ሸዋን ያላሳተፈ ፖለቲካ – መሐመድ አሊ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


(አቶ መሐመድ አሊ የቀድሞ ቅንጅት ከፍተኛ አመራር የነብሩ ሲሆን፣ ቅንጅት ተክቶ በወ/ት ብርቷን ሚድቀሳ የሚመራው የአንድነት ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆነው የሰሩ ናቸው። አቶ መሐመድ የሕግ ባለሞያና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚጦምሩ ጦማሪ ናቸው)

ሸዋን ያላሳተፈ ፖለቲካ sense አይሰጥም። “የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንዳሻው ሲዘውር ነበር” ተብሎ የሚታማውና በአደባባይም የሚከሰሰው ሸዋ ያጠፋቸውና የሚወቀስባቸው ነገሮች መኖራቸው እሙን ነው። በሌላ በኩል ግን ያገጠጠውን ሐቅ መሸፈን አይቻልም። ወደድንም ጠላንም ሸዋ አገር “ሠርቶ” ሰጥቶናል። በሌላ አነጋገር ሸዋ በዘመናዊ ሀገረ- መንግሥት ምሥረታ (nation state building) ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚና (indispensable role) እንደነበረው መካድ አይቻልም። ከዚህ አንፃር የሸዋን ታሪካዊ ውለታ መርሳትና ለዚህም የሚገባውን ዋጋ (due credit) አለመስጠት ንፉግነት ነው። በግሌ በፖለቲካው ውስጥ ሸዋን ጎላ ብሎ ካላየሁት የሆነ ነገር እንደጎደለ ይሰማኛል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ለጥፌው የነበረውን ጽሁፍ እንደገና ማጋራት ወደድኩ።

* * *

የሸዋ ፖለቲካ፣

ሸዋ በተለይ ከ19ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በተጨባጭ ሲዘውር እንደነበር አይካድም፡፡ ሸዋ “የሀገር እምብርት” ነው ማለትም ይቻላል፡፡ የሀገር እምብርት ነው ሲባል በመልከዓ-ምድራዊ አቀማመጡ ለሁሉም አማካይ ርቀት ላይ በመገኘቱ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሸዋ የአንድነት ማዕከል ሆኖ ሌሎችን ማሰባሰብ የቻለበት አንዳች መግነጢሳዊ ኃይል አለው፡፡ ሸዋ ዛሬም/ወደፊትም ቢሆን የስበት ማዕከል ነው።

ሸዋን ጉንፋን ሲይዘው ሁሉም በያለበት ያነጥሳል። ሸዋ በጠና ከታመመ ሁሉም ሊንገዳገድ ይችላል። ሸዋ የሀገር ራስ ነዋ! ያለሸዋ ሀገር ሊቆም አይችልም። ምስጢሩ ያለው እዚህ ጋ ነው። ይህ ነው “የሸዋ ፖለቲካ” የሚባለው፡፡ አንዳንዶች የሸዋ ፖለቲካ ሳይገባቸውና ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። እንዳውም የሸዋን ጭንቅላት “በቴስታ” ነቅንቀው አገር ሊያፈርሱ ነበር። ራሱን ከመታኸው አገር እንዴት ይቆማል?! ይህን ልታደርግ የምትችለው የሸዋ ፖለቲካ ካልገባህ ብቻ ነው።

በርግጥ የሸዋ ፖለቲካ “በሴራ የተቃኘ” መሆኑን የሚያሳይ ትንተና የሚያቀርቡ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ ቢሆንም ግን ሸዋ “ሀገርን ስለመበተን” አያሴርም፡፡ በአንፃራዊነት ሸዋ የሚያሴረው ለበጎ ነው ማለት ይቻላል። ሸዋ የኢትዮጵያን ግዛት ለማስፋፋትና አንድነቷን ለማጠናከር ሲባዝን የኖረ ባተሌ ማህበረሰብ ነው፡፡ በሸዋ ላይ የተለያዩ ክሶች የሚቀርቡ ቢሆንም፣ ሸዋ በታሪክ አጋጣሚ ያገኘውን የበላይነት በመጠቀም በተለይ ራሱን ለማበልፀግ አልሞከረም፡፡ ሸዋ ሀገር ወዳድ እንጅ ሁሉን ለራሱ የሚያግበሰብስ ስግብግብ አይደለም።

ሸዋ ሲባል ግን አማራውን፣ ኦሮሞውን፣ ጉራጌውንና ሌላውን ነባር የአካባቢው ነዋሪ ብቻ ሳይሆን በተለያዬ መንገድ ወደ ማዕከሉ እየተሳበና በዚያው ኑሮውን እየመሠረተ የሸዋን ሥነ-ልቦና የተላበሰውን ሁሉ የሚያካትት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በሸዋ አገዛዝ ላይ የሚቀርብ ታሪካዊ ክስ ካለም ሁሉንም የሚመለከት እንጅ በተወሰነ ማህበረሰብ/ብሔር ላይ ብቻ የሚጫን/የሚደፈደፍ አይደለም፡፡ ሲጀመር ሸዋ የህብረብሔራዊነት መገለጫ እንጅ ተነጣይ ማንነት ያለው አይደለም፡፡ ወዳጄ; የሸዋ ሥነ-ልቦናዊ ሥሪትና የሞራል ከፍታ ከዚያ በላይ ነው። አስፈላጊ ከሆነ በዚህ መስመር አጠንክሮ መከራከር ይቻላል፡፡

ሸዋ “የሀገር ዋልታና ምሰሶ!”