የአብይ አሕመድ መንግስት ሸኔ እያለ በሚጠራው የኦነግ ጦር ላይ እርምጃ እየወሰድኩ ነው አለ፤ ከነፃ ወገን የተረጋገጠ መረጃ አልተገኘም።

የመንግሥት ኃይል በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ላይ የተጠናከረ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ። መንግስት ይህን ይበል እንጂ ከገለልተኛ አካል የተገኘ ማረጋገጫ የለም። መንግስት የዋጋ ግሽበትን የኑሮ ውድነትን በተመለክተ በፍራንኮ ቫሉታ ምርቶች ገብተዋል ቢልም የገቡት ምርቶች በጭማሪ ዋጋ እየተሸጡ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ተቆጣጣሪዎች በምሬት ይናገራሉ። ተቆጣጣሪዎቹ ለባለስልጣናት ቢያሳውቁም አርፈው እንዲቀመጡ ተነግሯቸዋል።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ ረፋድ በሰጡት መግለጫ፣ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ሲል የሚጠራውንና መንግሥት ‘ሸኔ’ ሲል በአሸባሪነት የፈረጀውን ታጣቂ ኃይል ለማስወገድ ፀረ ሽምቅ ውጊያ ኮማንዶ በማሰማራት ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘመቻው በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ እና በምሥራቅ ወለጋ፣ በምዕራብ እና በምሥራቅ ጉጂ፣ በሰሜን፣ በምሥራቅ እና በምዕራብ ሸዋ እንዲሁም በቦርና ዞኖች እየተካሄደ እንደሆነም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

እየተደረገ ባለው ዘመቻ “በሺዎች የሚቆጠሩ” የታጣቂው ቡደኑ አባላት መገደላቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ፣ የቡድኑ አመራሮች፣ ታጣቂዎች፣ የስንቅና የሥልጠና ማዕከል “ከጥቅም ውጪ እንዲሆን ተደርጓል፤ መሳሪያዎችም ተማርከዋል ብለዋል።

ለገሰ ቱሉ ( ዶ/ር) ታጣቂው ኃይል በተቀናጀው ኦፕሬሽን እየደረሰበት ያለውን ጉዳት መቋቋም ባለመቻሉ እየተበተነ ነው ሲሉም በመግለጫቸው አመልክተዋል።

ሆኖም ከትናንት በስቲያ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ( ኦፌኮ) በሰጠው መግለጫ በኦሮሚያ ዞኖች ከዓለም ዓይን የተሰወረ ጦርነት እየተካሄደ ነው ሲል በጦርነቱ በርካታ ዜጎች በጅምላ መገደላቸውን ገልጿል።

ኦፌኮ እየተፈጸሙ ነው ያላቸው “የጅምላ ግድያዎች”ም ገለልተኛ በሆነ ዓለም አቀፍ አካልም እንዲጣራ ጠይቋል።

እንደ ፓርቲው መግለጫ ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ንጹሃን ናቸው ያላቸው ከ297 በላይ ሰዎች በክልሉ በመንግሥት ኃይሎች ተገድለዋል፤ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎችም ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ( ኦቻ) በዚህ ሳምንት ባወጣው ሪፖርት በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር እና ግጭቶች ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎች ቀያቸውን ለቀው እንደወጡ አመልክቷል።

ቀደም ብሎም መንግሥት በዘመቻው ድል እየቀናኝ ነው ማለቱን ተከትሎ ፣ ታጣቂ ቡድኑ በታጣቂዎቹ ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለና የመንግሥት እርምጃ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በቃል አቀባዩ በኩል ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

በክልሉ በታጣቂ ቡድኑና በመንግሥት መካከል እየተደረገ ባለው ውጊያ ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎችና ባለሥልጣናትም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ እንደተናገሩት መንግሥት ታጣቂ ቡድኑ በስፋት በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎችም በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃትም ፈጽሟል።

መንግሥት ግን እነዚህን ክሶች ያጣጣላቸው ሲሆን ዘመቻው በክልሉ እየደረሰ ያለውን ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ለማስቀረት የተጀመረ ነው ብሏል።

ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ እና ምዕራብ ሸዋ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት ታጣቂዎች ፈፀሙት በተባለ ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከቤት ንብረታቸውም ተፈናቅለዋል።

ለገሰ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ይህንን “ዘመቻ ለማጠልሸት የሚጥሩ ኃይሎች አሉ” ያሉ ሲሆን፣ እነዚህ ኃይሎች መንግሥት በታጣቂ ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ ሲጀምር ንጹሃን ዜጎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጉዳት እየደረሰባቸው ነው በሚል የሚጮሁ ናቸው” ሲሉ ማንነታቸውን ያልገለጿቸውን አካላት ከሰዋል።

ይሁን እንጂ ለተከታታይ ሳምንታት እየተካሄደ ባለው ዘመቻ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች “እፎይታ እየተሰማቸው ነው” ብለዋል።

በመግለጫው የተነሱ ሌሎች ጉዳዮችስ ?

