የዋጋ ንረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜጎችን ህይወት እጅግ እየተፈታተነው ይገኛል።

አቶ አብዲሳ ገቢሳ ከባለቤታቸው እና ከሁለት ልጆቻቸው ጋር በአዲስ አበባ ከተማ መኖሪያ ቤት ተከራይተው ይኖራሉ።

የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት አቶ አብዲ፤ ወርሃዊ ደመወዛቸው 5ሺህ ብር ሲሆን የባለቤታቸው ገቢ ሲጨመር የቤተሰቡ ወርሃዊ ገቢ 8 ሺህ ብር ይደርሳል።

ይሁን እንጂ ይህን ቤተሰብ በ8ሺህ ብር ወርሃዊ ገቢ ማስተዳደር እጅጉን ለአቶ አብዲ ከብዷቸዋል።

“5ሺህ ብር ወር ጠብቄ ነው የማገኘው ነው። ወጪ እና የማገኘው ገንዘብ አይመጣጠንም። የቤት ኪራይ አለ፣ ቀለብ አለ፣ ለልጆች ትምህር ቤት ወጪ አለ። ልጆች ትምህር ቤት ሲሄዱ ምሳ ይዘው ነው የሚሄዱት። ትራንስፖርት፣ ልብስ እንዲሁም ለሠራተኛ የሚከፈል አለ። ሕይወት በጣም እየጎዳን ነው” ይላሉ።

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የዋጋ ግሽበት በተከታታይ ጭማሪ ሲያሳይ ቆይቷል።

በተለይም ኀብረተሰቡ በዕለት ተዕለት በሚጠቀምባቸው መሰረታዊ ፍጆታዎች፣ በግንባታ እቃዎችና በሌሎች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜጎችን ህይወት እጅግ እየተፈታተነው ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ መንግሥት የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በኑሮ ውድነቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳርፍ እንደሚችል ነዋሪዎች እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሚናገሩት ነው።

የበርካታ አገራት ፈተና የሆነው የኑሮ ውድነት

በያዝነው አውሮፓውያኑ 2022 በርካታ የዓለማችን አገራት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት አጋጥሟቸዋል።

በዩናትድ ኪንግደም ባለፈው ወር በ30 ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የኑሮ ውድነት በ7 በመቶ ተመዝግቧል።

ኬንያውያንም በምግብ ዘይት፣ በእህል እና በአትክልት እና ፍራፍሬ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ አስቆጥቷቸዋል።

ከቀናት በፊት የብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፤ “አሁንም በኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ፈተና እየገጠመን ያለው ከዋጋ ግሽበት ጋር በተገናኘ ሲሆን፥ከአምናው የሚያዚያ ወር ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ግሽበቱ 36.6 በመቶ ደርሷል። ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ነው፡፡” በማለት አትቷል።

አቶ አብዲ ገቢያ የምርቶች ዋጋ ‘በየቀኑ እና በየሰዓቱ’ በሚባል ደረጃ እየጨመረ ነው ይላሉ።

“በየቀኑ፤ በየሰዓቱ ይጨምራል። ለምሳሌ ባለፈው እሁድ ለልጅ ታሽጋ የምትሸጥ ወተት በ20 ብር ነበር የገዛሁት። ማታ ለልጅ ገዝቼ ልግባ ስል ዋጋው 30 ብር ሆኗል። 10 ብር ጨመረ ማለት ነው ! ” በማለት ይናገራሉ።

ይህ የመዲናዋ ከተማ ነዋሪ የኑሮ ውድነቱ መቋቋም ከምንችለው በላይ ሆኖብናል ይላሉ።

“የኑሮ ሁኔታ ይህ ነው ማለት የሚቻል አይደለም። በጣም እየከበደ ነው። ከኔ በታች ሆኖ የሚኖር ደግሞ አለ። ከኔ በታች ያለ ሰው በምን ተዓር እንደሚኖር አላውቅም” በማለት የተጫናቸውን የኑሮ ክብደት ይናገራሉ።

የአገሪቱ መንግሥት ለዋጋ ግሽበቱና ላስከተለው የኑሮ ውድነት እንደምክንያት አድርጎ የሚያቀርበው አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ነው።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የጥሬ ግብዓት ውድነት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እያጋጠሙ ያሉ አለመረጋጋቶች እንዲሁም የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ለዋጋ ግሽበቱና ለኑሮ ውድነት እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው።

ከጎረቤት ጋር እየተረዳዳን አብረን እንኖራለን

አቶ አብዲ ገቢሳ 8 ሺህ ብር ገቢያቸውን በብልሃት ወጪ ያደርጋሉ። በባለቤታቸው ገቢ የቤት ኪራይ ከከፈሉ በኋላ በቀሪው ገንዘብ ቀሪ ወጪዎች እንደሚሸፈኑ ይናገራሉ።

“እሷ ቤት ኪራይ ከቻለች እኔ ደግሞ እንደ ቀለብ፣ ትራንስፖርት፣ የትምህር ቤት ክፍያ፣ ለቤት ሠራተኛ ደመወዝ እክፍላለሁ። ከእነዚህ ወጪዎች የተረፈ ካለ ሌሎች ነገሮች አደርግበታለሁ” ይላሉ።

“ካልበቃን ደግሞ ከሰው እንበደራለን። ደመወዝ እስኪደርስ ከሰው እንበደራለን። ከጎረቤት ጋር እየተረዳዳን አብረን እንኖራለን” ይላሉ

የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር ምን እርምጃ መወሰድ አለበት?

መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ አልያም ለመቆጣጠር እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች አጥጋቢ አደሉም በሚል ተደጋጋሚ ትችቶች ይቀርቡበታል።

ምርት በማከማቸት ዋጋ እንዲንር ምክንያት በሚሆኑ ነጋዴዎች ላይ፣ በሸማች እና አምራች መካከል በመግባት የኑሮ ውድነት የሚያስከትሉ ነጋዴዎች ላይ በቂ እርምጃ አልተወሰደም የሚለው አንዱ መንግሥት ላይ የሚነሳ ቅሬታ ነው።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ለታ ሴራ (ዶ/ር) የአንድ ምርት ዋጋ ከፍ የሚለው ፍላጎት ከአቅርቦት ሲያንስ እንደሆነ አስታውሰው፤ መሠረታዊ አቅርቦቶች በገበያ እንዲኖሩ መንግሥት አምራቾችን መደገፍ አለበት ይላሉ።

መምህሩ ምጣኔ ሃብታዊ ምክንያት በሌላው ሳይኖር በአንድ ለሊት የምርቶች ዋጋ የሚጨምርበት አጋጣሚ እንዳለ ይናገራሉ።

“አንዳንድ ጊዜ በአገራችን በአንድ ለሊት ‘ከገበያ ጠፍቷል’ ሲሉ ይሰማል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ትናንት የነበረ ዕቃ በአንድ ለሊት ጠፍቶ አደራ ሲባል ምርቱን ደበቀው ዋጋውን ከፍ አድርገው መሸጥ የሚፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን ያሳያል” ይላሉ።

ይህን የመቆጣጠር ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑን የምጣኔ ሃብት መምህሩ ይናገራሉ።

አቶ አብዲ ገቢሳ በተመሳሳይ “መንግሥት ታች ወርዶ ዋጋቸውን እየጨመሩ ያሉ ነገሮችን አይቶ መፍትሄ መስጠት ይችላል” ይላሉ

የብር የውጭ ምንዛሬ የመግዛት አቅም መዳከም የተፈለገውን ያህል ውጤት በምጣኔ ሀብቱ ላይ እንዳላመጣ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በሌላ በኩል በምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች የሚነሳው የአገሪቱ የወጪና የገቢ ንግድን ማመጣጠን አልመቻሉ ነው።

የባለፈውን ዓመት ስንመለከት አገሪቱ ከወጪ ንግድ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ስታገኝ በገቢ ንግድ ደግሞ 15 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች፤ ይህንንም ከፍተኛ ልዩነት ማመጣጠን አለመቻሉ ከፍተኛ ማነቆ መፍጠሩን ባለሙያዎች የሚያስረዱት ነው።

በተጨማሪም ከወጪ ንግዷ በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ምርቶች ከውጭ አገር የምታስገባው ኢትዮጵያ የብር ምንዛሬ ማሽቆልቆል ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን ማስከተሉና ይህም በዜጎች ላይ እያሳረፈ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ ሆኗል።

ከዋጋ ግሸበትም ጋር ተያይዞ መሰረታዊ የሚባሉ ሸቀጦች ዋጋ መናርም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

እነዚህ የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች በዋነኝነት የሚጠቅሱት መፍትሄ አገሪቷ የገቢና ወጪ ንግዷን አመጣጥና የንግድ ሚዛን ጉድለቷን ማስተካከል ነው።

ይህንንም ለማድረግ ከግብርና ግብዓቶችና ቁሳቁሶች በመውጣት ወደ ማኑፋክቼሪንግ ዘርፉ መገባት መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራው የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ።

ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት በበኩሉ በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ጫና የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ለመቅረፍ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን እና እርምጃው ቀጣይነት እንደሚኖረው ይገልጻል።

ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል ግለቦች እንደ ስንዴ፣ ዘይት፣ የሕጻናት ወተት እና ስኳር ያሉ ምርቶች በራሳቸው የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር እንዲያስገቡ መፍቀድ አንዱ ነው።

የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤቱ፤ “በቀጣይ ጊዜያት በኢኮኖሚያችን ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ጫናዎችን ለመቀነስ የተለያዩ አንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ። የመድኃኒት፣ ነዳጅ፣ ማዳበርያ፣ ዘይት፣ እና ሌሎችም መሠረታዊ ሸቀጦች ግዥን በተገቢው ሁኔታ እንዲካሄድ፣ በእነዚህ ሸቀጦች አቅርቦት ላይ መንዛዛት እንዳይኖር በግዥ ሥርዓቱ ላይ አስፈላጊው ማስተካከያ ይወሰዳል” ብሏል።