በርግጥም አገር ለማዳን፣ መንግስት ለመሆን ከተነሱ ሊደገፉ ይገባል – ግርማ ካሳ

“በመከላከል ላይ ብቻ የሚደረግ እንቅስቃሴ ውጤት አያመጣም፣ የማጥቃት ዘመቻ ይጀመር፣ በዓለ ሲመት ምጥርቅሾ እያላችሁ አትቀልዱ፣ ፋኖዎችና ሊዋጉ የመጡትን አስታጥቁ ..።” እያለን ስንጨቃጨቅና ስንሞግት ነበር፡፡
ኮረም፣ አላማጣ፣ ዋጃ፣ ሮቢት፣ ጎብዬ፣ ወልዲያ፣ መርሳ፣ ሁርጌሳ፣ ዉጫሌ : ሃይቅ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ሃብሮ፣ ኬሚሴ፣ ካራቆሬ፣ አጣዬ፣ ሰንበቴ፣ ሸዋ ሮቢት ብለው ደብረ ሲና ደጃፍ እስኪደርስ መጠበቅ አልነበረበትም፡፡ እዚህ የዘረዘርኳቸው ከተሞችና የሌሎች የሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ የሰሜን ጎንደር፣ የስሜን ሸዋ፣ የዋገመራ፣ የአፋር ወረዳዎች መያዝ፣ በዚያ ያለው የሕዝብ ስቃይና ሰቆቃ ተሰምቷቸው ጦርነቱን ዋናና ትልቁ አጀንዳቸው ማድረግ ነበረባችው፡፡ ለ4 ወራት ያንን ሳያደርጉ ቆይተው ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ እጅግ በጣም ትልቅ ዋጋ ተከፍሏል፡፡
አሁን ወያኔዎች ሸዋሮቢትን ይዘው ደብረ ሲና ደጃፍ ሲደርሱ ፣ ለአዲስ አበባ እየቀረቡ ስለሆነ፣ የፖለቲካ አመራሮች ከእንቅልፋቸው ነቀተዋል፡፡ በመጨረሻ፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ጀምሮ፣ በተለያዩ ግንባሮች በመሰማራት በሕወሃትና ኦነግ የተደቀነው የአገር ህልውና አደጋ ለመመከትና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡ የረፈደም ቢሆን እጅግ በጣም ትልቅና ወሳኝ ውሳኔ ነው፡፡
ወደ ኋላ ሳይሆን ወደፊት ነው ማየት ያለብን፡፡ የአገርንና የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም አለብን፡፡
ከብልጽግና የፖለቲካ አመራር ጋር መሰረታዊ ልዩነቶች ቢኖረዉም፣ ግርማ ካሳ፣ በዚህ ወቅት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሙሉ ለሙሉ ከጎናቸው ይቆማል፡፡ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው፡፡
አሁን የሚደረገው ትግል በብልጽግናና በወያኔ/ኦነግ መካከል አይደለም፣ ከሕዝብ ጋር የሚደረግ ትግል ነው፡፡
በዚህ ወቅት ዶር አብይ አህመድ፣ የተመረጠ ነው የምንልና በነጻና ፍታሃዊ ምርጫ አልተመረጠም የምንል ፣ የተለያዩ ልዩነቶች ያሉን ብዙ ነን፡፡ ግድ የለም፣ እርሱ ላይ በኋላ እነከራከራለን፡፡ አሁን፣ ተመረጠም አልተመረጠም አገርን ለማዳን የሚደረገው ትግል ለመምራት ተዘጋጅቻለሁ እያለ በመሆኑ፣ “መሪያችን ነው” በሚል፣ ሳንከፋፈል፣ ከጎኑ መቆም አለብን፡፡ ወያኔና ኦነግ ልካቸውን ካገኙ በኋላ ካስፈለገም እንደገና ምርጫ ይደረጋል፡፡ እርሱ አሁን ሊያሳስበንና ሊያጨቃጭቀን አይገባም፡፡
ደግሜ እላለሁ፣ ስንቃወማቸው፣ ስንተቻቸው፣ ስናወግዛቸው የነበሩት ስራቸውን እንዲሰሩ ነበር፡፡ ለመስራት ሲዘጋጁ፣ አገርን ለማዳን ሲነሱ፣ መንግስት መሆን ሲጀምሩ፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ ኢትዮጵያዉያን ከጎናቸውን መሰለፍ አለብን፡፡
በዚህ አጋጣሚም በተለያዩ ምክንያቶች ሕወሃትንና ኦነግን የምትደገፉ ወገኖች ጠባችሁ ከዶር አብይና ከብልጽግ ና ፓርቲ ጋር ሳይሆን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መሆኑ በመረዳት፣ አቋማችሁን እንደገና እንድትመረምሩ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
በፊትም ሕወሃቶችና ኦነጎች አቅም ኖሯቸው አልነበረም፡፡ እኛው ጋር የነበረ ችግር ነው የልብ ልብ የሰጣቸው፡፡ እመኑኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጦርነት ድባብ ወጥተን ሰላማዊ የፖለቲካ ክርክሮች ላይ: ልማት ላይ ማተኮሩ ውስጥ እንገባለን፡፡ ወያኔና ኦነግ ታሪክ ይሆናሉ ::
