም የአገሪቷ ምድር በነጻነት የመኖር፣ የመስራት፣ የመማር፣ የመነገድ፣ የመምረጥ፣ የመመረጥ ..መብታቸውን የሚያረጋገጥ ፣ ዘመናዊ፣ ተራማጅ ፣ ለአስተዳደር አመች የሆነ፣ ህዝብን የማያጉላላ የፌዴራል አወቃቀር ካላመጣን፣ በአገራችን ትልቅ ደም መፋሰስን ጠብቁ !!!!!