ስለጎንደሩ ግጭት

በጎንደር በቀብር ስፍራ በተወሰኑ ሰዎች አለመግባባት በተፈጠረ ግጭት ጉዳት ቢከሰትም ታቅዶ ነበር ያሉት ‘ሴራ’ መክሸፉን ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ተናግረዋል።

በግጭቱ የወደሙ መስጊዶችና አብያተ ክርስቲያናትን በጋራ ለመገንባት፣ ንብረታቸው የወደመባቸውና የተዘረፈባቸውን ግለሰቦች መልሶ ለማቋቋምም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ግጭት እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ አካላትም ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ቀርቦ እየታየ ነው ብለዋል።

ከሳምንታት በፊት በጎንደር በቀብር ሥፍራ ላይ በተከሰተ ሃይማኖታዊ መልክ ያለው ግጭት ቢያንስ የ21 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ150 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ መገለጹ ይታወሳል።

ይህ ግጭት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶም በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል።

ሚኒስትሩ ይህንን በተመለከተ የፌደራል ፖሊስ የመርማሪ ቡድን እስካሁን የተሰሩ ሥራዎችን በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

‘አልሸባብ’

የኮሚዩኒኬሽ አገልግሎት ሚኒስትሩ በመግለጫቸው የአልሻባብ የሽብር ቡድን ከሸኔ እና ከህወሓት ጋር በመቀናጀት በመሃል አገር፣ በምሥራቅና በምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች የሽብር ጥቃቶችን ለመፈፀም የወጠኑትን እቅድ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል።

በተወሰደው እርምጃም ቀደም ብሎ በርካታ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ባለፉት ቀናት በሶማሌ ክልል የተለያዩ ዞኖች፣ በኦሮሚያ፣ በምዕራብ ሐረርጌ እና በአርሲ፣ በምዕራብና ምሥራቅ ባሌ በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል።

እስካሁንም 45 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር በርካታ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸውንና በየቤተ እምነቶች የተቀበሩ መሣሪያዎችም በሕዝብ ጥቆማ እየተለቀሙ ነው ብለዋል።

በዚህም 105 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 13 ብሬል፣ 25 አርፒጂ፣ 25 ሳጥን የተለያዩ መጠን ያላቸው ጥይቶች፣ አራት ስናይፐር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

በአማራ ክልል ስላለው የጥታ ሁኔታ

የአማራ ክልል እና አጎራባች ክልሎችን ለማጋጨት እና ሕገ ወጥነት ለማስፋፋት ሆነ ብለው የሚሰሩ ኃይሎች ላይ የሚወሰድ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ውስጥ ያሉ “ኢ መደበኛ አደረጃጀቶች” ሕግ በማስከበርና ክልሉን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ለመመለስ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያስችል አሰራር ተነድፎ አሳታፊ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም በክልሉ ላይ ሊቃጣ የሚችልን ማንኛውም ጥቃት ለመመከት የሚደረግ እንቅስቃሴ ለመግታት የሚሰሩ ኃይሎች ላይም ምህረት እንደማይኖር አስጠንቅቀዋል።

ሰብዓዊ እርዳታ ለትግራይ

ሚኒስትሩ ከሰሜኑ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር በተያያዘም ወደ ትግራይ በየብስም፣ በአየርም የሚጓጓዘው ሰብዓዊ እርዳታ እንደቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሩ መግለጫ ከሆነ ባለፈው ሳምንት 165 ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መቀለ ገብተዋል።

የእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ማቅረብ የሚችሉት እርዳታ ያህል እንዲያቀርቡ መንግሥትም የተቻለውን እያደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን የትግራይ ኃይሎች ለእርዳታ ማጓጓዝ ሥራው እንቅፋት ሆነዋል ብለዋል።

“ህወሓት ከአፋር ክልል መውጣቱን ቢገልጽም፣ አሁንም በአፋር ክልል ከበርሃሌ፣ ከኮነባ፣ ከአብአላ እና ከመጋሌ ወረዳዎች አልወጣም። በአማራ ክልልም፣ አድርቃይ፣ ጠለምት፣ አበርገሌ እና ሌሎች አካባቢዎችን ይዞ ይገኛል” ሲሉ ከሰዋል።

ህወሓት የሰብዓዊ እርዳታ ያለገደብ ትግራይ እንዲደርስ ሙሉ በሙሉ ከአፋር ክልል መውጣቱን ያስታወቀ ቢሆንም የክልሉ የፀጥታ ባለሥልጣናት ኃይሎቹ አሁንም በክልሉ እንደሚገኙ ለቢቢሲ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

መንግሥት ከህወሓት የሚቃጣን ጥቃት ለመመከት በየትኛውም ጊዜና ሰዓት ሙሉ ዝግጁነትና አቅም ያለው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ግጭት ቀስቃሽ በሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች ተነሳስቶ ወደ ግጭት እንደማይገባ ግን በአጽንኦት ተናግረዋል።

የዋጋ ግሽበት

በኢትዮጵያ የምግብ ዋጋ ንረትና ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳሳቢ ሆኗል።

ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫም የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት ከምርት አቅርቦት ጋር የሚያያዝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ስኳር፣ ዘይት፣ የህጻናት አልሚ ምግቦች እና ሌሎች ምግብ ነክ ፍጆታዎችን በፍራንኮ ቫሉታ አገር ውስጥ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ፍራንኮ ቫሉታ ሕጋዊ ከሆነ ምንጭ የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ ሲሆን የባንክ ቤት ፈቃድ ሳያስፈልገው ከውጪ አገር ዕቃ ለማስገባት የሚያስችል ፈቃድ ነው።

ባለፉት ወራት በ700 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ የለማ ስንዴ ውጤት በማስገኘቱ ከ25 ሚሊየን ኩንታል በላይ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ እና ተጨማሪ ምርት ለማግኘት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ሚኒስትሩ አክለዋል።

ከዚህ ባሻገርም በግንባታው ዘርፍ ላይ እና በሲሚንቶ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታትም እየተሠራ ነው ብለዋል።