ከአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር (ኡጉጉሞ) የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ!

“የአፋር ሕዝብ በፌድራል መንግስት ተብዬው ስፖንሰርነት የተከፈተበተ ወረራ እንዲቀለበስ እየሰራን እንገኛለን” የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር (ኡጉጉሞ)

ከአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር (ኡጉጉሞ) የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ!

የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር (ኡጉጉሞ) ባለፉት አንድ አመት አስደናቂና አመርቂ የመደራጀትና የማደራጀትን ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝና አሁን ላይ ወደ ሙሉ ማጥቃት ለመሸጋገር ሙሉ ዝግጅትችን ማጠናቀቃችን ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው።

ብልጽግና መሩ ጦረኛው የአብይ አህመድ አገዛዝ ያለጦርነት ውሎ ማደር አይችልምና አገሪቱን የጦርነት ሜዳ ከአደረጋት እነሆ ስምንት ዓመታት ተቆጠሩ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም በኑሮ ውድነት፣ በሰላም እጦት፣ በሙስና፣ ሌብነት : ከአቅም በላይ በሆነ የግብር ብዝበዛ፣ በእገታ እና ወ.ዘ.ተ. እየተሰቃዬ ይገኛል። የብልጽግና አገዛዝ ጦርነት እስትንፋሱ ነውና ውድ የኢትዮጵያ ልጆችን በካኪ ልብስ እየጠቀለለ ወደ ጦርሜዳ በመሸኘት እናት ያለጦሪ ቀባሪ እየወረች ትገኛለች፤ ወጣቶች አጽማቸው የት እንደወደቀ ሳይታወቅ የአሞራ ቀለብ ከሆነ አመታት ተቆጠሩ፤ በመሆኑም ይህ ጦረኛ አገዛዝ እንዲገረሰስ እኛ የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር (ኡጉጉሞ) ሕዝባችን ከላላ አድርገን የአብይ አህመድ አገዛዝ ለመጣል ጠንካራ ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን።

ስለሆነም በዛሬው ዕለት ሕዳር 28 ቀን 2018 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ለመስጠት ተገደናል። የሚከተሉት ነጥቦችንም መላው የአፋር ሕዝብ ብሎም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የአብይ አህመድ ጦረኛ አገዛዝ ከሕዝብ ጫንቃ ላይ እንዲወርድ የሚፈልግ ኃይል ሁሉ ትኩረት እንዲሰጥበት ማሳሰብ እንፈልጋለን።

1ኛ. አሁን ላይ የአፋር ሕዝብንና የአፋር መሬትን ቁማር በማስያዝ የጦር ሜዳ ለማድረግ እየሰራ ያለው የአወል አርባ አገዛዝም ሆነ አለቃው አብይ አህመድ እያደረጋችሁት ያለው ነገር ትክክል አይደለም፤ የአፋር ሕዝብም ሆነ መሬት ነጻ ሊወጣ ይገባል እያልን በተለይ በአፋር መሬት ውስጥ ያላችሁ “ሀራ መሬት/ነጻ መሬት” በሚል የተደራችሁ የትግራይ የሰላም ኃይል ነን የምትሉ የአፋር ክልልን በአስቸኳይ ለቃችሁ እንድትወጡ እናሳስባለን። በዚህ ቀጥተኛ ተጎጅ የምትሆነው የአፋር ሕዝብም እነዚህ ኃይሎች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ጫና እንድታደርግ እንጠይቃለን።

2ኛ. በሙስጠፌ መሐመድ የሚመራው የኢሳ ኃይል አሁንም የወሰንና የደንበር ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በአፋር ሕዝብ ላይ ተከታታይ የሆኑ ኢ- ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። በቀጣይ በምርመራ የምናጋልጠው ሁኖ ዛሬም በኢሳ ኃይሎች ልጃገረጆችን ጨምሮ እናቶች እየተፈሩና እየተገደሉ መሆኑን እየገለጽን የሚዲያ ኃይሎችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና ተሟጋቾች የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ትኩረት እንድትሰጡ ማሳሳብ እንፈልጋለን።

3ኛ. የአወል አርባ አገዛዝ የአፋር ሕዝብን ጥቅምና መብት የሚከራከሩ ምሁራንን፣ ወጣቶችን፣ የፀጥታ ተቋማት አመራሮችን ዛሬም እያሳደደ፣ እያሰረ እና እየገደለ ይገኛል። ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲታቀብ እያሳሰብን፤ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ የፀጥታ ኃይሎች አጠቃላይ በአወል አርባ አገዛዝ እየተሳደዳችሁ ያላችሁ የአፋር ልጆች ወደ አፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር (ኡጉጉሞ) እንድትቀላቀሉ ጥሪ እናቀርባለን።

4ኛ. ጦረኛውን የአብይ አህመድ አገዛዝ እየታገላችሁ ያላችሁ ኃይሎች፦ አብይ መሩ የብልጽግና አገዛዝ አንድ ቀን በሰጠነው ቁጥር ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በዲፕሎማሲ እያንኮታኮታትና እየደፈቃት የሚገኝ ኃይል መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው። ይሄን ጉዳይ በአግባቡ በመረዳት የአብይ አህመድ አገዛዝን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ እንተባበር ስንል የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር (ኡጉጉሞ) ጥሪውን በይፋ ያቀርባል።

በመጨረሻም አንባገነን አገዛዞች እንደወደቁት፣ ጭፈራዎቻቸውም እንደተሳደዱት ሁሉ አንባገነኑ የብልጽግና አገዛዝ በቁርጠኛ ታጋዮች ይወገዳል፤ የአንባገነኑ መሪም ሆነ አገልጋዮቹ ለፍርድ አደባባይ እንደሚቀርቡ የአለም ታሪክ ምስክር ነውና ይህም በቅርቡ ይሆናል። አንባገነኑ ሕዝብ መጨፍጨፍ የስልጣኑ መሠረት ነውና ሎሌዎቹ ከሕዝብ ጎን እንድትቆሙ የመጨረሻ ጥሪ እናቀርባለን።

ድልና ድምቀት ለአፋር ኡጉጉሞ!
የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር (ኡጉጉሞ)
ህዳር 28 ቀን 2018 ዓ.ም