የዳኝነት ስርዐቱ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በትውውቅ እና በገንዘብ ሙስና ውስጥ ተዘፍቆ ለዜጎች ማነቆ ሆኖብናል ሲሉ መዐዛ አሸናፊ አመኑ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ “ሙስና በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ የምናውቀው ሳይሆን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የዜጎችን ሕይወት እየፈተነ ያለ ጥልቅ ችግር ነው” ሲሉ ተናገሩ።በዳኝነት ወንጀል ላይ የሚታዩ የሙስና ተግባራት መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ስታራቴጂ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው። በስትራቴጂው ውስጥ በዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ ሙስና ያለበት ደረጃ፣ ለሙስና በር ከፋች የሆኑ አሠራሮች እና የመከላከያ ስልቶች ተካተውበታል።
ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በውይይት መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የፍትሕ ተቋማት ዜጎች ንጹህ ፍትሕን ፈልገው የሚመጡበት በመሆኑ ልዩ ጥንቃቄን ይሻልም ብለዋል።
በቅርቡ በተደረገ ጥናትም ዜጎች በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ያላቸው እምነት 78 ከመቶ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ዜጎች ወደ ፍርድ ቤቶች መጥተው ጉዳያቸውን አሳክተው የመመለስ ምጣኔያቸው 87 በመቶ ላይ ይገኛል። ሙስና በዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ በሁለት መንገዶች እየተፈጸመ ስለመሆኑ በስትራቴጂው የተቀመጠ ሲሆን፣ በአንድ በኩል ገንዘብ በመቀበል በአንድ መዝገብ ላይ ተገቢውን ውሳኔ እንዳይሰጥ ማድረግ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ከባለጉዳይ ከገንዘብ ውጪ በዘር፣ በሀይማኖት እና በትውውቅ ውሳኔ ማሳለፍ ነው ተብሏል።