ስለ ክሱ ምንም እውቀት ያሌላቸው አዳዲስ ዳኞች በተሰየሙበት የነእስክንድር ነጋ ሐሰተኛ ክስ ላይ ለመወሰን ተቸገርን አሉ ።

በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ከአለፈው ዓመት ሐምሌ 14 ቀን በኋላ ዛሬ ጥቅምት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በአካል ቀርበዋል። በዓቃቤ ሕግ ጠያቂነት በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታግዶ የቆየው የምስክሮች አሰማም ሂደትም ነገ ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ክርክር ተደርጎበት እንደሚቀጥል አዲስ የተሰየሙት ሦስት ዳኞች ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግ በዛሬው ችሎት ሁለት ምስክሮችን በግልፅ ችሎት እንዲመሰክሩ ይዞ መቅረቡን ተናግሯል። ሆኖም “አሉ፤ መጥተዋል” ከማለቱ ውጭ የችሎቱ አዳራሽ ውስጥ ገብተው አላየናቸውም።

የእነ እስክንድር ጠበቆች የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በፈረደው መሰረት ምስክሮች በግልፅ ችሎት የሚቀርቡ ከሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት የምስክሮች ስም ዝርዝር ቀድሞ ለተከሳሾችና ለጠበቆች መሰጠት እንዳለበት ጠይቀዋል። በዚህም የምስክሮችን ማንነት ለማወቅና መስቀለኛ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ እንደሚያስችላቸው ጠበቆች ሔኖክ አክሊሉ፣ ሰሎሞን ገዛኸኝ እና ቤተ ማርያም አለማየሁ ጠይቀዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ስም ዝርዝራቸውን እንዲሰጥ በፍርድ ቤት አለመታዘዙን ጠቅሶ ተከራክሯል። ጠበቆችም ጉዳዩ ቀደም ሲል በተከራከሩበት የምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ መሰረት ሳይሆን በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ የሚታይ በመሆኑ ለብቻው ልዩ ትዕዛዝ እንደማያስፈልገው እና ስም ዝርዝራቸው አስቀድሞ መሰጠት እንዳለበት በወንጀለኛ ሕጉ በግልፅ መቀመጡን ጠቅሰው ሞግተዋል። በተጨማሪም ቀደም ሲል በተወሰነው መሰረት በአንድ ችሎት ቢያንስ አራት ምስክሮች ማቅረብ ሲገባው ሁለት ብቻ ለማቅረብ መጠየቁ አግባብ እንዳልሆነ፤ ይልቁንም ያለ ፍትሕ ጊዜውን ለመግፋት ያለመ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በዚህም መሰረት የምስክሮችን ስም ዝርዝር አስቀድሞ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ወስኗል። ክርክሩ ካለፉት ችሎቶች የቀጠለ በመሆኑ ዳኞች ያለፈውን እንደ ማያውቁትና ለመወሰንም መቸገራቸውን ገልፀዋል። ዶሴውን ሳያነቡት መምጣታቸውንም ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ገና ዶሴው ሲጀመር በቅድመ ምርመራ ከወንጀል ነፃ ተብለው የተሰናበቱና በዚሁ መዝገብ ተከሰው የነበሩ ሰዎችን ስም ጭምር አሁን በክሱ ውስጥ እንዳሉበት አድርገው ዳኛው ሲጠሩ ተደምጠዋል። ሆኖም 6ኛ ተከሳሽ የነበሩትን ስም እንደጠሩ ከ5ኛ ተከሳሽ በኋላ ያሉት በነፃ የተሰናበቱ መሆኑ በጠበቆች ተነግሯቸው ከስህተታቸው ታርመዋል።

አዲሶቹ ዳኞች ራሳቸውን ለችሎቱ ባስተዋወቁበት ጊዜ ሙሉ ስማቸውን አልተናገሩም። ሰብሳቢ ዳኛው ዘላለም እንደሚባሉ ከተናገሩ በኋላ የቀኝ ዳኛው ይልማ፤ የግራ ዳኛዋ ደግሞ አርቡማ እንደሚባሉ ተናግረዋል።

በዛሬው ችሎት እስክንድር ነጋ እና አስቴር ስዩም ከመናገር ተቆጥበዋል። አስካለ ደምሌ ከዚህ በፊት በምርመራ ሰበብ ሲያንገላታት እና በባልደራስ ውስጥ ያላትን የትግል እንቅስቃሴ እንድታቆም መደለያዎችን ሲያቀርብላት የነበረ የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ ባለፈው ነሐሴ 28 ቀን ወደ ምትኖርበት ቃሊቲ ወህኒ ቤት ውስጥ ሄዶ እንዳነጋገራት ተናግራለች።

በዚህም የወህኒ ቤት ፖሊሶችና አስቴር ስዩም በነበሩበት “በደል ያደረስኩብሽ በመንግሥት ታዝዤ ነው” ያላት መሆኑን ጠቅሳለች። ይህም ክሱ ሀሰተኛ መሆኑን የሚያስረዳ ከመሆኑም በላይ የደህንነት ባለሙያው በሕግ እንዲጠየቅላት ጠይቃለች። ለምርመራ ይዞት በነበረው የእጅ ስልኳ ውስጥ የነበሩ ሰነዶች መደምሰሳቸውንም ጠቅሳለች።

ስንታየሁ ቸኮል በበኩሉ የኩላሊት፣ የጉበት እና የጥርስ ህመሞች እንዳሉበት ጠቅሶ በፖሊስ አባላት ታጅቦ በመረጠው ሆስፒታል በግል ወጭው እንዲታከም ጠይቋል ። አሁን እየታከመበት ያለው የወህኒ ቤት ክሊኒክ ሰዎች ተጣልተው ሲፈናከቱ በፕላስቲክ ከማሸግና ቁስል ከማጠብ የዘለለ አገልግሎት እንደማይሰጥም ተናግሯል።

ፍርድ ቤቱም ጉዳዮችን በቀጣይ ችሎቶች እንደሚያያቸው ገልጿል።

በዛሬው ችሎት አዳራሹ ጠቦ ሰዎች አስከሚመለሱ ድረስ በርከት ያለ ታዳሚ ተገኝቷል። የባለደራስን ምክትል ፕሬዚደንት አቶ አምሀ ዳኘውኝ ጨምሮ የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ የምርጫ 2013 ዕጩ ተወዳዳሪዎችና ሌሎችም ተገኝተዋል።

(ጌጥዬ ያለው)