የኢትዮጵያውያን ደህንነት በኢትዮጵያውያን እንጂ በኤምባሲዎች መግለጫ አይረጋገጥም

መቀመጫቸውን አ/አ ያደረጉ አንዳንድ ኤምባሲዎች የኢትዮጵያን ደህንነትን በማስመልከት የሚያወጡት መረጃ አሁናዊ ትክክለኛ ሁኔታ የሚገልፅ አይደለም በማለት የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ትላንት በሰጡት መግለጫቸው ላይ ተችተዋል።

ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ፥ ” የኢትዮጵያውያን ደህንነት በኢትዮጵያውያን እንጂ በኤምባሲዎች መግለጫ አይረጋገጥም ” ብለዋል።

መንግስት የሽብር ተግባራትን አስቀድሞ እያከሸፈ መሆኑንም አሳውቀዋል።

ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በመግለጫቸው ምን አሉ ?

” ከፌዴራል፣ ከአ/አ አስተዳደር እና ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ከዙሪያው የፀጥታ ኃይሎች የተውጣጣው ግብረኃይል ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በአዲስ አበባ እና በዙሪያው ባደረገው ጥብቅ ፍተሻ የሽብር ስምሪት የተሰጣቸው የጥፋት ኃይሎች ከነዝርዝር እቅዳቸው እና ቁሳቁሳቸው ማለትም ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች፣ የመገናኛ ሬድዮዎች፣ ተቀጣጣይ ፈንጂዎች፣ የጦር ሜዳ መነፅሮች፣ የተለያዩ የፀጥታ አካላት ዩኒፎርሞች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የፀጥታ አካላት ባደረጉት በዚህ ኦፕሬሽን ከ90% በላይ ኢላማቸውን አሳክተዋል፤ የጥፋት ኃይሉ ሴራ ከሽፏል። አዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ አስተማማኝ ሰላማቸውን አረጋግጠው እንቅስቃሴያቸውን ቀጥለዋል።

የዴፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያለእንከን ተግባሮቻቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። “