የዉጊያው ሁኔታ – ዘገባ ዘግርማ #ግርማካሳ
11/23/2021
ሕወሃቶችና ኦነጎችብዙ ጥፋት ፈጽመዋል። እየፈጸሙም ነው። እነዚህን አሸባሪዎች ማስቆም የአገርን ሕልውና ማsቀጠል ነው። የፖለቲካ አመራሮች እንዋጋለን ብለው መነሳታቸው የግድ ጠምንጃ ይዘው ይተኩሳሉ ማለት አይደለም። ጦርነት መተኮስ ብቻ አይደለም። ትልቁ ነገር የፖለቲካ አመራሪ በዉጊያ አቅራቢያ መሆናቸው አንደኛ ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ ዙሪያ፣ ሁለተኛ ውሳኔዎችን በቶሎ በመወሰን ዙሪያ፣ ሶስተኛ በዚያ ለሚዋጋው ሰራዊት ሞራልና ወኔን በመቀስቀስ ዙሪያ እጅግ በጣም ትልቅና ወሳኝ ሚና አለው።
በአሁኑ ወቅት ጦርነቶች በበርካታ ግንባሮች እየተካሄዱ ነው።
1. የማይጠምሪ ግንባር
2. የጋሸና ግንባር
3. የዳዉንት ግንባር
4. የወረኢሉ ግንባር
5. የመንዝ ግንባር
6. የሸዋ ሮቢት/ደብረ ሲና ወይንም ይፋት ግንባር
7. የአፋር ካሳጊታ ግንባር
8. የአፋር ቡርቃ ግንባር
9. የአፋር ጭፍራ ግንባር
10. የአፋር /ሸዋ ሮቢት ግንባር
11የዋገመራ ግንባር
12. የራያ ቆቦ ግንባር
13 የሰሜን ወሎ ሃብሮ.ወረባቦ ግንባር
ከነዚህ መካከል በመጀመሪያዎቹ አስሩ ፣ በመከላከል ላይ ብቻ ነበር እንቅስቃሴ ሲደረግ የነበረው። በዋገመራ፣ በራያ ቆቦና በስሜን ወሎ ሃብሮ/ወረባቦ ግንባሮች ግን የአማራ ልዩ ኃይሎችም ፋኖዎች ሚሊሺያዎች የሽምቅ ዉጊያዎች እያደረጉ ወያኔ ላይ ከፍተኛ የማጥቃት ዘመቻዎች ሲያደረጉ ነበር።
በርካታ የዋገመራ ዞን ወረዳዎች ሰቆጣ ከተማን ጨምሮ በወገን ጦር ቀደም ሲል ነጻ ወጥተዋል። በዞብል ተራራ መደራጀት የጀመሩት የራያ ቆቦ ሚሊሺያዎችም የቆቦ ወረዳ ተቆጣጥረው፣ ወልዲያ ደጃፍ እስከ ጎብዬ ደርሰዋል። ወያኔ በቆቦ በኩል መውጣትና መግባት ካቆመች ሳምንታት አልፈዋል።፡እነ ጀግናው ሃሰን ኪረሙ በሃብሮና ወረባቡ ቆላማው የወሎ ወረዳዎች ከፍተኛ ጉዳት ወያኔ ላይ አድርሰዋል። ሃራ፣ መርሳ ፣ ወረባቡ ላይ ያለው የወያኔ ጦር ከፍተኛ ችግር ውስጥ አስገበተዉታል።
ዛሬ የፖለቲካ አመራሮ የወስነውን ውሳኔ ተከትሎ፣ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት
1) ለሁለት ወር ቆመው የነበሩ የጠለምትና የጋሸና ጦሮች እንቅስቃሴ ጀምሯል።
2) በጋሸናና በላሊበላ መካከል ያለችውን የድብኮ ከተማ ለማስለቀቅ ውጊያ እየተደረገ ነው።
3) ላሊበላን ለማስለቀቅ የአማራ ልዩ ኃይል ጥንቃቄ ያለው እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። በላሊበላ ዙሪያ ውጊያዎች አሉ።
4) በመከላከል ላይ ተጠምዶ የነበረው የአፋር ልዩ ኃይል፣ ሚሊሺያዎችና የመከላከያ ጥምረት ጦር ወደ ባቲ እየገሰገሰ ነው።
5) መከላከያ በኮምቦልቻ ከተማ ወደ ከሚሴ በሚወስደው መንገድ የምትገኘዋን የሃብሮ ከተማ በቆረጣ እንደተቆጣጠረ የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ነው።
6) በይፋት ግንባር፣ በደብረ ሲና እንዲሁም በሸዋ ሮቢት አካባቢ ከፍተኛ ዉጊያዎች እየተደረጉ ነው። በዚህ ያለው የወያኔ/ኦነግ ጦር ከፍተኛ እንደመሆኑ ፣ ሙሉ ለሙሉ ከተሸነፈ የወያኔና የኦነግ አከርካሪ ተመታ እንደማለት ነው።
7) በመሃል ሜዳ፣ ሞላሌ አድርጎ በሰላ ድንጋይ በኩል ደብረ ብርሃን ለመንቀሳቀስ የተሰማራው የወያኔና ኦነግ ጦር ሰላ ድንጋይ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት፣ ተበታትኗል።የተበታተነው ለመያዝ ወይንም ለመልቀም ሰፊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው።
በዚህ ሁኔታ ወገኖች በሰዓታት ውስጥ ባይሆንም በቀናት ውስጥ ላሊበላ፣ ጋሸና፣ ሸዋ ሮቢት፣ አጣዬ፣ ካራቆሬ፣ ማጀቴ፣ ባቲ፣ ኬሚሴ፣ ኮምቦልቻ ነጻ ይወጣሉ ብዬ ነው የምጠብቀው።
ምን አልባት በተለይም የሸዋ ድል ከተፋጠነ ወያኔዎችና ኦነግ እጅ ሊሰጡና ጦርንቱን በይፋ ሊያቆሙ ይችላሉ። #ግርማካሳ