የኢትዮጵያ መንግሥት አራት የአየርላንድ ዲፕሎማቶች መካከል በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ።

የኢትዮጵያ መንግሥት አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ ስድስት የአየርላንድ ዲፕሎማቶች መካከል አራቱ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ።

ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኢቲቪ በፌስቡክ ገጹ ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ አራት የአየርላንድ ዲፕሎማቶች ከአገር መባረራቸውንና በሳምንት ጊዜ ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መወሰኑን ዘግቧል።

የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውሳኔውን አረጋግጦ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በኤምባሲው ውስጥ ያሉትን አራት ዲፕሎማቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን ያሳወቃቸው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነው።

ይህ ውሳኔ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑትን የአየርላንድ አምባሳደርንና አንድ ሌላ ዲፕሎማትን እንደማይመለከት ተገልጿል።

የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ለዚህ የኢትዮጵያ ውሳኔ የተሰጠው ምክንያት “በአገሪቱ እየተካሄደ ካለው ጦርነትና ከሰብአዊ ቀውስ አንጻር በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትና በዓለም አቀፍ መድረኮች በያዘችው አቋም ነው” ብሏል።

የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይመን ኮቬኒ በኢትዮጵያ እርምጃ ማዘናቸውን አመልክተው “የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ አየርላንድ የምታራምደው አቋም ከአውሮፓ ሕብረት ጋር የተጣጣመ ነው” ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ከአስር ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሲወያይ ስብሰባዎቹን በመጥራት አየርላንድ የጎላ ሚና ከነበራቸው አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ይታወሳል።

አየርላንድ ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ የከፈተችው ከሃያ ዓመታት በፊት ሲሆን ኤምባሲው ከአፍሪካ ሕብረት እና ከኢጋድ ጋር ያለውን ግንኙነት ይከታተላል። አሁን በቀሩት ዲፕሎማቶች አማካይነትም ሥራውን እያከናወነ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

አራቱ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸው የዲፕሎማቶቹን ብዛት በሁለት ሦስተኛ የሚቀንስ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው “ውሳኔው ጊዜያዊ እንደሆነና ሠራተኞቻችን ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱ ተስፋ እናዳርጋለን” ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ተገቢ ያልሆነ ጫናና ጣልቃ ገብነትን እያንጸባረቁ ነው ስትል በተደጋጋሚ ትወቅሳለች።

በተደጋጋሚ በተደረጉትና አየርላንድ አንዷ ጠያቂ በነበረችባቸው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባዎች ላይ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ሉአላዊ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ አንዳንድ አገራት ያንፀባረቁትን አቋም መቃወሟ ይታወሳል።

ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ ኢትዮጵያ የአንድ አገር ዲፕሎማቶችን ከግዛቷ እንዲወጡ ስታዝ የመጀመሪያው ሲሆን ባለፈው መስከረም ወር ማብቂያ ላይ ግን ሰባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊዎች በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ እንደገቡ በመግለጽ ከግዛቷ እንዲወጡ አድርጋለች።