የአሜሪካ ሴኔት በኮሚቴ በኢትዮጵያ ሰላም እና ዲሞክራሲ ለማበረታታት በሚል የቀረበውን ረቂቅ ሕግ ተቀብሎ ወደ ሴኔቱ እንዲያልፍ አደረገ።

የአሜሪካ ሴኔትየአሜሪካ ሴኔት በኮሚቴ በኢትዮጵያ ሰላም እና ዲሞክራሲ ለማበረታታት በሚል የቀረበውን ረቂቅ ሕግ ተቀብሎ ወደ ሴኔቱ እንዲያልፍ አደረገ።

ይህ ኤስ3199 የተባለው በኢትዮጵያ ሰላም እና ዲሞክራሲ ማበረታታት ወይም The Ethiopia Peace and Democracy Promotion Act በሚል የቀረበው ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ እንዲሁም በጦርነት ተሳታፊ ናቸው በተባሉ ግለሰቦች ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብ ለመጣል የተዘጋጀ ነው።

የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ዛሬ ማክሰኞ ምሽት መጋቢት 20/2014 ዓ.ም. ባደረገው ውይይት ረቂቅ ሕጉን ተቀብሎ ወደ ሴኔቱ እንዲቀርብ ወስኗል።

ይህን ረቂቅ ሕግ ለሴኔቱ ያስተዋወቁት የኒው ጀርሲው ሴናተር ሮበርት ሜንዴዝ ናቸው። ኤስ 3199 ረቂቅ ሕግ ጥቅምት 25/2014 ዓ.ም. ለሴኔቱ ቀርቦ ለሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተመርቶ ነው ውይይት ተደርጎበት ወደ ቀጣዩ ሂደት እንዲያልፍ የተደረገው።

ይህ ረቂቅ ሕግ ከዚህ በኋላ ለሙሉው ሴኔት ቀርቦ ሌላ ዙር ውይይት የሚደረግበት ሲሆን ሴኔቱ የሚያጸድቀው ከሆነ ለሕዝብ ተወካዮች ይቀርባል፣ የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀብሎት ካለፈ በቀጠይነት ለፕሬዝዳንቱ ቀርቦ ፊርማቸውን ካኖሩበት ሕግ ሆኖ ተግባራዊ ይሆናል።

በተመሳሳይ ሌላ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን የተመለከተ ረቂቅ ሕግ በአሜሪካ ምክር ቤት መተዋወቁ ይታወሳል።

ረቂቅ ሕጎቹን የሚቃወሙ ሰልፈኞችይህ ረቂቅ ሕግ ኤችአር 6600 የሚባል ሲሆን በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ከግጭት ጋር ተያይዞ ለደረሱ በደሎች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ ግለሶች ላይ ማዕቀብ መጣል ያስችላል።

የኢትዮጵያ መንግሥት አጥብቆ የተቃወማቸው እነዚህ ረቂቅ ሕጎች በፕሬዝዳንት ባይደን የሚጸድቁ ከሆነ አሜሪካ በደኅንነት፣ በፋይናንስ/በኢንቨስትመንት እና በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ትጥላለች።

ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 01/2014 ዓ.ም. ቀርቦ የነበረ ሲሆን፤ ረቂቅ ሕጉ ለምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች፣ ፍትሕ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች እና ለጦር ኃይል አገልግሎቶች ተመርቷል።

ኤስ 3199 ረቂቅ ሕግ ይዘት ምንድነው?

በዚህ ረቂቅ ሕግ ላይ አሜሪካ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ግንባታ እና የሰብዓዊ መብት መከበርን እንደምትደግፍ ተመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ለተከሰተ ግጭት መፍትሄ እና እርቅ ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፏን እንደምታደርግ ረቂቅ ሕጉ ያትታል።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የሚደረጉ የሰላም፣ የመረጋጋት እና የዲሞክራሲ ግንባታ ጥረቶችን በሚያደናቅፉ ግለሰቦች ላይ የንብረት እና የጉዞ እግድ ይተላለፍባቸዋል ይላል።

ይህ ረቂቅ ሕግ ሆኖ ከወጣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጦር መሳሪያ አትልክም። በአሜሪካው “Better Utilization of Investments Leading to Development Act of 2018” መሠረት ዋሽንግተን በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ድጋፍ አታደርግም።

እንደ ኤችአር 6600 ሁሉ ኤስ3199 ረቂቅ ሕግ አሜሪካ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የምታደርገው የደኅንነት እና የፀጥታ ድጋፍ እንዲቋረጥ ይጠይቃል።

ከዚህ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚሰጡ ብድሮች ወይም የብድር ማራዘሚያዎች እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፎች እንዳይፈቀዱ አሜሪካ ተሰሚነቷን እና ድምጽ የመስጠት መብቷን ትጠቀማለች ይላል ረቂቅ ሕጉ።

እነዚህ ረቂቅ ሕጎች ኢትዮጵያውያንን የሚጎዱ እና ጦርነቱን ለማብቃት የሚደረጉትን የሰላም ጥረቶች የሚያደናቅፉ ከመሆናቸው በተጨማሪ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ሙከራዎች ናቸው በማለት የኢትዮጵያ መንግሥት አጥብቆ ተቃውሟቸዋል።

እንዲሁም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሕጎቹ እንዳይጸድቁ ጥረትና የተቃውሞ ሰልፎች እያደረጉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሕጎቹን መጽደቅ የሚደግፉ ኢትዮጵያውያንም ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ።