እዘምታለሁ ! ከአብይ ጋር ፉክክር ወይንስ የሃገር ፍቅር ? አብይ ከዘመተ ቆየ ፤ ያኔ የት ነበርክ ?

Image Konjit Sitotaw – ካሁን ቀደም እንዳይዘምቱ የተከለከሉ ይመስል ብልጽግና ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ተከትለው እንዘምታለን የሚሉ አጨብጫቢዎች መብዛታቸው ያነጋግራል። ካሁን ቀደም በተደጋጋሚ መንግስት ጥሪ ሲያቀርብ የት ነበሩ። ሃገርንና ሕዝብን የሚያስበሉ እንዲህ አይነቶች ቀድመው የተገኙ የሚመስሉ እንወደድ ባይ አስመሳይ አማሳኞች ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒትር አብይ አሕመድ የብልጽግናን ስብሰባ ተከትለው ባወጡት ረዥም መግለጫ ላይ ጊዜው ሀገርን በመሰዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ነው። ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ ማለታቸውን ተከትሎ በርካቶች መሪያችንን ተከትለን እንዘምታለን ማለታቸው አስገራሚ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ሃገራዊ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃገራችንን እናድን በማለት ከወራሪ እንከላከል ሲሉ ተማጽነዋል ። ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ምላሽ የሰጡ እንዳሉ ሁሉ ለሴራ ፖለቲካ አንገዛም ሲሉ የነበሩ ድንገት ተነስተው እንዘምታለን ሲሉ ጥያቄ ያስነሳል። በተደጋጋሚ ግንባር ላይ እንገናኝ ሲባሉ ለጦርነቱ ስም ሲያወጡ የነበሩት መሪየ ከዘመተ እኔም እዘምታለሁ እያሉ የሚደሰኩሩት ሰዎች ምን አስበው እንደሆነ አይገባኝም:: መሪህ ስለዘመተ ሳይሆን ሃገርህ በሰይጣኖች ስለተወረረችና ወገንህ ለእልቂት ሃገርህ ለመፍረስ ስለተዳረገች ነው መዝመት ያለብህ::

መዝመት ያለብን እኮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነስተው ልዘምት ነው ማለታቸውን አይተን ሳይሆን ሃገራችንን እና ሕዝባችንን ከሰቆቃና ከወረራ ለማዳን የዜግነት ግዴታችንን አውቀን ሊሆን ይገባል። ጠቅላዩ ካልዘመተ እኔ አልዘምትም የሚል ፉክክር ተይዞ መግለጫ እንደሚጠብቅ ሰው ድንገት መጮህ አዋጪ አይደለም ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ሃገራችንን ከወራሪዎች እንድንከላከል ነግረውናል ቀስቅሰዋል፤ ከዘመቱም ቆይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወሬ ብቻ ወይም በጭብጨባ ብቻ ሳይሆን እንደ መሪ ሚናቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። አሁንም እየተወጡ ነው።

ጠቅላዩን ተከትለው እንዘምታለን የሚሉ ግን ፉክክር ነው ያስመሰለባቸው። እስካሁን የተቀመጥክ አብይ ካልዘመተ አልዘምትም ብለህ ነው? እሱ መስዋዕት ሳይሆን እኔ ለምን እሰዋለታለሁ ብለህ ነው? ከአብይ ጋር እልህ ተጋብተህ ነው ያልዘመትክ?